1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤቦላን ተኀዋሲ ያገኙት የአንዱ የሳይንስ ምሁር ስራ እና ታሪክ

ሐሙስ፣ መስከረም 15 2007

ዓለም በኤቦላ ስጋት መታመስ ሲጀምር በቀድሞዋ ዛየር በዛሬዋ ዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ ኮንጎ ተኅዋሲውን ያገኙት የቤልጅየም ተወላጁ ፕሮፌሰር ፒተር ፒዮ መታወስ ጀመሩ።ፕሮፌሰሩ በአሁኑ ወቅት የለንደን የግል ንጽህናና የምድር ወገብ አካባቢ በሽታዎች ትምህርት ቤትን በሃላፊነት ይመራሉ።

https://p.dw.com/p/1DKb4
Professor Peter Piot
ምስል AFP/Getty Images

በቅርቡ የተከሰተውን አስከፊ የኤቦላ ወረርሽኝ ለመግታት እየሰሩ እንደሆነ ይታመናል። በጌንት የህክምና ትምህርት ቤት የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳሉ የተወሰኑ የፒዮ መምህራን በተኅዋሲ እና በባክቴሪያ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች በመድሃኒቶችና ክትባቶች መበራከት ምክንያት ስለሚቀንሱ ዘርፉ የወደፊት ተስፋው የተመናመነ እንደሆነ ነግረዋቸው ነበር።

ነገር ግን ፒዮ እነዚህ ደቃቅ ተኅዋሲያን በሰው ልጅ ላይ ባላቸው ከፍተኛ ተፅዕኖ ይገረሙ ነበር።እናም የመምህራኑን ምክር ሳይሰሙ ተኅዋሲ እባክቴሪያ በሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች ላይ ትኩረታቸውን ለማድረግ ወሰኑ።

Ebolavirus
ምስል picture-alliance/dpa/F.-A.Murpy

''ከህክምና ትምህርት ቤት ከተመረኩ የተወሰኑ ዓመታት በኋላ በአንትወርፕ የምድር ወገብ አካባቢ በሽታዎች ትምህርት ቤት በስልጠና ላይ ነበርኩ።አንድ ቀን ከቀድሞዋ ዛየር ለምርመራ የተዘጋጀ የደም ናሙና መጣልን።የደሙ ናሙና የአንዲት ሟች መነኩሲት ሲሆን የሞታቸው ምክንያት ቢጫ ወባ ተብሎ የሚጠራው ህመም ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር።ከዛ የደም ናሙና ውስጥ ዛሬ ኤቦላ ተብሎ የሚጠራውን አደገኛ ተኅዋሲ አገኘን።እናም ወደ ዛየር አመራሁ። የዓለም ጤና መድረክን በድንገት የተቀላቀልኩት በዚህ መንገድ ነበር።''

ፒተር ፒዮ የኤቦላ ተኅዋሲን ካገኙ አርባ አመታት ተቆጠሩ።በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው ኤቦላ መስፋፋት በአለም ሰላምና ደህንነት ላይ የተጋረጠ አደጋ መሆኑን የተባበሩት መንግስታ ድርጅት አስታውቋል።ከዚህ ገዳይ ተኅዋሲ ጋር በሚደረገው ትንቅንቅ ከፊት ከተሰለፉት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት ፒዮ አሁን የተከሰተው መስፋፋት እንዳስደነገጣቸው ይናገራሉ።

Symbolbild Ebola Labor
ምስል picture-alliance/dpa

''ይህ የኤቦላ መስፋፋት በይፋ ከሚታወቁት ሃያ አምስተኛው ነው።መስፋፋቱ በምዕራብ አፍሪካ የመጀመሪያው ከእስካሁኖቹም ትልቁ ነው።በዚህ መስፋፋት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በቀድሞዎቹ በአንድነት ከገደሉት መብለጡ አስገርሞኛል።ምክንያቱም የቀድሞዎቹ በቦታና ጊዜ የተወሰኑ ነበሩ።ካሁን ቀደም የኤቦላ ህሙማኑን በመለየትና እንቅስቃሴያቸውን በመገደብ በትናንሽ መንደሮችና ከተሞች የተከሰቱትን ወረርሽኞች መግታት ተችሏል።''

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምክትል ዋና ጸሃፊነት በሙያው ያገለገለገሉት ፒዮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ጓድ የኤቦላ መስፋፋትን ለማስቆም ለሚደረገው ጥረት እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይቷል።

''ይህ ከፍተኛ የተኅዋሲዎች ስርጭት በደኖች አልያም በሌሊት ወፎች ውስጥ የተደበቀ ነዉ። የህዝብ ቁጥር ብዛት መጨመር የሚታይባቸዉ ፤ ደናማና ደን የተጨፈጨፋባቸዉ፤ ለዓመታት የርስ በርስ ጦርነት የሚታይባቸዉ አካባቢዎች እንዲሁም በሙስና የተጨማለቁ መንግሥታት ምን ያህል ለዚህ ተኅዋሲ መስፋፋት ተጋላጭ መሆናቸዉን አናቅም። ይህም ማለት በባለስልጣናት እና ብልሹ የጤና ተቋማት እምነት ጠፍቶአል።''

በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምህጻሩ ዩ.ኤን.ኤም...አር. ተብሎ የሚጠራ የኤቦላን የምዕራብ አፍሪቃ ስርጭት ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ-ሃይል አቋቁሟል።ፒዮ ግን ይህን ስርጭት ለመግታት የሚደረገው ጥረት ዘገምተኛ ነው በማለት በተደጋጋሚ ይተቻሉ።ስርጭቱ ከቁጥጥር ውጪ የሆነበትም አንዱ ምክንያት ይህው ዘገምተኛ ምላሽ መሆኑን ይናገራሉ።

''በላይቤሪያ ለ100,000 ሰዎች ያለው አንድ ዶክተር ብቻ ነው።ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ በቅርቡ በኢቦላ ሞተዋል።''

የኢቦላ ህመምተኞቹን በመለየትና እንቅስቃሴያቸውን በመገደብ በቅርቡ የተከሰተው ወረርሽኝ የመጨረሻው መሆን እንዳለበት ፒዮ ያምናሉ።ለዚህም ወረርሽኙ ሊዛመት በሚችልባቸው አካባቢዎች በቂ የመድሃኒት ክምችት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

ትሬቨር ግሩንዲ

ሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ