1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢንዱስትሪ ዕድገት፤ የብልጽግናና የሥልጣኔ መለያ

ረቡዕ፣ ኅዳር 6 1999

የኢንዱስትሪ ልማት የብልጽግናና የሥልጣኔ መለያ ነው። በዓለም ላይ ለዚህ የታደለው ደግሞ ሰሜናዊው የዓለም ክፍል ብቻ ሆኖ ቆይቷል። ዕድገቱ ዓለምን እንደልማትና ኋላ ቀርነቱ መጠን በአንደኛ፣ በሁለተኛ፣ በሶሥተኛና የድሃ ድሃ በመኖሩ ደግሞ በአራተኛ ደረጃ ጭምር ከፍሎ ነው የሚገኘው። ዛሬ የ 21ኛው ክፍለ-ዘመን ሃቅና ልዩነት ገጽታ ይህን የመሰለ ነው።

https://p.dw.com/p/E0dL
የቻይና የመገናኛ መዋቅር ዕድገት መለያ
የቻይና የመገናኛ መዋቅር ዕድገት መለያምስል AP

በ 18ኛው ክፍለ-ዘመን መገባደጃ ገደማ በብሪታኒያ ጀምሮ በተከታዩ ምዕተ-ዓመት አብዛኛውን ምዕራብ አውሮፓንና አሜሪካን ያዳረሰው የኢንዱስትሪ ዓብዮት በሕብረተሰብ ዕድገት ላይ ከየትኛውም ዕርምጃ ይልቅ ወሣኝነት ነበረው። በቴክኖሎጂ፣ በምጣኔ-ሐብት፣ በማሕበራዊ ኑሮና በባሕል ሥር-ነቀል ለውጥን ያስከተለ ዓቢይ እመርታ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። በጊዜው የተለያዩ ግኝቶች የዕጅ ሥራ በኢንዱስትሪ አመራረት ስልቶች እንዲተካ፣ የብረታ-ብረትና የጨርቃ-ጨርቅ አመራረት ቴክኒክ እንዲረቅ ጥርጊያ ከፍተዋል። የመንገዶች፣ የባቡር ሃዲዶችና የባሕር መተላለፊያ መስመሮች መስፋፋታቸው ለንግድ መጠናከር መበጀቱም የዚያኑ ያህል ሃቅ ነው።

የኢንዱስትሪው ዕድገት፤ የከበርቴው የኤኮኖሚ ስርዓት መስፋፋት የጥቅሙን ያህል ለዛሬይቱ ዓለማችን የኋላ ኋላ መዘዝ ማስከተሉም አይቅር እንጂ በአጠቃላይ ሂደቱ ቢቀር የበለጸገ እያልን ለምንጠራው የዓለም ክፍል የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ምንጭ ሊሆን መብቃቱ አልቀረም። የቴክኖሎጂ ተሃድሶና የዕውቀት መስፋፋት የሰውልጅ ጠፈርን እከመዳሰስ እንዲደርስ ያደረገ እስትንፋስ የሚያሳጣ ዕርምጃ እንዲታይ መንስዔ የሆነ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል በዚህ ጸጋ የታደለው አንዱ የዓለም ክፍል ዛሬ በ 21ኛው ክፍለ-ዘመን በዘመናዊ የሥልጣኔ ደረጃ ገስግሶ በሚገኝበት ጊዜ ታዳጊ እየተባለ የሚጠራው ወገን የኑሮው መሻሻል ቀርቶ መሠረታዊ ዕለታዊ ፍላጎቶቹን እንኳ ማሟላት ተስኖት መቀጠሉ ነው ክፋቱ።

ሃቁ የበለጸገው ዓለም በከፍተኛ ደረጃ ያፈራውን ዕድገትና የኑሮ ሁኔታ ለመጠበቅ መራመዱን በቀጠለበት ወቅት በታዳጊ አገሮች በተለይም በአፍሪቃ አጀንዳው ዛሬም ከኢንዱስትሪው ዓብዮት ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላም የከፋ ድህነትን በመጋተር መወሰኑ ነው። የኢንዱስትሪ ዕድገት አሁንም የነገ፤ የሩቅ ጉዳይ እንደሆነ ቀጥሏል። በበለጸገው ሰሜንና ለዚህ ባልታደለው በደቡቡ ዓለም መካከል ያለውና የነበረው የኑሮ ሁኔታ ልዩነትከመጠን በላይ እየሰፋ መሄዱን አላቋረጠም። አልላቀቅ ያለ ክፉ መዘዝ ሆኖ ነው የሚገኘው።

የኢንዱስትሪው ዓብዮት በምዕራቡ ዓለም ያስከተለው የምጣኔ-ሐብት ዕድገት በጥሬ-ሐብት ጥማት በታዳጊ አገሮች ላይ ለተከተለው የቅኝ-አገዛዝ ዘመቻ ዓቢይ መንስዔ ነበር። ይህ ደግሞ ለታዳጊው ዓለም ከጭቆና ቀንበር ላይ ከመውደቅ ባሻገር እስከዛሬ ድረስ ማለቂያ ላጣው ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና የልማት ዕጦት ክፉ ቅርስ ጥሎ ነው ያለፈው። ለዚህም ነው በ 21ኛው ክፍለ-ዘመን ሰፊው የዓለም ክፍል በ 18ኛው ክፍለ-ዘመን ደረጃ ተጎትቶ የሚገኘው። በብዙ ሚሊያርድ ለሚቆጠር የአፍሪቃ፣ የእሢያና የላቲን አሜሪካ ሕዝብ በዛሬው ዘመነ-ኤሌክትሮኒክም በምዕራቡ ዓለም መሠረታዊ የሆኑት ትምሕርትን፣ ጤና ጥበቃንና የምግብ ዋስትናን የመሳሰሉት ጉዳዮች ብርቅዬ ሆነው ነው የሚገኙት።
አንዱ ዓለም በቅንጦት በሚኖርበት ጊዜ ሌላው የዕለት ጉርስ አጥቶ፣ የዕድገት ተሥፋው መንምኖና ሰብዓዊ ክብሩ ተዋርዶ ነው የሚታየው። ለመሆኑ ከዚህ መዘዝ መውጫ መንገድ አለ ወይ? የታዳጊው ዓለም የዕድገት ዕጣ በመጀመሪያ ደረጃ በራሱ በሕብረተሰቡ የለውጥ ዕርምጃ የሚወሰን ቢሆንም በዓለምአቀፍ ደረጃ ከበለጸጉት መንግሥታት አኳያ ቅንነት መኖሩ ግድ የሚሆን ነው የሚመስለው። እርግጥ ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያሣየችውን አስደናቂና የተፋጠነ የኤኮኖሚ ልማት ካስተዋልን ታዳጊ አገሮች ማሕበራዊ ይዞታቸው ከፈቀደ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላቸውን የኑሮ ደረጃ ልዩነት እያጠበቡ በብልጽግና አቅጣጫ ለመራመድ የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም።

እርግጥ ሁኔታው እንዲለወጥ የበለጸጉት መንግሥታት ከራስ ጥቅም በመነሣት በተቀረው ዓለም ላይ የጫኑት ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ስርዓት ከሥር መሠረቱ መለወጥ ይኖርበታል። በተጨባጭ ግን ይህ ቀላል ነገር እንዳልሆነ ባለፉት ሶሥትና አራት አሠርተ-ዓመታት ጎልቶ የታየ ጉዳይ ነው። እንደ አብነት እንኳ በዓለም ንግድ ላይ ፍትሃዊ ግንኙነትን ለማስፈን ተብሎ የተያዘው የዶሃ የድርድር ዙር ማብቂያ አጥቶ መቀጠል ለመጥቀስ ይቻላል። ድህነትን ለማሸነፍ የሚነገረው-የሚዘከረው ሁሉ እምብዛም ከቃል ያለፈ አልሆነም። አዳጊው ዓለም እንዳያድግ መሰናክሎቹ ብዙዎች መሆናቸው ነው።

በሌላ በኩል ነገሩ በመርፌ ቀዳዳ የማለፍን ያህል ከባድ ቢሆንም ዛሬ በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ላይ የምትገኘው ቻይና አዳጊው ዓለም ይህን ሃቅ እንዲገነዘብ፤ ቆርጦ እንዲታገልም አርአያ እየሆነች መሄዷ አልቀረም። ሕዝባዊት ቻይናም አንዴ የቅኝ ገዢዎች ሰላባ፤ ለነጻው የገበያ ኤኮኖሚ ስርዓትም ባዕድ ነበረች። ይሁንና ባለፉት 15 ና ሃያ ዓመታት ተጨባጩን ሃቅ በማጤን በተለይ በኤኮኖሚ ፖሊሲ ረገድ ያደረገችው ለውጥና ያሣየችው ከፍተኛ ዕርምጃ ሁለተኛዋ ጃፓን እንድትሆን እያደረጋት ነው። በዚህ ዕርምጃዋ ደግሞ ሊያቆማት የሚችል አንዳች ሃይል መገኘቱ ሲበዛ ያጠራጥራል።

እርግጥ ሕዝባዊት ቻይና የነበረችበትንና ያለችበትን ሁኔታ ከሌሎቹ የአፍሪቃ፣ የእሢያና የላቲን አሜሪካ አገሮች ለማመሳሰል አይቻልም። ቻይና በሶሻሊስት ርዕዮቷ የተነሣ ዝግ ሆና የኖረችበት ጊዜ ቢኖርም በተለይም በሕዝብ ብዛቷ የተነሣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት በተቋቋመው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ም/ቤት ውስጥ ከአምሥቱ ሃያላን ቋሚ ዓባል ሃገራት አንዷ ናት። ይህ ደግሞ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖዋን ቀላል አያደርገውም። ይበልጡን ግን የዕድገቷ ማየል ዋና ምሥጢር በተፋጠነ የልማት ዕርምጃ ከበለጸጉት መንግሥታት ለመስተካከል ቁርጠኛ ሆና መነሣቷ ነው።

ቻይና ዛሬ በንግድ መጠኗ በዓለም ላይ ቀደምት ከሆኑት አምሥት ታላላቅ መንግሥታት መካከል አንዷ ለመሆን በቅታለች። የዓለምን ገበዮች ከዳር እስከዳር ባጥለቀለቀው ጨርቃ-ጨርቅና ሌላ ቀላል የኢንዱስትሪ ምርት በአብዛኛው በምዕራቡ ዓለም የኢንዱስትሪ ዓብዮት ማግሥት የምትገኝ ብትመስልም ዕርምጃዋ ከዚያ ባሻገር የዘለቀ ነው። ሕዝባዊት ቻይና በስልታዊ መንገድ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ Know How ማለት ዕውቀትን በማከማቸት ዛሬ ከምዕራቡ ዓለም ገልብጣ የማትሰራው የምርት መኪናም ሆነ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ አለ ለማለት አይቻልም። እርግጥ ያለባለቤቱ ፈቃድ የሚደረገው ግልበጣም ሆነ ኩረጃ በዓለም ንግድ ድርጅት ዘንድ ቻይናን ደጋግሞ ቢያስከስስም፤ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ባላት የንግድ ግንኙነት ብዙ ማከራከሩ ባይቀርም አገሪቱ ከታዳጊ ወደበለጸገ አገርነት ለማደግ፤ ከምዕራቡ ዓለም ሞኖፖል ለመውጣት ሌላ መንገድ አላየችም። ይህም እየሰመረላት ነው።

ቻይና ዛሬ ቀድሞ በአንድ አቅጣጫ በታዳጊ አገሮች ምርት ሲያራግፍ የቆየውን ምዕራባዊ ዓለም የተገላቢጦሽ የራሷ ገፍ ምርት ማራገፊያ ልታደርገው በቅታለች። በሌላውም የዓለም ክፍል ከአፍሪቃ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፤ ከቪየትናም እስከ ካቭካዚያ ብርቱ ተፎካካሪ መሆን ብቻ ሣይሆን ተጽዕኖዋ ሃያል እየሆነ በመሄድ ላይ ነው። የቅርብ መረጃዎች እንደጠቆሙት የቻይና የንግድ ትርፍ ወደ 23.8 ቢሊዮን ዶላር ከፍ በማለት አዲስ ወሰን ላይ ደርሷል። ዕድገቱ የተገኘውም በተለይ የውጭ ንግዱ ካለፈው ዓመት ሲነጻጸር 29.6 በመቶ በመጨመር 88.1 ቢሊዮን ዶላር በመድረሱ ነው። ቻይና በተፋጠነ ዕድገቷ መጠን ወደ አገር የምታስገባውም ምርት በ 14.7 ከመቶ ወደ 64.3 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።

ይህም ቻይና በዓለም የኢንዱስትሪ ምርት አቅርቦት ላይ ታላቅ ድርሻ እየያዘች መሄዷን የሚያመለክት ነው። በነገራችን ላይ የቻይና የኢንዱስትሪ ምርት ከመላው ዓለም ሲነጻጸር ባለፉት ዓመታት በሶሥት ዕጅ ማደጉን ቪያና ላይ ተቀማጭ የሆነው በአሕጽሮት UNIDO በመባል የሚጠራው የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት በቅርቡ አስታውቋል። በድርጅቱ መረጃ መሠረት ቻይናን ሕንድንና ደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ በተፋጠነ ልማት ላይ የሚገኙት አዳጊ አገሮች ባለፈው ዓመት በዓለም ኢንዱስትሪ ምርት ዕርምጃ ላይ ዓቢይ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

የድርጅቱ አስተዳዳሪ ካንዴህ ዩምኬላ እንዳሉት ከሁሉም በላይ የሚያስደንቀው ደግሞ ቻይና በዓለም የኢንዱስትሪ ምርት ረገድ ድርሻዋን በማበራከት የኢንዱስትሪ ሃይል ለመሆን መብቃቷ ነው። በአንጻሩ ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል የኢንዱስትሪ ውጤት፤ ለዚያውም ኢንዱስትሪ አለ ለማለት የሚያስደፍር ከሆነ ድርሻው ከአንድ በመቶ ያነሰ ነበር። በታዳጊው ዓለም ውስጥ ራሱ የዳዊትንና የጎልያድን ያህል ልዩነት መታየቱ ብዙም የሚያበረታታ አይሆንም። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቻይና ድርሻ በዓለም የኢንዲስትሪ ምርት ረገድ በ 23 ዓመታት ውስጥ ከ 2.2 በመቶ ወደ 6.9 በመቶ ሊያድግ በቅቷል። የሕንድ ድርሻ በዚሁ ጊዜ ከ 0.9 ወደ 1.2 በመቶ፤ የደቡብ አፍሪቃ ደግሞ በዚያው በነበረበት 0.5 በመቶ ደረጃ ነው የሚገኘው።

በቪየናው የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት መረጃ መሠረት የኢንዱስትሪውን ዓለም የተቀላቀሉት ደቡብ ኮሪያና ሜክሢኮ ምንም እንኳ በዘጠናኛዎቹ ዓመታት ከቀደምቶቹ አሥር አገሮች መካከል ባይመዘገቡም በኢንዱስትሪው ምርት የ 3.4 እና የ 1.1 በመቶ ድርሻ አላቸው። ሁለቱ አገሮች ዛሬ ፓሪስ ላይ ተቀማጭ የሆነው የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት የ OECD ዓባላት ናቸው። በሌላ በኩል የብራዚል የኢንዱስትሪ ምርት ድርሻ ከ 2.5 ወደ 2.1 በመቶ አቆልቁሏል። ቢሆንም ላቲን አሜሪካይቱ አገር ከካናዳ በፊት በዓለም ላይ በኤኮኖሚ ዕድገት ቀደምት ከሚባሉት አገሮች መካከል እንዳለች ናት።

የሆነው ሆኖ የቻይና የኤኮኖሚና የውጭ ንግድ ዕድገት በዓለም ገበዮች ላይ ያለው ተጽዕኖ ከሁሉም በላይ ማየሉ ከአሁኑ ጎልቶ የሚታይ ጉዳይ ነው። በቅርቡ በ OECD ተካሂዶ የነበረ ጥናት ውጤት እንደሚጠቁመው ከሆነ ቻይና በ 2010፤ ከሶሥት ዓመት ገደማ በኋላ በውጭ ንግድ በዓለም ላይ አንደኛዋ መሆኗ የሚቀር አይመስልም። በወቅቱ በዓለም የኢንዱስትሪ ምርት ላይ ታላቁን ድርሻ ይዛ የምትገኘው አሜሪካ ናት። ከዚያም ጃፓንና ጀርመን ይከተላሉ፤ ቻይና ደግሞ ለጊዜው አራተኛ ናት።

የቻይና ግስጋሤ ከዚህ ደረጃ በደረሰበት ጊዜ የአፍሪቃ የልማት አጀንዳ በአንጻሩ በድህነት ቅነሣ፣ በበጎ አስተዳደር ለውጥና በጸረ-ሙስና ትግል ደረጃ የተወሰነ ነው። ዕድገትን አንቀው የያዙት የውጭ ብቻ ሣይሆን ቤት-ሰራሽ እክሎች ሁሉ መፍትሄን ይጠይቃሉ። ከሁሉም በላይ የክፍለ-ዓለሚቱ መለያ ገጽታ ረሃብና ድህነት ሆኖ ሊቀጥል አይገባውም። ለልማት ተገቢው ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል። የጋምቢያው ፕሬዚደንት ያህያ ጃሜህ ባለፈው ወር በበለጸጉት መንግሥታት አቅጣጫ ሲናገሩ ለአራት መቶ ዓመታት ያህል የወሰዳችሁብንን ሃብት ከሩብ ወለድ ጋር ብትመልሱልን እንደ ሃብታም እንጂ እንደተመጽዋች መልሳችሁ አታገኙንም ብለው ነበር። ዕውነት አላቸው። ግን ከገንዘቡ ይልቅ ዕውቀትና ነጻነታችንን መልሳችሁ ስጡን ቢሉ ይበልጥ ግሩም በሆነ ነበር።