1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ይጨምራል መባሉና ማስተባበያዉ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 24 2008

መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ከሚያወጣው ወጪ ባነሰ ታሪፍ አገልግሎት እንደሚሰጥ በመግለጽ፣ ወጪውን ለማካካስ 50 በመቶና ከዚያም በላይ ሊደርስ የሚችል ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል መባሉን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አስተባበለ።

https://p.dw.com/p/1Gytl
Hinkley Point Atomkraftwerk in England
ምስል Getty Images

[No title]

የተቋሙ የዉጭ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ዛሬ ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የኤክትሪክ ኮርፖሬሽን ምንም ዓይነት የታሪፍ ጭማሪ እንደማያደርግ፤ የተጠቀሰዉ ጉዳይም በጥናት ደረጃ ላይ ያለና፤ የወጣዉ ዘገባ የተሳሳተ ሲሉ አስተባብለዋል።


ባለፈዉ ሳምንት ዘ ኢኮኖሚስት አዲስ አበባ ባካሄደዉ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ፤ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት በድጎማ ሲያቀርበዉ የቆየዉ የኤሌትሪክ ኃይል ታሪፍ በጣም ዝቅተኛ እንደነበር መጥቀሳቸዉ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል አምርተው ለመንግሥት ለመሸጥ ፍላጎት ካላቸው ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስም፣ የታሪፉ ዝቅተኛነት የድርድር አቅሙን እንዳዳከመበት በማስረዳት የአገልግሎቱ ክፍያ 50 በመቶና ከዚያም በላይ ሊደርስ የሚችል ጭማሪ እንደሚደረግ መግለፃቸዉን ከሀገር ዉስጥ በጋዜጣ ተዘግቧል። ይህን ተከትሎ ፋብሪካዎች ተቃዉሞአቸዉን ማሰማታቸዉን ዘገባዉ ጠቅሷል። የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል የዉጭ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሪክተር አቶ ምስክር ነጋሽ በበኩላቸዉ ምንም ዓይነት የታሪፍ ጭማሪ እንዳልተደረገ መታወቅ አለበት ሲሉ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል።


የመንግሥታችን ዓላማ የሕዝቡን ፍትኃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ፤ ዝቅተኛ ገቢና የኤኮኖሚ አቅም ያላቸዉን ዜጎችም ከግምት አስገብቶ የሚሠራ ነዉ ያሉት አቶ ምስክር ነጋሽ በመገናኛ ብዙሃን የወጣዉ ዘገባ የተሳሳተ ነዉ ብለዋል።


በሀገሪቱ ስለሚታየዉ ከፍተኛ የኤሌትሪክ መቆራረጥና የማኅበረሰቡን ስሞታ በተመለከተ ደግሞ፤ እሳቸዉ የኢትዮጵያ የኤሌትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን እንደሚወክሉ እና የተጠቀሰዉን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ከኢትዮጵያ የኤሌትሪክ አገልግሎት ማብራሪያ እንድንጠይቅ ነግረዉናል። ሆኖም ግን የኤልትሪክ አገልግሎት ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት ለጊዜዉ ለዛሬ ግን አልተሳካም።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ