1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርዶኻን የአፍሪቃ ጉብኝት

ረቡዕ፣ ጥር 17 2009

በ3 የአፍሪቃ ሃገራት ጉብኝት ለማድረግ በታንዛኒያ ጉዟቸዉን የጀመሩት የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን ለሞዛምቢክ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሚከሷቸዉ የፈቱላህ ጉለን ሃሳብ ተከታዮች እዚያ እንደሚገኙ ጠቆሙ። ኤርዶኻን ትናንት ባቀባበላቸዉ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር የማፑቶ ባለስልጣናት ጉለን የሚያራምዱትን አስተሳሰብ እንዲዋጉ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/2WOV3
Afrikareise Erdogan in Mosambik
ምስል Getty Images/AFP/A. Barbier

Erdogan in Afrika - MP3-Stereo

 የቱርኩ ፕሬዝደንት አሁን የሚያደርጉት ጉብኝት አፍሪቃን ጨምሮ በመላዉ ዓለም የተንሰራፋ ግንኙነት አለዉ የሚባለዉ የጉላን አስተሳሰብ ተከታዮች ያተኮሩባቸዉ ትምህርት ቤቶች ጉዳይ አንዳች መፍትሄ እንዲያገኝ ያለመ ነዉ።


የቱርክ ፕሬዝደንት ራሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን ትናንት ሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ ላይ ለሀገሪቱ ባለስልጣናት ያቀረቡትን ጥያቄም ሆነ ያነሱትን ሃሳብ ታንዛኒያ ላይም በግልፅ ተናግረዉታል። ቱርክ ዉስጥ በቅርቡ ለተሞከረዉ መፈንቅለ መንግሥት ዋና ተጠያቂ አድርገዉ ለሚከሷቸዉ ፈቱላህ ጉለን አስተምህሮ እና አስተሳሰብ የገበሩ በርካቶች እዚያም እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነ መረጃዉ እንዳላቸዉ ኤርዶኻን በግልፅ ተናግረዋል። እናም የታንዛኒያም ሆነ ሞዛምቢክ መሪዎች ይህን እንቅስቃሴ እንዲዋጉም ጠይቀዋል። በጉለን ንቅናቄ አማካኝነት በቱርክ የባህል ፖሊሲ ትልቅ ሚና የሚጫወትባቸዉ ትምህርት ቤቶች ያሏቸዉ ሌሎችም የአፍሪቃ ሃገራት መኖራቸዉ ይታወቃል። ዛሬ ግን ግዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት የሃይማኖት ሰዉ በቱርክ መንግሥት ጠላትነት ተፈርጀዋል። በዚህም ምክንያት ኤርዶኻን አምስት ቀናት በሚቆየዉ የሦስት የአፍሪቃ ሃገራት ጉብኝታቸዉ ከጉለን ጋር ንክኪ ያላቸዉን ትምህርት ቤቶች ለማዘጋት ግፊት እያደረጉ ነዉ። በዚህ የሚጠረጠሩት ትምህርት ቤቶች እዉቅና ያላቸዉና ከፈረንሳይ ትምህርት ቤቶች ጋር ሲወዳደሩም ክፍያቸዉ ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ ነዉ ከጊኒ ዩኒቨርሲቲ ባኖ ባሪ ይናገራሉ። በመካከኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኘዉ ኅብረተሰብም ዋነኛ አማራጮች መሆናቸዉንም ያስረዳሉ።
«የቱርክ ትምህርት ቤቶች መሆናቸዉ አይደልም ዋናዉ ነገር፤ በቅድሚያ የሚታየዉ ጥሩ ትምህርት ቤቶች መሆናቸዉ ነዉ። ያንን ነዉ የመካከለኛዉ መደብ የሚፈልገዉ።»
ጊኒ ዋና ከተማ ኮናክሪ ዉስጥ 20 የሚሆኑ የቱርክ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። ባለፉት ዓመታትም በመላዉ አፍሪቃ የቱርክ ትምህርት ቤቶች እየተስፋፉ ነዉ። እናም በመላዉ አህጉር የቱርክ ባህል ከጉለን የትምህርት ስርዓት ጋር በቅርበት በመጣመር ላይ ነዉ። በስዊትዘርላንድ ባዝል ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ጥናት ማዕከል ባልደረባ ዑፉክ ቴፔባስ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ላይ በሚወሰደዉ ርምጃ ጥንቃቄ እንደሚያሻ ነዉ የሚያሳስቡት።
«በዚህ ሂደር የቱርክ መንግሥት ጥንቃቄ እና ትዕግስት የተሞባለት ስልት መከተል ይኖርበታል። በዚያም ላይ የአፍሪቃ ወዳጆቹን ለማሳመንም ጠንካራ መረጃዎችንና አማራጭ መፍትሄዎችንም ማቅረብ አለበት። አለበለዚያ አንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ይህን እን,d ማስገደድ ቆጥረዉ የሁለትዮሽ ንግኙነቱ ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል።»
እንዲያም ሆኖ የቱርክ እና የታንዛኒያ ጉድኝት እስካሁን ችግር የገጠመዉ አይመስልም። ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ ከዳሬ ሰላም ወደ ዛምቢያ ለመዘርጋት ለታሰበዉ የባቡር ሃዲድ ኤርዶኻን ብድር እንዲሰጧቸዉ ጠይቀዋል። የባቡር መንገዱ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎን ጭምር ያገናኛል። አንድ የቱርክ ኩባንያ የግንባታ ጨረታዉን የማሸነፍ ዕድል አለዉ። ሌሎች ለጋሽ ሃገራት የዛሬ ሁለት ዓመት በታየ የሙስና ቅሌት ከታንዛኒያ ወጥተዋል። ኢስታምቡል የሚገኘዉ የሄንሪሽ በል ተቋም ባልደረባ ክርስቲያን ብራክል የሰሞኑ የኤርዶኻን የአፍሪቃ ጉብኝት ከፖለቲካዉ ይልቅ የኤኮኖሚ ዒላማ ያለዉ እንደሆነ ይናገራሉ። ቱርክ በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ ገበያዋ መንኮታኮቱን የሚተነትኑት ብራክል ከምንም በላይ ለመካከለኛዉ የንግድ ማኅበረሰቧ አስተማማን ገበያ ትፈልጋለች ነዉ የሚሉት።
«እኔ እንደማስበዉ ኤርዶኻንና መንግሥታቸዉ ከአፍሪቃ ጋር ስላላቸዉ ትስስር ከፍ በማድረግ ብዙ የሚያወሩለት ያ ብዙ አታሞ የተደለቀለት ነገር በትክክልም ዋናዉ ጉዳይ እንዲመስል ነዉ። አብዛኛዉም ተምሳሌታዊ ነዉ።»
ዘገባዎች እንደጠቆሙትም የቱርክ ፕሬዝደንት ወደ አፍሪቃ የተጓዙት አንድ መቶ የሚሆኑ የንግድ ልዑካንን አስከትለዉ ነዉ። በኤርዶኻን «AKP» ፓርቲ የምትተዳደረዉ ቱርክ የመካከለኛ ደረጃ ኤኖሚዋ ተጠናክሯል። ቻይና በስፋት በምትንቀሳቀስባት አፍሪቃ የቱርክ ተፅዕኖ እምብዛም የሚወዳደር እንዳልሆነም ባርክል ጠቁመዋል። ኤርዶኻን ከሞዛምቢክ በመቀጠል ወደ ማዳጋስካር ይጓዛሉ። 
ሸዋዬ ለገሠ/ክርስቲነ ሃርየስ

Afrikareise Erdogan in Tansania
ኤርዶሃን ከታንዛኒያዉ ፕሬዝደንት ማጉፉሊ ጋርምስል Getty Images/AFP

አዜብ ታደሰ