1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ወጣቶች የምርጫ ተሳትፎ

ዓርብ፣ ጥር 15 2007

ኢትዮጵያ ዉስጥ በመጪዉ ግንቦት ወር ለሚካሄደዉ አጠቃላይ ምርጫ ድምፁን ለመስጠት 33 ሚሊዮን መራጭ ሊመዘገብ እንደሚችል የምርጫዉ አስተባባሪ ባለስልጣናት ይገምታሉ። ወጣቱ በሚያመዝንባት ኢትዮጵያ፤ የወጣቱ የምርጫ ተሳትፎ ምን ይመስላል? የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ርዕሳችን ነው።

https://p.dw.com/p/1EP8a
Addis Abeba Äthiopien Wahlen
ምስል Yohannes Gebereegziabher

ኢትዮጵያ ውስጥ በመጪው ግንቦት ለሚካኼደው 5ኛ አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ተጀምሯል። ምዝገባው ከተጀመረ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ12 ሚሊዮን የሚበልጡ መራጮች መመዝገባቸዉን የምርጫ ኮሚቴው አስታውቋል። እንደ ምርጫ ቦርዱ ከሆነ ፤ ድምፁን ለመስጠት 33 ሚሊዮን መራጭ እንደሚመዘገብ ይገመታል። በመጪው ምርጫ ከሚሳተፉ ወጣቶች መካከል ፤ ሱራፌል ምህረቱ አንዱ ነው። የ22 ዓመቱ ወጣት የመምረጥ መብት ሲኖረው ይህ 2ኛ ጊዜው ነው፤ እድሉን ሲጠቀም ግን ፤ የመጀመሪያው ነው።

በግል ድርጅት ውስጥ የሂሳብ አያያዥ ሰራተኛ ሆኖ የሚያገለግለው ፤ ሱራፌል በመጀመሪያው ምርጫ ያልተሳተፈው፤ መታወቂያውን ዘግይቶ በማውጣቱ እና ስለሚመርጠው ፓርቲ በቂ ግንዛቤ ስላልነበረው እንደነበር ገልፆልናል።

በ97 ዓም በተካሄደው ምርጫ ሱራፌልን በ2 ዓመት ትበልጠው የነበረቸው ስያሜ አንለይ፤ በምርጫው ተካፍላለች። የዘንድሮው የግንቦቱ ምርጫ ደግሞ 2ኛዋ ነው።መምህርት ስያሜ የትኛውን ፓርቲ እንደምትመርጥ ፤ ከምርጫው ጥቂት ወራት አስቀድሞ ብታውቅም ፤ የፓርቲው ማንነት የግል ሚስጥሯ ነው።

Addis Abeba Äthiopien Wahlen
ምስል Yohannes Gebereegziabher

ስያሜም ትሁን ሱራፌል ገና የምርጫ ካርድ ለመውሰድ አልተመዘገቡም ፤ ነገር ግን ስለምርጫው የሚደረጉ ውይይቶችን ይከታተላሉ። ሱራፌል በዘንድሮው ምርጫ ማንኛውም የመምረጥ መብት ያለው ኢትዮጵያዊ ለምርጫ ስለቀረቡት ማንኛውም ፓርቲዎች አላማ እና አቋም የመገንዘብ እድል አላቸው ብሎ ያምናል።

ሞክሬ ስላየሁት፤ እና ሌሎች ምክንያቶችም ስላሉኝ በዘንድሮው ምርጫ አልሳተፍም ያለን፤በሱፍቃድ ሙሉጌታ ነው፤ በምርጫው የማይሳተፈውየሚወክለው ፓርቲ ባለማግኘቱ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በምርጫው ፍታሃዊነት ከማያምኑ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ ዉስጥ በመጪዉ ግንቦት ወር ለሚካሄደዉ አጠቃላይ ምርጫ የሶስት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የምርጫ ዝግጅት ፤ በድምፅ ዘገባ ያገኙታል።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ