1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርዶሀን ተቃዋሚዎች

ሐሙስ፣ መጋቢት 14 2009

የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬቼፕ ጠይብ ኤርዶሀን ተቃዋሚዎች ፣ ቱርክ ውስጥ በሚያዚያ ሊካሄድ የታቀደው ህዝበ ውሳኔ ለዴሞክራሲ አደጋ ነው ይላሉ ። ይህን ከሚሉት ውስጥ ጀርመን የሚኖሩ ቱርኮች ይገኙበታል ። እነዚህ ወገኖች ቱርኮች በህዝበ ውሳኔው ፣ የህገ መንግሥት ማሻሻያውን ተቃውመው ድምፃቸውን እንዲሰጡ በተለያዩ የጀርመን ከተሞች ዘመቻ እያካሄዱ ነው ።

https://p.dw.com/p/2Zq9D
Deutschland Demonstration in Hamburg Besuch des türkischen Außenministers
ምስል picture-alliance/dpa/A. Heimken

Erdogan-Gegner in Deutschland - MP3-Stereo

« ነፃነቷን በተግባር የምታሳይ እያንዳንዷቱርካዊት በህዝበ ውሳኔው ማሻሻያውን አልቀበልም ስትል  ድምጿን መስጠት አለባት ፤ ትላለች ወጣቷ ኑርችያን ባስ ። በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ከተማ  ኖይማርክት በተባለው የገበያ ማዕከል ባለፈው ቅዳሜ እርስዋና ሌሎች ተቃዋሚዎች ፣ቱርኮች የህገ መንግሥት ማሻሻያ መደረጉን ተቃውመው ድምጽ እንዲሰጡ ሲቀሰቅሱ ነበር ። አስተባባሪያቸው ጉኒ ካፓንም ሆኑ ሌሎቹ ተቃዋሚዎች የፍትህ እና የልማት ፓርቲ በምህፃሩ AKP የተባለው የቱርክ ገዥ ፓርቲ አባላት አይደሉም ። በህዝበ ውሳኔው ድምፅ የሚሰጡ ቱርኮችን ለማሳሰብ የተሰባሰቡ የቱርክ ዜጎች እንጂ ። ካፓን እንደሚሉት ችግሩ አብዛኛዎቹ ቱርኮች ስለ ህዝበ ውሳኔው ምንነት በቅጡ አለመረዳታቸው ነው ።
«እኔም ሆንኩ ሌሎቹን ያሰባሰበን የቱርክ እጣ ፈንታ ነው ። የህገ መንግሥት ማሻሻያው ምክር ቤት ውስጥ ያለ አንዳች ተቃውሞ እንዲያልፍ ከባድ ትግል ነው የተደረገው ። እናም በሚያዚያ 16ቱ ህዝበ ውሳኔ  የሚሳተፉት የቱርክ ዜጎች ህዝበ ውሳኔው ለምን እንደሚካሄድ አያውቁም ። ግን ማሻሻያውን ይደግፋሉ ። የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች የሚያካሂዱ ተቋማትም ጀርመን ካሉ ቱርኮች አብዛኛዎቹ ህዝበ ውሳኔው እንደሚካሄድ ከማወቅ ባለፈ ስለ ምንነቱ ያላቸው መረጃ ውስን ነው። »
ካፓን እንደሚሉት አብዛኛዎቹ ህዝበ ውሳኔው ኤሮዶሀንን ደግፎ ወይም ተቃውሞ ድምጽ መስጠት ነው ብለው ነው የሚያስቡት ። እናም ካፓን እና ሌሎች ቱርኮች ፣የቱርክ ዜጎች ሊገኙ በሚችሉበት ስፍራ ሁሉ መረጃ ይሰጣሉ። በቱርኮች ቡና ቤቶች ሳይቀር ውይይቶችን ያካሂዳሉ ። በኮሎኙ ቅስቀሳ የተሳተፈው ሌላው በሀያዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው የኮሎኝ ነዋሪ ዶጋን  የኤርዶጋን የህገ መንግስት ማሻሻያ ከሚቃወሙት አንዱ ነው ። ወጣቱ ዶጋን እንደሚለው ብዙ ጓደኞቹ የኤርዶሀን ደጋፊዎች ናቸው ። በነሱ አስተሳሰብ  የህዝበ ውሳኔው ጉዳይ ለክርክር መቅረብ የለበትም ። በህዘበ ውሳኔው ላይ ትችት ሲሰነዘር የተጠቁ ያህል ነው የሚሰማቸው ።እናም ይላል ዶጋን ጀርመን የሚገኙ የአብሮ አደጎቹን ባህርይ ሊረዳ አልቻለም ። ካፓን እንደሚሉት ህዝበ ውሳኔው ዴሞክራሲ ወይስ አምባገነንነት የሚለውን ምርጫ ነው የሚያስቀምጠው ።የነርሱ ዘመቻም ይህን ማስረዳት ነው ። በርሳቸው አስተያየት ቱርክ ውስጥ ሆኖ መቃወም ከባድ ችግሮችን ያስከትላል ።
«ማሻሻያውን  የሚቃወሙ የተለያዩ ወንጀሎች ይፈጸሙባቸዋል ። ተቃውሞአቸው ከአሸባሪነት ጋር እንዲያያዝ ነው የሚደረገገው ። ቱርክ ውስጥ ለህዝበ ውሳኔ በሚካሄደው ዘመቻም ተቃዋሚዎች ከደጋፊዎች ጋር የሚፎካከር አቅም የላቸውም ።የቱርክ መንግሥት ጠብ አጫሪ አቋም በቱርክ ብቻ ሳይሆን በጀርመንም እየታዘብን ነው ። ይህ ደግሞ በጀርመን ያለውን ማህበራዊ ነጻነትም እየጎዳ ነው ውዝግቡ አሁን በሁሉም አቅጣጫ ጽንፍ ይዟል ።»
በአሁኑ ጊዜ በብዙ የጀርመን ከተሞች ቱርኮች ማሻሻያውን ተቃውመው ድምጽ እንዲሰጡ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው ። የቱርክ ዝርያ ያላቸው ቱርጉት ዩክሴል በሄሰን ፌደራዊ ግዛት ፓርላማ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ተወካይ ናቸው ።በቅርቡ ቪስባደን በተባለው ከተማ ቱርኮች ማሻሻያውን ተቃውመው ድምጽ እንዲሰጡ ዘመቻ የሚያካሂድ ቡድን መስርተዋል ። እርሳቸው እንደሚሉት ህዝበ ውሳኔ የሚሰጥበት የቱርክ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ማሻሻያ ጀርመን የሚኖሩ ቱርኮችን በእጅጉ ከፋፍሏል ። 
« ጀርመን የሚኖሩ ማሻሻያውን የሚደግፉ እና የሚቃወሙ ቱርኮች በፍፁም ርስ በርስ አይነጋገሩም ። ተቃዋሚዎቹን የአሸባሪዎች ደጋፊ ወይም የቱርክ መንግስት አሸባሪ የሚለው ፔካካ የተባለው ቡድን አባል ተብለው ስለሚፈረጁ ብዙ ሰዎች ሀሳባቸውን ከመግለፅ ይቆጠባሉ ። ሆኖም ድምጽ ለመስጠት የወሰኑም አሉ ። »
በአሁኑ ጊዜ በሄሰን በባንድቩርተምበርግ እና ሽሌሽዊሽሆልሽታይን እና በሌሎችም ፌደራዊ ግዛቶች በሚገኙ ከተሞች ቱርኮች የህገ መንግሥት ማሻሻያውን ተቃውመው ድምጽ እንዲሰጡ የሚካሄደው  ዘመቻ ቀጥሏል ።

Bundestag T-Shirts Free Deniz Bundestag Berlin
ምስል picture alliance/dpa/M.Kappeler
Türkei Jahrestag Schlacht von Canakkale | Präsident Tayyip Erdogan
ምስል Reuters/O. Orsal

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ