1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች ገበያ

ረቡዕ፣ ግንቦት 24 2008

በአፍሪቃ የአዲስ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ እና የመገጣጠም ሥራ ከሌሎች አሕጉራት አኳያ እጅጉን ውስን ነው። የአፍሪቃ የተሽከርካሪ ገበያ እና የመግዛት አቅም ውስንነት ዋንኞቹ ተግዳሮቶች ናቸው።

https://p.dw.com/p/1IyPT
Äthiopien Addis Ababa Bushaltestelle
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

የኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች ገበያ

ኢትዮጵያ በዓለም አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ናት። ዓለም አቀፉ ባለ ሞተር የተሽከርካሪ አምራቾች ማህበር (OCIA) ከሁለት አመት በፊት ይፋ ባደረገው ዘገባ መሰረት ሁለት ባለ ሞተር ተሽከርካሪዎች ለ1000 ኢትዮጵያውያን ግልጋሎት ይሰጣሉ። ከሁለት አመት በፊት በወጣው ዘገባ መሰረት በኢትዮጵያ ከሚገኙ 150 000 ተሽከርካሪዎች መካከል 90 000 የህዝብ ማመላለሻ ሲሆኑ 60 000 ያክሉ ደግሞ ለንግድ ሥራ የሚያገለግሉ ናቸው። ከጎርጎሮሳዊው 2005 እስከ 2014 ባሉት አመታት በዘርፉ ላይ ፈሰስ የተደረገው መዋዕለ ንዋይ በ2% እድገት አሳይቷል።

ዴሎይት ኮንሰልቲንግ በቅርቡይፋ ያደረገው መለስተኛ የዳሰሳ ጥናት በዓመት 18 000 ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ይጠቁማል። ከእነዚህ መካከል ወደ 2 000 የሚጠጉት አዲስ ሲሆኑ ከ5 000 እስከ 7 000 የሚደርሱት ደግሞ ያገለገሉ ናቸው። ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡት አዲስም ሆነ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች መካከል 65% የጃፓኑ ቶዮታ ምርቶች ሲሆኑ በአብዛኛው ከቻይና እና ዱባይ የተሸመቱ ናቸው። የቶዮታ ተሽከርካሪዎች ጠንካራ መሆናቸው እና በተመጣጣኝ ዋጋ ሊጠገኑ የሚችሉ እንዲሁም ያላቸው መሆኑ የመለዋወጫ እቃ አቅርቦት በገበያው ላይ ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖራቸው ማገዙን የዳሰሳ ጥናቱ ይጠቁማል።

Äthiopien Addis Ababa LKW
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

በኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥሙ የግል እና የመንግስት ኩባንያዎች ቢኖሩም በግብይቱ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ግን እጅጉን ውስን ነው። አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይ ዴሎይት የተሰኘው የኦዲት እና ማማከር ሥራ ኩባንያ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥራ አስኪያጅ ናቸው። አቶ ቴዎድሮስ በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ መኪኖች በገበያው ያላቸው ድርሻ ከ15% እንደማይልቅ ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ መረጃ መሰረት 31 የውጭ ኩባንያዎች ከጎርጎሮሳዊው 1998 ዓ.ም. ጀምሮ ተሽከርካሪ ለመገጣጠም ፈቃድ ወስደዋል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የቻይና ሲሆኑ ጥቂት የአውሮጳ ኩባንያዎችም ተሳትፎ አለበት። በዚሁ ተመሳሳይ ጊዜ 73 የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በተመሳሳይ ሥራ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ ወስደዋል። በዚህ መሰረት ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ተሽከርካሪ ለመገጣጠም 104 ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደዋል ማለት ነው። ይሁንና በወሰዱት ፈቃድ መሰረት ሥራ የጀመሩት እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው። አብዛኞቹ ሥራቸውን ለመጀመር ቅድመ-ዝግጅታቸውን አላጠናቀቁም።

በፈቃዳቸው ወደ ስራ ከገቡት መካከል በኢትዮጵያ ብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን ስር የሚገኘው ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንደስትሪ በዓመት 4 000 የህዝብ ማመላለሻ፤የግንባታ እና የእርሻ ሥራ መኪኖችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል። በጥረት ኢንተርናሽናል 1200፤ሊፋን ሞተርስ እና መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂኔሪንግ ደግሞ 1 000 መኪኖች በዓመት ይገጣጥማሉ። በምህጻሩ አምቼ ተብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ መኪና ማምረቻ ኩባንያ (Automotive Manufacturing Company of Ethiopia (AMCE) እና በላይ አብ ኢንተርናሽናል የተሰኙ ኩባንያዎችም በመገጣጠም ሥራው ላይ ተሰማርተዋል። አቶ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች ከውጭ ከሚገቡት ጋር ለመወዳደር በደንበኞች ዘንድ ያለውን አስተሳሰብ መቀየር አለባቸው ሲሉ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ አነስተኛ የቤት መኪኖች በመገጣጠም ለገበያ ማቅረብ ሲጀመር ተሽከርካሪዎቹ አማላይ ስያሜዎች አግኝተው በአገር ውስጥምርት ስም ተዋውቀውም ነበር። በኢትዮጵያ የተገጣጠሙ መኪኖችን የመግዛት እና የማሽከርከር ፍላጎት ጨምሮም ነበር። ይሁንና የጥገና አገልግሎት እና የመለዋወጫ አቅርቦት እጥረት በተሽከርካሪዎቹ ተቀባይነት ላይ ጥላ አጥልተዋል።

የኢትዮጵያ የእድገት እና ለውጥ እቅድ የአምራች ኢንደስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረው ድርሻ በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ከነበረበት 4% በ2020ዓ.ም. ወደ 8% የማሳደግ እቅድ አለው። ይሁንና ኢትዮጵያ የአውቶሞቲቭኢንዱስትሪ የሚመራበት ፖሊሲ የለውም። አቶ ቴዎድሮስ ዘርፉን ለማደግ ፖሊሲው ሊዘጋጅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

VW Produktion
ምስል picture-alliance/dpa

የኢትዮጵያ የተሽከርካሪ ገበያ አነስተኛ መሆን እና የሸማቾች አቅም ውስንነት በመገጣጠም ላይ ለተሰማሩት ፈተናዎች ናቸው። አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይ ኢንደስትሪው ከገንዘብ ተቋማት ጋር ሊተሳሰር እንደሚገባ ይናገራሉ።

አቶ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ የተሽከርካሪ ፍላጎት እና ገበያ ለውጭ ባለ ወረቶች ጭምር ቦታ እንዳለው ያምናሉ። የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገበያ ቢሳተፉ ለአገሪቱም ተጨማሪ ጥቅም ይኖረዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

ዴሎይት ኮንሰልተንሲ በሰራው የዳሰሳ ጥናት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የኬንያ እና የናይጄሪያን ገበያዎችም ፈትሿል። የኬንያ መንግስት ወደ አገሪቱ በህገ-ወጥ መንገድ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን ከማስቆም ጎን ለጎን በአገር ውስጥ የሚገጣጥሙ ኩባንያዎችን ለማበረታታት ጥረት ላይ ይገኛል። በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. በኬንያ የተመዘገቡ መኪኖች ቁጥር 112 536 የደረሰ ሲሆን 80% ያገለገሉ ናቸው።

ናይጄሪያ ከውጭ በሚገቡ ያገለገሉ መኪኖች ላይ ገደብ ከመጣሏ በፊት ከዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በዓመት 100 000 መኪኖችን ትሸምት ነበር። ባለፈው ዓመት ከዩናይትድ ስቴትስ የገዛቻቸው መኪኖች ቁጥር ወደ 40 000 ዝቅ ብሏል። አገሪቱ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም የጀመረችው ከጎርጎሮሳዊው 1970 ጀምሮ ነው። በአሁኑ ወቅት በናይጄሪያ መንግስት ፈቃድ የተሰጣቸው 35 ኩባንያዎች በመገጣጠም ስራው ላይተሰማርተዋል።አቶቴዎድሮስ ኬንያም ትሁን ናይጄሪያ በዚህ ዘርፍ ከኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ