1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢንተርኔት አፈና በኢትዮጵያ 

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 6 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት «ሆን ብሎ እና ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ » ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችና የመረጃ አቅራቢ ድረ ገጾችን እየዘጋ ሰብዓዊ መብትን ከመደፍለቅ እንዲቆጠብ ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ።

https://p.dw.com/p/2ULvj
Logo Amnesty International

Amnesty & OONI Social media and news websites blocked by government - MP3-Stereo

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት ወዲህ የተቀሰቀሰዉን ሕዝባዊ ተቃሞና ከዚያም በታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት መንግሥት የማኅበራዊ መገናኛ አዉታሮች በማፈን ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈረመችዉን የፖለቲካና ሲቪል መብቶች ስምምነት አንቀጽ 19 ላይ የተጠቀሰዉን ሃሳብን በነጻ የመግለፅና መረጃን የመፈለግና የማሰራጨት መብት ደፍጥጣለች ሲል ወቅሷል። 
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት በተቀነባበረና ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን፣ የዜና ማሰራጫና ድረ-ገፆችን በመዝጋት የመንግሥት ወታደሮች ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች ላይ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፋ እንዳይወጡ አድርጓል፤ በዚህም የሰብዓዊ መብትን ገድቧል ሲል ዘገባ አዉጥቶአል። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍስሀ ተክሌ፤ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ዋትሳፕን ጨምሮ 16 የዜና መቀበያዎች መዘጋታቸዉን አረጋግጠናል ሲሉ ገልፀዋል።  
አቶ ፍስሃ አምነስቲ ይህን ጥናት ያካሄደዉ በኢንተርኔት ሰርቪስ አገልግሎት ላይ አላግባብ የሆነ ጣልቃ ገብነትን የሚቆጣጠረዉ ከጎርጎረሳዉያኑ 2001 ዓ,ም ጀምሮ የተቋቋመ «Open Observatory of Network Interference»  ድርጅት ጋር መሆኑን ገልፀዋል የዚህ ድርጅት ባልደረባና ተመራማሪ ማርያ ዛይ እንደገለፁት ፍተሻዉ የተካሄደዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ።    
«ድርጅታችን አንድ ድረገድ መታገድ አለመታገዱን እንዲሁም እንዴት እንደታገደ የሚመረምር ሶፍት ዊር ያመርታል። « በኢትዮጵያ ይህን ፍተሻ ለማካሄድ እኔ እራሴ አልሄድኩም። ስማቸዉን የማንጠቅሳቸዉ እዝያ ያሉ ኢትዮጵያዉያን ተመራማሪዎች ይህ ድርጅቱ ያመረተዉን ሶፍት ዌር ሃገር ዉስጥ በመጠቀም ነዉ የታገዱትን የመረጃ አዉታሮች ለማወቅ የበቁት። ተመራማሪዎቹ ከአገር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን ከሌላም ሃገርም ኢትዮጵያ የሄዱ ናቸዉ። አብዛኛዉን ፍተሻ ያደረግነዉ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ሆነን ነዉ» 
የኦኒ ድርጅት ባልደረባ ማርያ ዛይ በመቀጠል ምርምሩና ፍተሻዉ የተካሄደዉ  አሉ፤ 
«ሙከራዉ የተካሄደዉ ከጎርጎሮሳዊዉ 2016 ሰኔ ወር እስከ ጎርጎረሳዊዉ ጥቅምት 7 ድረስ ነዉ፤  ጥቂት ወራት ማለት ነዉ። በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲደነገግ ለደህንነት ስንል ሥራችንን አቋርጠን፤ ምርምራችንንም አጠናቀቅን።» 
ኢንተርኔትን ማገዱ ሕጋዊ መሠረት የሌለዉና በሀገሪቱ ለተነሳው ተቃውሞ የተወሰደ ሌላ ያልተመጣጠነ እርምጃ  ነው፤ በሕገ ወጥ መንገድ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችና የመረጃ አቅራቢ ድረ ገጾችን ማገድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነዉ፤ ሲሉ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍስሀ ተክሌ ተናግረዋል። 
የኦኒ ድርጅት ባልደረባ ማርያ ዛይ እንደ ገለፁት ድርጅታቸዉ  የድረገጽ እገዳና አፈና በርግጥ ከማን በኩል እንደተፈፀመ እና እንዴት ነዉ እንደሆነ ለማየትና ለማወቅ አልቻልንም፤ እንደኔ ከዚህ ቀደም የኔ ባልደረቦች በቱክሚኒስታን የኢንተርኔት አገልግሎችን ለመገደብ ጥቅም ላይ የዋለዉ አይነት ዘዴ ነዉ የሚል ግምት አለኝ ግን ይህ ጥርጣሪና ግምት ብቻ ነዉ።» ሲሉ ተናግረዋል። 


አዜብ ታደሰ 


ሸዋዬ ለገሠ