የኤቦላ ወረርሽኝ በዩጋንዳ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 24 2004ምእራብ ዩጋንዳ ውስጥ በፍጥነት በሚዛመተው ኤቦላ በተባለው በሽታ እንደተያዙ የሚጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን መንግሥት አስታወቀ ። የበሽታውን ስርጭት የሚከታተሉ ተመራማሪዎች የኤቦላ ወረረሽኝ በአካባቢው መከሰቱን ካረጋገጡ ከጥቂት ቀናት በኋላ በበሽታው የተጠረጠሩ 6 ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸው ተዘግቧል ። የዩጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ህዝቡ ራሱን ከበሽታው እንዲጠበቅ ጥሪ አስተላልፈዋል ። ገዳዩ ኤቦላ በወረረሽኝ መልክ የገባው 600 ሺህ ያህል ነዋሪ ባላት በምዕራብ ዩጋንዳዋ ኪባሊ ቀበሌ ውስጥ ነው ። ከዚሁ ቀበሌ የአንድ ቤተሰብ 9 አባላት አንዲት ነርስና የ 4 ወር ህፃን ልጅዋ በኤቦላ ህይወታቸው አልፏል ። በዚሁ ቀበሌ በአንድ መንደር ተወስኖ የነበረው ኤቦላ
አሁን ወደ ሌሎች መንደሮችም መዛመቱን የኪባሊ ቀበሌ የጤና ቢሮ ሃላፊውን ጠቅሶ አሶስየትድ ፕሬስ ዘግቧል ። የኡጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሃላፊዎችና የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ቅዳሜ እንዳሳወቁት በሐምሌ ወር ውስጥ 14 ኡጋንዳውያን በኤቦላ ቫይረስ ህይወታቸው አልፏል ። ኤቦላ ኡጋንዳ መግባቱ በተረጋገጠ በጥቂት ቀናት ውስጥ 6 በበሽታው ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ህመምተኞች ሆስፒታል ገብተዋል ። ሰዎቹ የታመሙት በኤቦላ መሆኑ ከተረጋገጠ በበሽታው የተያዙትን ሰዎች ቁጥር ወደ 26 ከፍ ያደርገዋል ። የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ትናንት ለሃገራቸው ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝቡ አላስፈላጊ ከሆኑ የሰው ለሰው ንክኪዎች እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል ።
« ኤቦላ ሰውነትን ከበሽታው አስተላላፊ ተውሃስ የሚከላከል መሳሪያ ባጠለቁ የህክምና ባለሞያዎች ነው ክትትል ሊደረግበት የሚገባው ። ከበሽታው ራሳችሁን እንድትጠበቁ ነው ጥሪ የማቀርበው ። እጅ አትጨባበጡ ፤ ኢቦላ በሚያሳያቸው ምልክቶች የሞተን ሰው እናንተ አትቅበሩ ። ከዚያ ይልቅ ቀብሩ በጤና ባለሞያዎች እንዲከናወን አድርጉ ። ከሰዎች ጋር ከአካላዊ ግንኙነት ከማድረግ ተቆጠቡ ። ምክንያቱም ይህ በሽታ በወሲብም ሊተላለፍ ይችላልና ። »
ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በተጨማሪም ህዝቡ የኤቦላ ጥርጣሬ ካለው ወዲያውኑ ለጤና ባለሞያዎች እንዲያሳውቅ አሳስበዋል ። የኤቦላ ወረርሽኝ ዩጋንዳ መግባቱን ለማረጋገጥ መርማሪዎች ወደ አንድ ወር የሚጠጋ ጊዜ ወስደዋል ። ሰኞ እንደተሰማው ኤቦላ በኪባሊ ቀበሌ ብቻ የተወሰነ መሆኑ ያጠራጥራል ። በመዲናይቱ ካምፓላ 2 ሰዎች የበሽታው ምልክት እንደታየባቸው ዲሊ ሞኒተር የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል ። የኡጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ግን ካምፓላ ውስጥ በኤቦላ የተያዘ ሰው የለም ሲል ዘገባውን አስተባብለዋል ። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ሩክያ ናካማቴ ከኤቦላ በሽተኞች ጋር ንክኪ የነበራቸው የጤና ባለሞያዎችንም ሆነ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ ለማወቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል
« እስካሁን ከሆስፒታሉ 34 የጤና ባለሞያዎች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን አግኝተዋል ። እነዚህ ከበሽተኞች ጋር በመገኛኘት በክትትል የተገኙ ናቸው ። ከህብረተሰቡ ውስጥ የሚደረገው ክትትልም ጀምሯል ። እንደተባለው ክትትሉ ከቀጠለ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር የነበሩ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል»
ኤቦላ ከአንዱ ወደ ሌላው በፍጥነት የሚተላለፍ ፣ ህይለኛ ትኩሳት የሚለቅ ፣ የአካል ውስጥ ደም መፍሰሰ የሚያስከትልና አጣድፎም የሚገድል በሽታ ነው ። ኃይለኛ ትኩሳት ራስ ምታት የሰውነት መገጣጠሚያና የጅማት ህመም እንዲሁም የጉሮሮ ቁስልና ድካም የበሽታው ምልክቶች ናቸው ። ሲበረታም ተቅማጥ ና ትውከት እንዲሁም የሆድ ህመም ያስከትላል ።ሽፍታ ፣ የአይን መቅላት ፣ ስቅታ እንዲሁም የውጫዊና ውስጣዊ የሰውነት አካላት መድማትም በአንዳንድ በሽተኞች ላይ ይከሰታሉ ። በሽታው በቀጥታ ንክኪ ወይም በደም አለያም ከሰውነት በሚወጣ የትኛውም አይነት ፈሳሽ አማካይነት እንዲሁም በኤቦላ ቫይረሱ ከሞተ ሰው አስከሪን ጋር በሚደርግ ንክኪም ሊተላለፍ ይችላል ። የኤቦላ ወረረሽኝ በዩጋንዳ ሲከሰት እ.ጎ.አ ከ 2000 ወዲህ የአሁኑ ለ4 ተኛ ጊዜ መሆኑ ነው ። የመጀመሪያው የኤቦላ ወረርሽኝ በሰሜን ዩጋንዳ የ 224 ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል ። በ 2007 ደግሞ 42 ሰዎች በዚሁ በሽታ ሞተዋል ።
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ