1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሮም ውስጥ በስደተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 18 2009

ባለፈው ቅዳሜ ማለዳ ሮም ውስጥ ለዓመታት ሲኖሩበት ከነበረው ህንፃ በኃይል እንዲወጡ የተደረጉት ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ከሚውሉበት እና ከሚያድሩበት በአካባቢው ከሚገኝ ሜዳ  በኃይል እንዲርቁ ተደረገ ። ዛሬ ማለዳ  መከላከያ ያደረጉ ፖሊስች በተኙበት ውሐ እየረጩ እና እየደበደቡ ከአካባቢው እንዳባረሯቸው ስደተኞቹ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/2inGU
Italien Polizisten gehen gegen Flüchtlinge bei einer Demo in Rom vor
ምስል picture-alliance/dpa/AP/ANSA/A. Carconi

የኢጣልያ ፖሊስ እና የስደተኞች ፍጥጫ

ስደተኞቹም ፖሊሶቹ ላይ ድንጋይ እና ጠርሙሶች መወርወራቸው ተዘግቧል።ቁጥራቸው 725 እንደሚሆን የተነገረ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን መሀል ሮም ይኖሩበት ከነበረው ህንፃ በኃይል ከተባረሩ ዛሬ አምስት ቀናት ሆኗቸዋል። ኤርትራውያን የሚያመዝኑባቸው እነዚሁ ስደተኞች በግራ ዘመም ፓለቲከኞች እገዛ ከገቡበት ህንፃ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ አሁንም መሄጃ አጥተው የሚንከራተቱ በህንጻው አቅራቢያ በሚገኝ ሜዳ ላይ የሚውሉ የሚያድሩ ጥቂት አይደሉም። ይህ ሳያንስ ፖሊስ ዛሬ ማለዳ ህንጻው አቅራቢያ በሚገኝ ሜዳ ላይ ተኝተው የነበሩ ስደተኞችን በኃይል ከአካባቢው እንዲርቁ እንዳደረጋቸው ስደተኞቹ ከህንጻው ከተባረሩ  ውሎ እና አዳራቸው ሜዳ ላይ የሆነውን አንድ ስደተና ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

ስደተኞቹም ፖሊስ ላይ ድንጋይ እና ጠርሙሶች መወርወራቸው ተዘግቧል። ፖሊስ እንደሚለው ከመካከላቸው ሁለቱን ይዟል። በዚሁ እርምጃ 13 መቁሰላቸውም ተነግሯል።

Italien Polizisten gehen gegen Flüchtlinge bei einer Demo in Rom vor
ምስል picture-alliance/dpa/AP/ANSA/A. Carconi

ፖሊስ እርምጃው አስፈላጊ ነበር ይላል። ምክንያቱም እንደ ፖሊስ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ለስደተኞቹ አዘጋጅቶላቸዋል የተባለ መቆያ ውስጥ እንገባም በማለታቸው እና በሚውሉ እና በሚያድሩበት ቦታም ቡታ ጋዝ መጠቀማቸው አደጋ አለው ብሎ በማሰቡ መሆኑን አስታውቋል። ዶቼቬለ የጠየቃቸው ስደተኛ ትናንት ለአቅመ ደካሞች ተገኝቷል ስለተባለው ስለዚሁ መኖሪያ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ከመካከላቸው የተመረጡ ሰዎች ሄደው እንደነበር ተናግረዋል።
እኚሁ ስደተኛ እንዳሉት ህንጻው ከስደተኞች ነፃ እንዲሆን ከተደረገ በኋላ አንደኛ ፎቅ ውስጥ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ሴቶች እና ህጻናትም ዛሬ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ተወስደዋል። ቃለ ምልልሱን እስካደረግንበት ከቀትር በኋላ ድረስ እነዚሁ ከ30 ይበልጣሉ ያሏቸው ሰዎች አለመመለሳቸውንም  ገልጸውልናል። 
የዛሬው የኢጣልያ ፖሊስ እርምጃ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተወግዟል። የተመ የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍን ጨምሮ ግብረሰናይ ድርጅቶች  ለስደተኞቹ መኖሪያ ለማመቻቸት የወጣው አዲስ እቅድ ብዙ ቤተሰቦችን የሚለያይ እና ህጻናትንም ከትምህርት ቤቶቻቸው የሚያፈናቅል ነው ሲሉ ተቃውመዋል። ድርጅቶቹ ስደተኞቹ ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ይኖሩበት ከነበረው ሕንጻ መባረራቸውንም ኮንነዋል።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ