1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የዕድገትና የለዉጥ ዕቅድ

እሑድ፣ ሰኔ 7 2007

ገና ሲጀምር አለቅጥ የተለጠጠ ወይም አምቢሽየስ የተባለዉ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ገቢር እንዳልሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ራሳቸዉ በየአጋጣሚዉ እያስታወቁ ነዉ።ያም ሆኖ እስካሁን የተከናወኑት ሥራዎች የደኸይቱን ሐገር ልማት ለማፋጠን ትልቅ መሠረት መጣላቸዉን ባለሥልጣናቱ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/1FgUe
ምስል DW/Y. Gebre-Egziabher

የኢትዮጵያ የዕድገትና የለዉጥ ዕቅድ

ለዛሬዉ ዉይይታችን «የኢትዮጵያ የዕድገትና የለዉጥ ዕቅድ አምስተኛ ዓመት የሚል ርዕስ ሰጥተነዋል።የኢትዮጵያ መንግሥት ከአማርኛ ይልቅ እንግሊዝኛን-ከአማርኛ በቀየጠ አጠራር «የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን»፤ በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ (GTP) ብሎ የሰየመዉን «የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ» ከነደፈ አምስተኛ ዓመቱ ተገባደደ።

የዕቅዱ የመጨረሻ ዘመን በመሆኑ ይመስላል-ሌላ GTP 2 የተባለ የአምስት ዓመት ዕቅድ መነደፉ እየተነገረ ነዉ።አዲሱ የኢትዮጵያ ምክር ቤት በመጪዉ መስከረም ሲሰየም ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል የሚል ዘገባም ደርሶናል።የዛሬ ትኩረታችን ግን አሁን ባረጀዉ ዕቅድ-አንድ ላይ ነዉ።

ገና ሲጀምር አለቅጥ የተለጠጠ ወይም አምቢሽየስ የተባለዉ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ገቢር እንዳልሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ራሳቸዉ በየአጋጣሚዉ እያስታወቁ ነዉ።ያም ሆኖ እስካሁን የተከናወኑት ሥራዎች የደኸይቱን ሐገር ልማት ለማፋጠን ትልቅ መሠረት መጣላቸዉን ባለሥልጣናቱ ይናገራሉ።

የዕቅዱ ተቺዎች ግን ይሕን አይቀበሉትም። አንዳዶች የመንግሥትን ምክንያትና መግለጫ ከማጣጣልም አልፈዉ ዕቅዱ ወትሮም ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለመደበቅ፤ ሕዝብን ለማማለል፤ የለጋሽ መንግሥታትን ድጋፍ ለማግኘት ወዘተ የተነደፈ እንጂ የኢትዮጵያን የሐብት፤የዕዉቀት እና የጉልበት አቅምን፤ የአስፈፃሚዎችን ብቃትም ያላገነዘበ ነዉ ይላሉ።

የሰፊዉን ዕቅድ ምንነት፤በየመስኩ የተከናወኑና ያልተከናወኑ ጉዳዮችን፤ ለመከናወን ወይም ላለመከናወን የሚሰጡ ምክንያቶችን በዚሕ ዝግጅት በዝርዝር ማየት አንችልም።ምሳሌ እየጠቀስን ዋና ዋና ዎቹን አንስተን ባጭሩ ለመቃኘት ነዉ የምንሞክረዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ