1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢንተርኔት ጥሪ ቊለፋ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 5 2008

በኢትዮጵያ የኢንተርኔትና የጥሪ አገልግሎቶችን በብቸኝነት የሚያቀርበው ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ዋትስአፕ፣ ዊቻት አይነት የነፃ አገልግሎቶችን ለማስከፈልና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን መሣሪያ ማግኘቱን አሳውቋል። የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ እስከተፈጸመ ድረስ በዓለም ዙሪያ በነፃ የሚገኙት የጥሪና የሰነድ ማስተላለፊያ አገልግሎቶች ባሕሪያቸው ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/1IUjn
Symbolbild Internet Spionage
ምስል picture-alliance/dpa/F. Gabbert

የኢንተርኔት ጥሪ ቁለፋ

በመረጃ እና ግንኙነት ዘርፍ ማንኛውም መልእክት ከላኪው ወደ ተቀባዩ ከመድረሱ አስቀድሞ የሚያልፍበት መንገድ አለው። መልእክቱ ካልተቆለፈ በስተቀር ከላኪ እና ከተቀባይ ውጪ መሀል መንገድ ላይ በሦስተኛ ወገን ሊበረበር ይችላል። በኢንተርኔት አገልግሎት ውስጥ የጥሪ እና የሰነድ መልእክቶች በሦስተኛ ወገን ምሥጢራቸው ሳይፈታ እንደተቆለፉ በላኪው እና በተቀባዩ ብቻ እንዲታዩ ማድረግ የሚያስችሉ በብዛት የሚታወቁት ማስተናበሪያዎችስ (apps) የትኞቹ ናቸው?

በእርግጥ አንድ መልእክት ከላኪ እና ከተቀባዩ ውጪ በሦስተኛ ወገን ተለይቶ እንዳይታወቅ ማድረጊያ የመቆለፊያ ሒደት አለ፤ በእንግሊዝኛው (encryption) ይሰኛል። ኢንክሪፕሽን ከመደበኛው የመስመር ስልክ ውጪ የኢንተርኔት የመገናኛ መግባቢያን (IP) በመጠቀም የኢንተርኔት መረብ ውስጥ የስልክ ጥሪ የማከናወን እና ሰነዶችን የመላክ ስልትን(VoIP) ይጠቀማል።

አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ የስነ-ቴክኒክ ከፍተኛ አማካሪ እና የሶፍትዌር አበልጻጊ ናቸው። ቴክ ቶክ የተሰኘውን የኢቢ ኤስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም በማዘጋጀትም ያቀርባሉ። ስለ መልእክት ቊለፋ (encryption) ሲያብራሩ፦ «በአጭሩ ኢንክሪፕሽን ማለት ከአንድ ኮምፒውተር ወደ ሌላ ኮምፒውተር የሚተላለፍን» ሊነበብ የሚችል ሰነድን እንዳይነበብ በማዘበራረቅ ትርጉም አልባ አስመስሎ ወደ ምሥጢራዊ መልእክት መቀየር ነው ብለዋል።

ኢንክሪፕሽን በጥቅሉ ምንነቱ ሳይታወቅ በሆነ መንገድ ተቆልፎ የተላከ መልእክት ተቀባዩ ጋር ብቻ ሲደርስ ግልጽ ሆኖ እንዲፈታ የማድረግ ሒደት ነው። የዲጂታሉ ዘመን የጀመረበት የመጀመሪያ ዓመታት አካባቢ ተቆልፈው ይላኩ የነበሩ መልእክቶች በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ነበሩ።

WhatsApp Ende-zu-Ende Verschlüsselung
ምስል Reuters/T. White

የኮምፒውተሮች መስፋፋት እና መርቀቅ ግን የተቆለፈው መልእክት እጅግ ውስብስብ እንዲሆን እና በቀላሉ እንዳይፈታ ለማድረግ አግዘዋል። በተለይ የኢንተርኔት የመገናኛ መግባቢያን (IP) በመጠቀም የኢንተርኔት ጥሪ(VoIP) አገልግሎት መጀመሩ መልእክቶች የበለጠ እንዲቆለፉ አስችሏል።

በዓለማችን መልእክቶችን ቆልፎ የመላክ ጥበብ የዲጂታሉ ዘመን ብቻ ያመጣው አዲስ ነገር አይደለም። ጥንትም የነበረ ነው። መልእክት ቊለፋ በሮማን ኢምፓየር ዘምን ጭምር ጥቅም ላይ የነበረ ጥበብ ስለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ይጠቅሳሉ። ባለንበት የዲጂታል ዘመንም መልእክቶችን ቆልፎ መላክ እየተጠናከረ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ «ትልቁ እና አንደኛው ነገር ምሥጢራዊነትን መጠበቅ» መሆኑን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።

በተለይ መሠረታቸውን ኢንተርኔት ላይ ባደረጉ የግንኙነት መስመሮች መሀል ዘው ብሎ በመግባት በላኪው እና ተቀባዩ መካከል ብቻ ተቆልፎ የሚከወን የመረጃ ቅብብሎሽን ፈልፍሎ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት አለ። የጥረቱ ምንጭ በእርግጥ ዘርፈ-ብዙ እና ሰፊ ነው፤ ከማጭበርበር አንስቶ የፖለቲካ ተልዕኮ እስከ ማስፈጸም ሊደርስ ይችላል።

Symbolbild Internet Verbind Störung Netz Netzwerk
ምስል picture-alliance/blickwinkel

ለመሆኑ የመልእክት ቊለፋ (encryption) እንደ ቫይበር፣ ዋትስአፕ፣ ስካይፕ መሴንጀር እና በመሳሰሉት የመልእክት መቀበያ ወይም መላኪያ ማስተናበሪያዎች የሚሠራው እንዴት ነው? አቶ ሰለሞን ይኽን በምሳሌ ሲያብራሩ፦ «ሦስት ቃላት ብልክልህ በኢንክሪፕሽን ፕሮግራም ውስጥ ሲያልፍ ያ ነገር ምናልባት አንድ አለያም ሁለት ሺህ ፊደሎችን ያካተተ ዝብርቅርቅ ያለ ነገር ነው የሚሆነው» ብለዋል። ያም በመሆኑ መልእክቱ «ሰው እጅ ላይ እንኳን ቢወድቅ ዝብርቅርቅ ያለ እና ግራ የገባው የፊደል ድርደራዎችን ነው የሚያዩት፤ ነገር ግን ያ አንተ ጋር ሲደርስ» የተዘበራረቀው መልእክት ስርአት ባለው እና ሊገባ በሚችል መልኩ እንደሚቀየር አብራርተዋል። ያን የሚያደርገውም መልእክት ላኪው እና ተቀባዩ ጋር የሚገኘው አፕሊኬሽን ነው።

ከጥንት ጀምሮ የነበረው የመልእክት ቊለፋ በዋናነት በሁለት ይከፈላል። የጋራ ቊልፍ ኖሮ ቊልፉን የሚያውቁ አካላት ብቻ ሊፈቱት የሚችሉት የቊለፋ አይነት (symmetric cryptography ወይንም shared secret encryption) አንደኛው ነው። በዚህ ዘዴ የተቆለፈውን መልእክት ለመፍታት ላኪው እና ተቀባዩ ተመሳሳይ መቆለፊያ እና መፍቻ ዘዴን ነው የሚጠቀሙት። የጋራ ቊልፋቸውንም መቀባበል ይገባቸዋል። ሆኖም ቊልፉ ከላኪ እና ተቀባይ ከወጣ የመልእክቱ ምሥጢር በሦስተኛ ወገን በቀላሉ ሊፈታ ይችላል።

ሌላኛው ዘመናዊ የቊለፋ አይነት በመልእክት ላኪው እና ተቀባዩ መካከል ብቻ የሚመሰጠር ነው። መልእክቱን የሚቀበለው ሰው፤ ላኪውም የራሳቸው የግል ቊልፍ ይኖራቸዋል፤ (Asymmetric Cryptography) መፍቻ ቊልፍ መቀባበል አያስፈልግም። ይህ ዘዴ ይፋ የሆነው እንደ ጎርጎሪዮሳስ አቆጣጠር በ1976 ነው።

Fotografie Bildung
ምስል www.apple.com

በኢንተርኔቱ ዓለም ሙሉ ዲጂታል መረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ማስተናበሪያዎች (apps) በርካታ ናቸው። የቊለፋ ስልት በመጠቀም የኢንተርኔት ጥሪን የሚያስተናግዱ ማስተናበሪያዎች ግን አይነታቸው በሁለት ይከፈላል። አንደኛው ከላኪው እና ተቀባዩ ውጪ አገልግሎት ሰጪው እንኳን መልእክቱን ማየት የማይችልበት ነው። የዚህ ተጠቃሚዎች ለአብነት ያኽል ዋትስአፕ እና የአፕል አይ ሜሴጅ ይጠቀሳሉ።

ሌሎቹ እንደነ ትዊተር፣ሀንግ አውት፣ የፌስቡክ መሴንጀር፣ ስካይፕ የመሳሰሉት ሲሆኑ፤ እነሱም እንደነዋትስአፕ የቁለፋ ስልትን ይጠቀማሉ። ሆኖም ለየት የሚያደርጋቸው የአፕሊኬሽኖቹ ባለቤቶች ያልተቆለፈው መልእክት የሰነድ ማከማቻ ቋታቸ (server) ውስጥ መገኘቱ ነው። «ስለዚህ መንግሥት በሆነ ምክንያት፤ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ተቀብሎ ያንን መልእክት ከነዚህ ኩባንያዎች ሊቀበል ቢሄድ» ያልተቆለፈው መልእክት በነሱ የሰነድ ማከማቻ ተቋም ላይ ስላለ «ማስረከብ የሚያስገድዳቸው ሁኔታ ሊኖር ይችላል» በማለት የሶፍትዌር አበልጻጊው ባለሙያ አቶ ሰለሞን አብራርተዋል።

በስነ-ቴክኒኩ ዘርፍ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ ማኅበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (SEED) ዘንድሮ ለሽልማት ካጫቸው ኢትዮጵያውያን መካከል የሚገኙበት አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ ለሰጡን ሙያዊ አስተያየት እናመሰግናለን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ