1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢንተርኔት ጠቀሜታ በአፍሪቃ

ረቡዕ፣ መስከረም 13 1996
https://p.dw.com/p/E0gI

በዛሬው ዘመን ኋላቀር በሆነው በአፍሪቃው አህጉር እንኳ የኮምፒውተሩ መረብ ኢንተርኔት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በሰፊው ይታመንበታል። ሌላው ቀርቶ፣ አፍሪቃ ውስጥ ለኮምፒውተሩና ለኢንተርኔቱ ሥነቴክኒክ ብዙ ወጭ መከስከስ ፋይዳ የለውም፣ በድህነት አንፃር የሚደረገውን ትግል ያዳክመዋልና በማለት የሚከራከሩት ሃያስያን እንኳ “አዲስ መገናኛ” የሚሰኘው ይኸው የኢንተርኔቱ ጥበብ አፍሪቃውያንን በኤኮኖሚ የሚረዳ እንደሚሆን አሁን በግልጽ ነው የሚናገሩት። በኢንተርኔት በኩል ከዓለምአቀፉ የመረጃ መረብ ጋር የሚያያዘው ኮምፒውተር-መሣሪያ አፍሪቃ ውስጥ የዴሞክራሲን ዕድገት ለማነቃቃትና የጾታዎችን እኩልነት ለመተግበር በሚደረገውም ጥረት ረገድ የሚረዳ እንደሚሆን በጥብቅ ነው የሚታመንበት። አዲሱ ኤሌክትሮኒክ መገናኛ የድሃውን ኅብረተሰብና የሌሎችንም የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚበጅ መሣሪያ እንደመሆኑ መጠን ለዚሁ መረብ ማስፋፊያ የሚወጣው ገንዘብ እንደ ጠቃሚና እንደምርታማ ውዒሎተንዋይ እንጂ፣ እንደብክነት የሚቆጠር አይሆንም ብዙ ጠበብት እንደሚያስገነዝቡት።

የዚሁ የአዲሱ መገናኛ ጠበብት ከቅርብ ጊዜ በፊት ሐሳብና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ባካሄዱት፣ “ጎዳና አፍሪቃ” በተሰኘው ጉባኤ ላይ እንዳስገነዘቡት፣ አፍሪቃ ውስጥ አዲስ የመረጃ ቴክኖሎጂ/ወይም ሥነቴክኒክ ለማነቃቃትና ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ረገድ የሚጓደለው፣ የፊናንሱ ምንጭ ብቻ አይደለም፤ ብዙውን ጊዜ የፖለቲካውም በጎፈቃድ ነው መሟላት የሚሳነው።

ድህነት በሚጫነው በአፍሪቃው አህጉር ለአዲሱ ሥነቴክኒክ ግብዓት ለምሳሌ አነስተኞቹ ገበሬዎች አስፈላጊውን ኮምፒውተር መሣሪያ የሚያቀርቡበት አቅም አይኖራቸውም፣ እውቀቱም ይጓደላል፣ ሌላው ቀርቶ የኮሬንቲ አቅርቦት እንኳ ላይኖራቸው ይችላል። ግን በየቦታው የሚከፈቱ የኅብረተሰብ አገልግሎት ማዕከላት በሚዘረጓቸው አርኣያ መርሐግብሮች አማካይነት እነዚያው አነስተኛ ገበሬዎች ወደዚያው እየሄዱ ለእርዳታ ከተመደቡት የኢንተርኔት ጠበብት አስፈላጊውን መረጃ ሊሰበስቡ ይችላሉ። ለምሳሌ ገበሬዎቹ ከኢንተርኔቱ ጠበብት ስለ አየር ፀባይ ሁኔታ፣ ስለ አዝርእት ዓይነት እና ስለ እፀዋት ይዘት፣ እንዲሁም ስለገበያው ሁኔታ የሚሰጣቸውን መረጃና ምክር መከታ በማድረግ የሚነሳሱበት እንቅስቃሴ ምርታማነትን ሊፈጥርላቸው፣ ገቢያቸውን ሊያጠረቃላቸው እና የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ ሊያደርግላቸው እንደሚችል ይታመንበታል። የዚሁ ሥነቴክኒክ መስፋፋት አነስተኞቹ የአፍሪቃ ገበሬዎች ከእጅ-ወደ-አፍ ብቻ ከሆነው ድክረት እየተላቀቁ፣ ምርትን እያትረፈረፈ እስከ ገበያም የሚያዳርሰውን ንግዳዊውን እርሻ እንዲያያዙት የሚያስችላቸው ይሆናል። ገበሬዎች ተራድኦ/ወይም የኅብረት ሥራ ማኅበራትን እየፈጠሩና እየተደራጁ፣ የመሬት ሐብታቸውን እያቀናጁ፣ አንድ የተወሰነ ሰብል በጋራ እያመረቱ ለአካባቢያዊ ገበያዎች የሚሸጡበት፣ ማዕከላይ ገዥዎቹም በበኩላቸው ያንኑ የእርሻ ውጤት ወደውጭው ገበያ የሚልኩበት አዲስ ግብርና ዛሬ አፍሪቃ ውስጥ ከፍተኛውን ትርጓሜ በማግኘት ላይ ይገኛል። እነዚሁ አነስተኞቹ ገበሬዎች ወደተመደቡላቸው የኢንተርኔት ማዕከላት እየሄዱ በዓለም ገበያዎች ላይ ስላለው የዋጋ ደረጃ በዚሁ የኮምፒውተር መረብ አማካይነት መረጃዎችን ከሰበሰቡ፣ ምርታቸውን ከተቀበሉት ገዥዎቻቸው ተገቢውን ዋጋ አግኝተው እንደሆን ሊገነዘቡት ይችላሉ። አፍሪቃ ውስጥ ድህነትን ለመታገል በሚደረገው ጥረት ረገድ የመረጃው ሥነቴክኒክ ያለው አስተዋኦ በጣም ከፍተኛ ነው።

እስካሁን የመንግሥታቱ ሚና ሆኖ የቆየውን የልማት መርሐግብሮች አመራር ዛሬ መንግሥትዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ናቸው የሚጎሉበት፣ ለዚሁም በዘመናዊው የመረጃ ሥነቴክኒክ ነው የሚጠቀሙት። እንዲያውም፣ በብሔራዊ የዕዳ ብዛትና በገቢ እጥረት ከሚፋጠጡት መንግሥታት ይልቅ፣ ዓለምአቀፍ ትሥሥር ያላቸውና የትብብሩ መረብ የሚያጠማምራቸው መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች ናቸው ዛሬ በልማት መርሐግቦች አነቃቂነት ረገድ የበለጠ ቅልጥፍና የሚታይባቸው። በአንዲት አዳጊ ሀገር ውስጥ ለተፈጥሮ ደኅንነት የሚንቀሳቀሱት ቡድኖች በደረጁት ሀገሮች ውስጥ ካሉ ተመሳሳይ ስብስቦች ከኢንተርኔቱ መረብ የተገኘውን መረጃ መሠረት ያደረገ ቴክኒካዊ ድጋፍ ሊያገኙ ይችላሉ። ሌላ ምሳሌ ለመስጠት ያህል፥ በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ ለሴቶች መብትና እኩልነት የሚታገሉት ቡድኖች ለሚዘረጓቸው ፕሮዤዎች ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ዓለምአቀፍ ድርጅቶች የፊናንሱን ርዳታ ለማግኘት ይበቃሉ። ለዚህ ሁሉ የኢንተርኔቱ መገናኛ ነው አማካይ የሚሆነው።

ዴሞክራሲን ለማጠናከር የሚታገሉትም ቡድኖች በኢንተርኔቱ መረብ በኩል ነው የዓለም-አቀፍ መድረኮችን በር የሚያገኙት። መንግሥታት ስለሚፈጽሙት በደልና ጭቆና፣ ፖሊሶች ስለሚወስዱት የጭካኔ ርምጃ፣ ሰብዓዊው መብት ስለሚረገጥበት ሁኔታ ዜናው፥ ዘገባው፣ ስሞታው በቅጽበት ወደ መላው ዓለም፣ ወደሚመለከታቸው ወገኖች የሚሰራጨው በኢንተርኔት አማካይነት ነው።

የመረጃን ስርጭት የሚያነቃቁት ወገኖች እንደሚሉት፣ በኢንተርኔት የሚተላለፈው ሁሉ እውነት ነው ማለት አይደለም፣ እንዲያውም ፕሮፓጋንዳው ነው የሚበዛው፤ ግን የመረጃ ምንጮችን በማነፃፀር፣ አስተማማኙን ፍሬነገር ከገለባው ወሬ ለይቶ መገንዘብ አያዳግትም።

የኅብረተሰብ ቡድኖች ከሌላው የዓለም ከፊል ሊገኝ ስለሚችለው የፊናንስ ምንጭ፣ ተማሪዎችም ወደ ውጭ ሀገር እየሄዱ ከፍተኛ እውቀት ከገበዩ በኋላ ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ በልማት አገልግሎት ሊሳተፉ ይችሉ ዘንድ፣ ይህንኑ ዓላማ ለመተግበር ስለሚያስችላቸው የትምህርት ድርጎ ሁኔታ የኢንተርኔቱ መረብ አስፈላጊውን መረጃ ያቀብርላቸዋል።

አፍሪቃ ውስጥ ይህንኑ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማጠናከር ይቻል ዘንድ፣ ብሔራዊ ቴሌኮም-ኩባንያዎች የኢንተርኔት መግቢያውን ዋጋ ማሳነስ ይኖርባቸዋል። ዛሬ አፍሪቃ ውስጥ ሁለት የመሐይምነት ዓይነቶች ናቸው መወገድ ያለባቸው፥ ይኸውም ጠቅላላው መሐይምነትና የኮምፒውተር መሐይምነት። ትግሉ ሁለቱንም ነው የሚመለከተው። አዲሱ መገናኛ ሥነቴክኒክ ትርጓሜ የሚኖረው፣ የንግግር፣ የሐሳብ ነፃነት ባሕል ሲጠናከር ብቻ ነው። መንግሥት የመረጃን ስርጭት በሚቆጣጠርበት፣ ዜናውን በሳንሱር መቀስ በሚቀጭበት፣ የሐሳብን ነፃነት በሚያምቅበት በአፍሪቃው አህጉር ኢንተርኔት የልማት መሣሪያ የሚሆንበት ጠቀሜታ አሁንም ሩቅ ሕልም ሆኖ ነው በአንዳንድ ሃያስያን የሚታየው። ሆኖም፣ አዲሱን የመረጃ ሥነቴክኒክ አፍሪቃም ውስጥ ለማስፋፋት የሚጥሩት ጠበብት ያው የአፍሪቃው አህጉር ከዘመናዊው የመረጃ ኅብረተሰብእ ጋር ለመቀላቀል ብቁእ መሆኑን ያምኑበታል። ይኸው የመረጃ ሥነቴክኒክ ዐብዮት እንደተቀሩት ዐብዮቶች ሁሉ ጊዜ ይወስድ ይሆናል፤ መከናወኑ ግን የማይቀር ነው፥ የዘመኑ ጥሪ ነውና።

ስለ መረጃው ሥነቴክኒክ በመጭው ታህሣሥ በዠኔቭ/ስዊስ በሚከፈተው የተባ መ ዓለምአቀፍ ጉባኤ ላይ መላው የአፍሪቃ ሀገሮች እንደሚሳተፉ ቃል ገብተዋል። በዚያው ጉባኤ ላይ የሚተላለፈው ውሳኔ ተፈራራሚዎቹ ሀገሮች አዲሱ መገናኛ የሚጠናከርበትን ሕጋዊ ደንብ እንዲያመቻቹ፣ ለንግግርና ለሐሳብ-ገለፃ ነፃነት ዋስትና እንዲሰጡ፣ የኢንተርኔትና የኮምፒውተር አጠቃቀም በሕዝቡ ዙሪያ የሚያብብበትን አካባቢ እንዲፈጥሩ ግዴታ ያደርጋል። ውሳኔው አሳሪ ነው፣ መተግበር አለበት።

መዘርዝሩ እንደሚያሳየው፣ በሰሐራ ደቡብ አፍሪቃ ከየሺው ነዋሪዎች ፫ቱ ብቻ ናቸው ኮምፒውተር መሣሪያ ያላቸው። ከጠቅላላው ሕዝብ ፫፻፶ ሚሊዮኑ/ወይም ከ፶ በመቶ የሚበልጠው ከፊል በቀን ከአንድ ዩኤስ-ዶላር ባነ ወጭ በሚኖርበት በዚያው በአፍሪቃው አህጉር ብዙዎቹ አፍሪቃውያን ኮምፒውተር የሚገዙበት አቅም የላቸውም። ስለዚህ አሁን የሚያዋጣው፣ አስቀድመን እንደጠቀስነው፣ ለኅብረተሰቡ የጋራ ጠቀሜታ በየቦታው የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋማት እንዲከፈቱ የሚደረግበት መርሐግብር ነው።