1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤቦላ ሥርጭትና ፖለቲካዊ ሥጋቱ

ዓርብ፣ መስከረም 16 2007

የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ ዶክተር ክርስቶፈር ዳይን እንደሚሉት ችግሩ ፈጥኖ ካልተገታ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት በፖለቲካዊ ቀዉስ መናወጣቸዉ የማይቀር ነዉ። የዶይቼ ቬለው ማርክ ካልድዌል ያነጋገራቸው ክርስቶፈር ዳይ ጥናት እንዳመለከተዉ፣ የኤቦላ ስርጭት በዚሑ ከቀጠለ የተለካፊዉ ቁጥር ከአንድ ወር በኋላ ከሃያ ሺ ይበልጣል።

https://p.dw.com/p/1DL7H
Kampf gegen Ebola Symbolbild
ምስል D.Faget/AFP/Getty Images

የኤቦላ ተኅዋሲ ስርጭት ከጤና እና ማሕበራዊ ቀዉስ አልፎ የፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል አንድ አጥኚ አስታጠነቀቁ።የኤቦላ ተሕዋሲን ስርጭት መዘዙን ያጠኑት የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ ዶክተር ክርስቶፈር ዳይን እንደሚሉት ችግሩ ፈጥኖ ካልተገታ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት በፖለቲካዊ ቀዉስ መናወጣቸዉ የማይቀር ነዉ።

በዓለም ጤና ድርጅት ጥናት መሰረት እስካሁን 2917 ሰዎች በኢቦላ ወረርሽኝ ሞተዋል።6263 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘዋል። ድርጅቱ በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናታዊ ጽሁፍ የኢቦላ ወረርሽኝ በዚሁ ከቀጠለ በመጪው ህዳር ወር በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በሶስት እጥፍ አድጎ ሃያ ሺ ሊደርስ እንደሚችል ይፋ አድርጓል። ወረርሽኙን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር ካልተቻለ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን የዓለም ጤና ድርጅትን ዘገባ ካጠኑት አንዱ ዶ/ር ክሪስቶፈር ዳይ ስጋት አላቸው።

''ኤቦላ በምዕራብ አፍሪካ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ካልቻልን በሳምንት በመቶዎች ብቻ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተኅዋሲው ለሞት ሲዳረጉ እንደምናይ አሁን ይፋ ባደረግንው ጥናት ላይ አመልክተናል።ይህ ጥናት ለተግባራዊ እርምጃ የቀረበ ጥሪ ነው።አስፈላጊው ተግባራዊ እርምጃ ከተወሰደ የኤቦላን ወረርሽኝ መግታት እንደምንችል እርግጠኞች ነን።ያን ማድረግ ካልቻልን ግን የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ አይቀርም።''

Ebola Medikament ZMapp angeblich erfolgreich getestet
ምስል Gallup/Getty Images

በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ከቀዳሚዎቹ የመወያያ አጀንዳዎች አንዱ የሆነውን የኤቦላ ወረርሽኝ ለመግታት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠይቅ ይታመናል።በተሕዋሲዉ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በተለያዩ ተቋማት የተለያዩ ግምቶች ይሰጣሉ።ዶ/ር ዳይ ግን የወረርሽኙን ስፋት መገመት ከአየር ትንበያ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ይናገራሉ። በእርሳቸው አባባል የኤቦላን ወረርሽኝ ከቀናትና ሳምንታት ባለፈ መገመት አስቸጋሪ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።

''በአሁኑ ወቅት አንድ በኤቦላ የተያዘ ሰው በሽታውን ወደ ሌሎች ሁለት ሰዎች ያስተላልፋል።ወረርሽኙ ፍጥነቱን በየሶስት ሳምንቱ በእጥፍ ያሳድጋል።ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍበትን ፍጥነት ወደ ሁለት ዝቅ ማድረግ ከቻልን በወረርሽኙ የሚሞቱትን እና የሚያዙትን ሰዎች ቁጥር መቀነስ እንችላለን።''

ኤቦላን ወረርሽኝ ለመግታት አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችና ክትባቶች አሁን ባይኖሩም ዶ/ር ዳይ በጥቂት ወራት ሊገኙ ይችላሉ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።በአሁኑ ወቅት ግን ጥረቱ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፍበትን መንገድ በመቆጣጠር ላይ የተመሰረተ ነው። የአለም ጤና ድርጅት ባለሙያ ቀደም ሲል ከተፈጠሩት ወረርሽኞች ልምድ ስላገኘን ይህንን እንዴት መቆጣጠር እንዳለብን እናውቃለን ባይ ናቸው።

Ebola in Liberia
ምስል picture-alliance/dpa/C. Van Nespen

''መሰረታዊው ነገር ሰዎች እንደታመሙ ቀናት ወይም ሳምንታት ሳይቆዩ ለህክምና ተቋማት ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።ይህን ማድረግ ከቻሉና ከሌሎች ሰዎች እንዲለዩ ከተደረገ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ለማድረግ ጥሩ እድል ይኖረናል።አዲስ የኤቦላ ህመምተኛ እንደተገኘ ከባድ ቢሆንም የተገናኛቸውን ሰዎች ለመለየት እንሞክራለን።የላይቤሪያዋን ሞንሮቪያ በመሳሰሉ ትልልቅ ከተሞች ከባድ ቢሆንም በሌሎች አካባቢዎች ግን ይህን ማድረግ ይቻላል።ሌላው ጠቃሚ ነገር ጥንቃቄ የተሞላበት የቀብር ስነ-ስርዓት ነው።በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ሰው ሲሞት አሳዛኝ ነው። የቀብር ስነ-ስርዓቱን የሚስፈጽሙ የአካባቢው ሰዎች ከሟች ጋር የሰውነት ፈሳሾች ጋር እንዳይነካኩ ማድረግ ብንችል ወረርሽኙን መግታት እንችላለን። ''

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ