1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራ የሠብአዊ መብት ይዞታ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 6 2008

የኤርትራ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከሁለት ሳምንት በፊት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ምክር ቤት መንግሥታቸዉ ለሠብአዊ መብት እና ለሰዎች ክብር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታዉቀዉ ነበር። ሁለቱ ድርጅቶች ግን የሚንስትሩን መግለጫ «ከተጨባጩ እዉነታ ጋር የሚቃረን» ብለዉታል።

https://p.dw.com/p/1IDME
ምስል picture-alliance/dpa

[No title]

የኤርትራ መንግሥት ይፈፅመዋል ያሉትን የሠብአዊ መብት ጥሠት የተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ መብት ምክር ቤት እንዲከታተል ሁለት የመብት ተሟጓች ድርጅቶች ጠየቁ። የኤርትራ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መንግሥታቸዉ ሠብአዊ መብት እንደሚያከብር ለተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ መብት ምክር ቤት በቅርቡ አስታዉቀዉ ነበር። ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች እና የምሥራቅ አፍሪቃ እና የአፍሪቃ ቀንድ የሠብአዊ መብት ተቋም ለምክር ቤቱ እንደነገሩት ግን የኤርትራ መንግሥት አሁንም የዜጎቹን መብት እየረገጠ ነዉ።

የሁለቱ ድርጅቶች ተወካዮች ለተባበሩት መንግስታት የሠብአዊ መብት ምክር ቤት እንደነገሩት በርካታ ኤርትራዉያን አሁንም የ«ዕድሜ ልክ» ያሉትን ወታደራዊ አገልግሎት እና በመሠረታዊ መብቶቻቸዉ ላይ የሚደርሰዉን ጥሰት ሽሽት እየተሰደዱ ነዉ።«የኤርትራ መንግስት አንድም ነፃ መገናኛ ዘዴ እንዲኖር አልፈቀደም፤ በርካታ ጋዜጠኞችና አቀንቃኞችን እንዳሰረም ነዉ።» የድንበር የለሽ ዘጋቢዎች (RSF-በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ) የአፍሪቃ ክፍል ሐላፊ ክሌ ካሕን-ስሪበር አከሉበት። እንዲሕ ብለዉ።

«2001 እጎአ ጀምሮ ነፃ ጋዜጦች በሙሉ ተዘግተዉ፤ ጋዜጠኞቹ በሙሉ ታስረዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኤርትራ ዉስጥ የግልና ነፃ ፕረስ የለም። ሁሉም መገናኛ ዘዴዎች፤ ቴሌቪዥን፤ ራዲዮ እና ጋዜጦች በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ናቸዉ። ጋዜጠኞቹንም ማስታወቂያ ሚንስቴር ነዉ-የሚቆጣጠረዉ። ሥለዚሕ ነፃ አይደሉም።»

Eritrea Hauptstadt Asmara Panorama
ምስል Reuters/T. Mukoya

ኤርትራ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር የነበራት የሻከረ ግንኙነት በቅርቡ መሻሻሉን አንዳድ ዘገቦች ጠቁመዉ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባልደረቦች ቢያንስ አንድ እስር ቤት መጎብኘታቸዉም ተዘግቦ ነበር። ክሌ ካሕን ስሪበሪ እንቅስቃሴዎቹ መኖራቸዉን ያምናሉ። ይሁንና እዉነታዉን «ለመቀባባት» የተደረጉ ይሏቸዋል።

«እነዚሕ እርምጃዎች ተወስደዋል። ግን በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ለመቀባባትና ለሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ የተደረጉ ናቸዉ። በኤርትራዉያን የዕለት ከዕለት ኑሮ ላይ የሚያመጡት ለዉጥ የለም። በርካታ ቁጥር ያላቸዉ ሰዎች አሁንም እየተሰደዱ ነዉ። የጠቀስከዉ እስር ቤት፤ የሠብአዊ መብት አቀንቃኞች ወይም ጋዜጠኞች የታሠሩበት አይደለም። እስር ቤቱ መጎብኘቱ ጥሩ ነዉ። ግን ባሁኑ ወቅት ፖለቲከኞች የታሠሩበት አይደለም። ኤርትራ እራስዋን ግልፅ ለማድረግ እርምጃዎች መዉሰዷ የሚበረታታ ነዉ። ይሁንና እነዚሕ ዓላማዎች ለኤርትራ ሕዝብ በሚጠቅም መልኩ ገቢራዊ እንዲሆኑ እርምጃዎቹ ይበልጥ መጠናከር አለባቸዉ።»

የኤርትራ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከሁለት ሳምንት በፊት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ምክር ቤት መንግሥታቸዉ ለሠብአዊ መብት እና ለሰዎች ክብር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታዉቀዉ ነበር። ሁለቱ ድርጅቶች ግን የሚንስትሩን መግለጫ ከተጨባጩ እዉነታ ጋር የሚቃረን ብለዉታል።

Eritrea Hauptstadt Asmara Telefonzelle
ምስል Reuters/T. Mukoya

ዓለም አቀፉ ድርጅት የኤርትራን የሠብአዊ መብት ይዞታ የሚመረምሩት ልዩ አጥኚ ሥራቸዉን እንዲቀጥሉ ያደርግ ዘንድም ድርጅቶቹ ጠይቀዋል። የታሠሩ ጋዜጠኞች ባሁኑ ወቅት ስላሉበት ሁኔታም የኤርትራ መንግሥት መረጃ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

«ከዓመታት በፊት ብዙ ጋዜጠኞች እስር ቤት ሞተዋል የሚል መረጃ ደርሶን ነበር። በፈረንሳይ የኤርትራ አምባሳደር ግን ይሕን አስተባብለዉ ነበር። ለአምባሳደሯ በፃፍነዉ ደብዳቤ መረጃዉ ዉሸት ለመሆኑ ማረጋገጪያ እንዲሰጡን ስንጠይቃቸዉ ግን ጋዜጠኞቹ ስላሉበት ሁኔታ፤ ሥለ መኖር መሞታቸዉም ምንም ዓይነት ማስረጃ አልሰጡንም። ለአምስት ዓመታት ያክል ታስረዉ የተለቀቁ የትምሕር ማሰራጪያ ራዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኞች እንኳ ሥለ ጉዳዩ መናገር አልፈለጉም። ብዙዎቹ ካገር ወጥዋል። ሌሎቹ ደግሞ መናገር አልፈለጉም ምክንያቱም ለደሕንነታቸዉ ሥለሚፈሩ።»

የኤርትራ መንግሥት የሠብአዊ መብት ይዞታዉን እንዲያሻሽል ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አሁንም ግፊቱን ያጠናክር ዘንድ ወይዘሮ ክሌ ካሕን-ስሪቤሪ ጠይቀዋል።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ