1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የመሬት እጦት እና ጥበት ወጣቶችን ከትውልድ ቀያቸው ለመሰደድ ከሚያበቁ መካከል ይጠቀሳሉ

ረቡዕ፣ ጥር 3 2009

የተሻለ የስራ እድል እና  ገቢ የሚፈልጉት የኢትዮጵያ ወጣቶች የመሬት ጥበት እና እጥረት፤የከባቢ አየር ለውጥ እና የፖሊሲ ድጋፍ ማጣት በግብርናው ዘርፍ ፈተና እንደሆኑባቸው ሲናገሩ ይደመጣል። የጥናት ባለሙያዎች ወጣቶቹ የእርሻ ማሳቸውን ጥለው መሰደድ ጀምረዋል ሲሉም ይደመጣሉ።

https://p.dw.com/p/2Ve7e
Utopie Äthiopien
ምስል Gino Kleisen

የኢትዮጵያዉያን ወጣት ገበሬዎች ፈተና

የ30 አመቱ ቢላል ጂብሪል ከኢትዮጵያ ተሰዶ ሳዑዲ አረቢያ ከገባ አራት አመታት ተቆጠሩ። በአማራ ክልል ከቻግኒ አቅራቢያ ጓንጓ ወረዳ ተወልዶ ያደገው ቢላል የገበሬ ልጅ ነው። በጠባብ ማሳቸው በቆሎ፣ጤፍ ዳጉሳ አልፎ አልፎም ኑግ እንደሚዘሩ የሚናገረው ቢላል አመታዊ ምርታቸው ከ15 ኩንታል እንደማይበልጥ ይናገራል። ቢላል የተሻለ ነገር ፍለጋ ሥደት የጀመረው እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የተሻለ የእርሻ መሬት የተሻለ የሥራ ቦታ ፍለጋ ቢላል ከቻግኒዋ የጓንጓ ወረዳ ወደ ቤኑንጉል ጉምዝ ቡለን ወረዳ አቀና። «መሬቱ ማዳበሪያ አይፈልግም። ከወጪ እናርፋለን።» ይላል ወደ ቡለን ወረዳ ለማቅናት ከወሰኑባቸው ምክንያቶች አንዱን ሲያስታውስ። የቤት እንስሳት እርባታ ጀምሮ ተሳክቶለት እንደነበርም ይናገራል።

ቢላል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቡለን ወረዳ የጀመረው የእርሻ እና እንስሳት እርባታም አዋጪ ቢሆንም መቀጠል አልቻለም። የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት እነ ቢላል የሰፈሩበት አካባቢ ለደን የተከለለ በመሆኑ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፉ። ወደ 500 የሚጠጉ አባወራዎች እስከ ክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ ፍርድ ቤት ያደረጉት ክርክር የፈየደላቸው ነገር አልነበረም።

ገበሬ መሆን የሚሻው ማነው?

Äthiopien Ackerland
ምስል DW/Eshete Bekele

የኢትዮጵያ ሥታስቲክስ ባለሥልጣን በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ብሔራዊ የዳሰሳ ጥናት እንደገለፀው በገጠር ከሚኖሩ ዜጎች መካከል ከግብርናው ዘርፍ ውጪ በሥራ ላይ የተሰማሩት 10 በመቶ ያክሉ ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያውያን የመሬት ባለቤት ባይሆኑም (የመሸጥ የመለወጥ መብት ባይኖራቸውም) በግብርና መሰማራት የሚፈልጉ እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ ዜጎች የገጠር መሬት ለእርሻ የመጠቀም መብት አላቸው።  በመሬት እጥረት ምክንያት የአገሪቱ የማከፋፈል ፖሊሲ ከተቀየረ ወዲህ ግን ወጣቶች የእርሻ መሬት የማግኘት እድላቸው የጠበበ መሆኑን የኖርዌይ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎቹ ሶስና በዙ እና ስታይን ሆልደን በሰሩት ጥናት ጠቁመዋል።

ጠባቧ የአባቱ ማሳ የወጣትነት ፍላጎቱን እንደማታሟላ ገብቶት ወደ ደቡብ አፍሪቃ የተሰደደው ዳናን ኑቾ ተወልዶ ያደገው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በሐድያ ዞን ነው። ዛሬ በሕይወት የሌሉት አባቱ በነበረቻቸው ጠባብ መሬት ላይ እንሰት፤በቆሎ እና ጤፍ ያመርቱ ነበር።

 ኑሮውን ጁሐንስበርግ ዙሪያ ያደረገው ዳናን ዛሬ አነስተኛ የሸቀጣሸቀጥ ንግድ ላይ ቢሰማራም የአባቱን ማሳ ግን አልዘነጋትም። ዝናብ ላይ ጥገኛ የሆኑት ገበሬ አባቱ ከአነስተኛ መሬታቸው በሚያገኙት ምርት ዳናን ጨምሮ ስድስት ልጆች ያስተዳድሩ ነበር። «መሬቱ ትንሽ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ አያመርቱም።» የሚለው ዳናን ኑሮውን ለማሸነፍ ከሁለት ወንድሞቹ ጋር ስደት ገባ-መድረሻቸው ደግሞ ደቡብ አፍሪቃ።

የመሬት እጦት ያሳሰባቸው ወጣቶች ሌሎች አማራጮች መቃኘት ከጀመሩ መሰነባበታቸውን ሶስና በዙ እና ስታይን ሆልደን በሰሩት በሰሩት ጥናት ገልጠዋል። ባለሙያዎቹ በዳሰሳ ጥናታቸው ካነጋገሯቸው ወጣቶች መካከል 9 በመቶው ብቻ በግብርና ሥራ መቀጠል የሚፈልጉ ናቸው። እንደ ቢላል ጅብሪል እና ዳናን ኑቾ ሁሉ አገር ጥለው መሰደድን የመረጡ አሊያም ማሰላሰል የያዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን ቁጥር በርካታ ነው። በቦን ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናት ማዕከል (ZEF) በግብርና ኤኮኖሚ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የፒ.ኤች.ዲ. ምርምራቸውን በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ተካልኝ ጉቱ ጉዳዩ በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባው ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ወጣቶች በግብርና ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እያጠኑ የሚገኙት አቶ ተካልኝ ነባራዊ ሁኔታው ከቦታ ቦታ ይለያያል ኢe ናቸው። «ኦሮምያን የወሰድክ እንደሆነ ከአካባቢ አካባቢ ቢለያይም ወጣቱ በአጠቃላይ ግብርናን ጥሎ አልሔደም።» የሚሉት አቶ ተካልኝ ሥራ ቢቀይሩ እንኳ «ዞሮ ዞሮ ከግብርና ጋር በተያያዘ የሥራ ዘርፍ ውስጥ ነው የሚሰሩት።» ሲሉ ተናግረዋል። «በጣም የመሬት እጥረት ያለበት እና ለግብርና ምቹ ያልሆኑ አካባቢዎች በወጣቶች ዘንድ ወደ ከተማ የመሰደድ አዝማሚያ ይታያል።» ሲሉም አክለዋል።

Äthiopien Mädchen beim Wasserholen
ምስል picture alliance/Ton Koene

አቶ ተካልኝ ወጣቶችን ከማሳ ከሚያሸሹ መካከል የመሬት እጥረት አሊያም ጥበት አንዱ ቢሆንም ሌሎች ፈተናዎች መኖራቸውንም ይናገራሉ። የገበያ ችግር ፤የመንቀሳቀሻ ገንዘብ እጦት እና የከባቢ አየር ለውጥ በዘላቂነት ወጣቶች ግብርናን ሙያዬ ብለው ለመያዝ እንደሚፈትኗቸው አቶ ተካልኝ ጨምረው ገልጠዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ጎብዬ ከተባለች ከተማ የሚኖረው ደርቤ ቢሆን ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ዘርፍ በተፈጥሮ ሐብት አያያዝ (Natural Resource Management) ተምሮ ቢመረቅም ሥራ ሲፈልግ ሁለት አመታት አለፉ። ጤፍ እና ማሽላ የሚያመርቱት የደርቤ ቤተሰቦች ወደ አራት ሔክታር በሚጠጋ የእርሻ መሬታቸው በዚህ አመት ወደ 15 ኩንታል ምርት አግኝተዋል።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በትንሿ ከተማ ጎብዬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ወልዲያ የተማረው ደርቤ የጤና ባለሙያ አሊያም መሐንዲስ የመሆን ህልም ነበረው። የተፈጥሮ ሐብት አያያዝ በመማሩ ግን አይከፋም። ተወልዶ ባደገበት ቀዬ ለዘመናት ሲታረስ የኖረው መሬት ለምነት ማሽቆልቆል ግን እጅጉን ያሳስበዋል። «ከባዱ ነገር ሰሜን ወሎን ድርቅ ያጠቃዋል። ጥሩ ዝናብ የሚዘንም እና ዘመናዊ መስኖ ቢኖር ጥሩ ጥሩ ነገሮች ማምረት እችል ነበር» የሚለው ወጣቱ ሥራ ፈላጊ የአካባቢው የእርሻ ማሳ «በተደጋጋሚ ስለሚታረስ ማዕድኑ በሙሉ የለም።» ሲል ያክላል። 

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ የግብርና ባለሙያ የሆኑት አቶ መሐመድ የዕለት ተለት ውሏቸው ከገበሬዎች ጋር ነው። ላለፉት አስር አመታት በሙያቸው ያገለገሉት አቶ መሐመድ ገበሬዎች አካባቢያቸውን እንዲንከባከቡ፤የወንዝ ተፋሰሶችን እንዲያለሙ እገዛ ያደርጋሉ። ዋነኛ አላማቸው የገበሬውን ምርታማነት ማሳደግ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሽቆለቁለው ምርታማነት ወጣቶችን ከማሳ እያሸሸ መሆኑን የግብርና ባለሙያው አስተውለዋል።

Wasser in der Landwirtschaft IWMI International Water Management Institute
ምስል Hugh Turral

«ወጣቱ ላይ በአሁኑ ሰዓት የማስተውለው ከግብርና ውጭ የሆኑ ሥራዎችን የመሥራት ኃሳብ ነው።» የሚሉት አቶ መሐመድ ወጣቶች ወደ ከተማ ተጉዘው ሥራ መፈለግን እንደሚመርጡ ተናግረዋል። የምርት መጠን መቀነስ፤የመሬት ጥበት እና የቤተሰብ ብዛት ወጣቶቹን ከማሳ የሚያሸሹ ችግሮች እንደሆኑ ተናግረዋል።

የሥራ ፍለጋው ያልተሳካለት ደርቤ የእንስሳት እና ዶሮ እርባታ ለመጀመር ያዘጋጀውን እቅድ ለወረዳው ቢያቀርብም የመነሻ ገንዘብ ማግኘት አልቻለም። ደርቤ «ወረዳችን ድጋፍ አያደርግም። ከመንግሥት የሚለቀቅ ገንዘብም ተፋፍኖ መንገድ ላይ ነው የሚቀረው። ዘንድሮ ለወጣቶች ተብሎ ብርም ነበር ምንም ነገር አልደረሰንም» ሲል ያማርራል።

አቶ ተካልኝ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የሥራ አጥነት በቅርቡ ለተከሰተውን ተቃውሞ እና ኹከት ገፊ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ ነበር የሚል እምነት አላቸው። ከአገሪቱ ሕዝብ 70 በመቶው ሕፃናት እና ወጣቶች ቢሆኑም እንኳ የመንግሥት ፖሊሲዎች ትኩረት ነፍገዋቸዋል ሲሉም ይተቻሉ።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ