1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የHIV ስጋትነት ቀጥሏል

ማክሰኞ፣ ኅዳር 20 2009

«ኤች አይ ቪ» ዛሬም የአዉሮጳ መሠረታዊ የጤና ሥጋት መሆኑን በዛሬዉ ዕለት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። የአዉሮጳ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ዛሬ እንዳስታወቀዉ ከሰባት አንዱ አዉሮጳዊ በተሐዋሲዉ መያዙን አለማወቁ በጣም አሳሳቢ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2TSzE
Institut für HIV-Forschung, Essen
ምስል Universitätsklinikum Essen/Institut für HIV-Forschung/Foto: Patrick Juszczak

የ«ኤች አይ ቪ» ስጋትነት ቀጥሏል

አዉሮጳ ዉስጥ ከሰባቱ አንዱ በHIV ተሐዋሲ መያዙን እንደማያዉቅ የአዉሮጳ ኅብረት እና የዓለም የጤና ድርጅት አመለከቱ። የኢትዮጵያ ፌደራል ስታትስቲክስ ጽህፈት ቤት ባለፈዉ ጥቅምት ወር ያወጣዉ የሕዝብ እና የጤና ቅኝት ደግሞ HIV ስለሚተላለፍበት መንገድም ሆነ መከላከያ ስልቱን በተመለከተ በገጠር የሀገሪቱ ክፍል የሚኖረዉ ወጣት በከተማ ከሚኖረዉ አነስተኛ ግንዛቤ እንዳለዉ አመላክቷል።

Institut für HIV-Forschung, Essen
ምስል Universitätsklinikum Essen/Institut für HIV-Forschung/Foto: Patrick Juszczak

በተለይ በHIV ህክምና እና ምርመራ ላይ እንደሚሠራ የተገለፀዉ በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከበሽታ መከላከል ዘርፍ የHIV መርሃ ግብር፤ በአሁኑ ወቅት በHIV ተሐዋሲ ይጠቃሉ ተብሎ የሚገመቱ ለዚህ የተጋለጡ የኅብረተ ሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ በመሥራት ላይ መሆኑን በዘርፍ ከሚሠሩት ሲስተር ሰብለ ማሞ ዘርፉ ለመረዳት ችለናል። እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲመረመሩና ህክምናዉንም እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም ገልጸዉልናል። ለተሐዋሲዉ ተጋላጭ መሆናቸዉ የሚገመተዉን የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲስተር ሰብለ ሲዘረዝሩም፤ ሴተኛ አዳሪዎች፤ የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች፤ የፋብሪካ እና የግድብ አካባቢ ሠራተኞችን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ የወጡ ዘገባዎች አዳዲስ በHIV ተሐዋሲ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን በተለይ አፍሪቃ ዉስጥ ደግሞ ከፍ እያለ መሄዱን ያመለክታሉ። ሲስተር ሰብለ ይህ ምናልባት ለተሐዋሲዉ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚካሄደዉ ምርመራ ዉጤት ሊሆን እንደሚችል ነዉ የሚገምቱት።

Symbolbild HIV Medikamente Therapie UN
ምስል picture-alliance/dpa/L.Bo Bo

እንዲያም ሆኖ ይላሉ ሲስተር ሰብለ ኢትዮጵያ ዉስጥም የተሐዋሲዉ ስርጭት በምሳሌነትም ጋምቤላ እና አዲስ አበባ አካባቢ ከፍ ብሎ መታየቱን፤ በሶማሌ፣ ሐረር እና ቤንሻንጉል ደግሞ ዝቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል 10 ቀን ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ በዘመቻ መልክ ባካሄደዉ የHIV ምርመራ 40 ሺ ሰዎች ተመርምረዉ የጤናቸዉን ሁኔታ ማወቅ መቻላቸዉን የክልሉ የHIV/AIDS ዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስፋት እና ማጠናከር ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ዉቤ ዘዉዴ ገልጸዉልናል። ይህ የተፋጠነ ያሉት የHIV ምርመራ እና የፀረ HIV ህክምና በክልሉ እስከ ሰኔ ወር ድረስ የሚዘልቅ ነዉ። እሳቸዉ እንደሚሉትም በክልሉ በርካታ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዉስጥ የፀረ HIV መድኃኒት አቅርቦቱ በተሟላ መልኩ  ለኅብረተሰቡ ቀርቧል።

ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል የHIV ተሐዋሲ ስርጭት ከፍተኛ እንደነበር በአሁኑ ወቅት ደግሞ እየቀነሰ መሄዱን የገለፁልን ደግሞ የክልሉ የጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋሽ ስሜ፤ በHIV/AIDS እና TB ምክንያት የሚከተለዉን ሞት በ50 በመቶ መቀነስ እንደተቻለ አመልክተዋል። እሳቸዉ እንደሚሉትም በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ለHIV ተሐዋሲ ተጋላጭነቱ ወደ 0,89 አካባቢ ወርዷል። እንዲያም ሆኖ በአሁኑ ጊዜ በትላልቅ ከተሞች እና ባለሃብቶች ወረታቸዉን አፍስሰዉ በሚንቀሳቀሱባቸዉ አካባቢዎች ስርጭቱ እየጨመረ መሄዱ የሚያመላክቱ ማሳያዎች መኖራቸዉንም ገልጸዋል።

HIV self testing
ራስን የመመርመሪያዉ USB ምስል Imperial College London/T. Angus

በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚገኘዉ የኅብረተሰብ ክፍል ከበሽታዉ ራሱን ለመከላከል እንዲችል የመመርመር ብቻ ሳይሆን የፀረ HIV መድኃኒቶችን እንዲያገኝ የማድረግ ጥረት መኖሩንም አመልክተዋል። በክልሉ ዉስጥም እስካሁን እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች የፀረ HIV መድኃኒት አገልግሎት ተጠቃሚዎች መሆናቸዉን፤ ህክምናዉን በሰፊዉ ለማዳረስም በርከት ያሉ ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ መደረጉንም ገልጸዋል። የመቅድም ኢትዮጵያ ፕሬዝደንት አቶ መንግሥቱ ዘመነ በበኩላቸዉ በአሁኑ ወቅት መዘናጋት መኖሩን ሁሉም የተገነዘበዉ እንደሚመስል ይናገራሉ።

ሙሉዉን መሰናዶ ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ