1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤኮኖሚ ዕድገት እስከምን?

ረቡዕ፣ ግንቦት 22 2004

የአንድ ሕብረተሰብ ዕርምጃና የሚገኝበት የኑሮ ሁኔታ የሚለካው በተለይም በኤኮኖሚ ዕድገት በደረሰበት ደረጃ ነው። እንደየደረጃው ድሃ፣ ራመድ ያል ወይም የበለጸገ ሆኖ ይመደባል። ጀርመንን በመሳሰሉት በበለጸጉት ምዕራባውያን ሃገራት የሕዝቡ ከፍተኛ

https://p.dw.com/p/15463
ምስል AP

የአንድ ሕብረተሰብ ዕርምጃና የሚገኝበት የኑሮ ሁኔታ የሚለካው በተለይም በኤኮኖሚ ዕድገት በደረሰበት ደረጃ ነው። እንደየደረጃው ድሃ፣ ራመድ ያል ወይም የበለጸገ ሆኖ ይመደባል። ጀርመንን በመሳሰሉት በበለጸጉት ምዕራባውያን ሃገራት የሕዝቡ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃና የዚያኑ ያህል ትልቅ የሆነው የፍጆት ፍላጎቱ ያልተቋረጠ ዕድገትን የሚጠይቅ ሆኖ ነው የቆየው። እናም በዚህ በበለጸገው የዓለም ክፍል የኤኮኖሚ ዕድገት ከልማትና ከብልጽግና ጋር በአንድ ላይ የሚታይ ነው።

ግን በዓለም ላይ ውሱን እየሆነ መሄድ ከያዘው የጥሬ ተፈጥሮ ሃብት ሁኔታ አንጻር ለመሆኑ ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት ጉዞ ተገቢና የሚቻልስ ነገር ነውይ? ይህ ጥያቄ በፊታችን ወር «ሪዮ-ፕላስ 20» በሚል መርሆ በሚካሄድ የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ ዓቢይ ትኩረት የሚሰጠው ነው። የበለጸገውን ዓለም ገጽታ ዛሬ ለተመለከተ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ከፍተኛነት አጉልቶ የሚያሳየው በተለይም የፍጆት ብቃቱና አቅሙ ነው።

ለምሳሌ ያህል ግጥም ብለው በምርት የተሞሉ የገበያ አዳራሾች፣ አዳዲስ ለገበያ የቀርቡ መድሃኒቶችም ሆኑ የቱሪዝም ቁጥር መጨመር ኤኮኖሚው ቀደም ካለው ዓመት የበለጠ የማደጉ ምልክቶች ናቸው። ይህ ሁሉ የአንድ አገር አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ከፍተኛነት መለያ ሲሆን በዓመት ውስጥ የተመረተውንና የተሰጠውን አገልግሎት ሁለንተናዊ መጠን ያንጸባርቃል። ቀደም ካለው ዓመት የበለጠ ተመርቶና ተሽጦ ከሆነ እንግዲህ አጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት አድጓል ማለት ነው። ይህም ነው የኤኮኖሚ ዕደገት ተብሎ የሚጠራው።

ስለዚህም ይሄው አጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት በአብዛኞቹ ሃገራት የብልጽግናና የልማት መጠን መለኪያ ሆኖ መታየቱ አልቀረም። ግን በዚህ ስሌት ውስጥ ለምሳሌ ጥሬ ሃብትን በማውጣት ወይም በምርት ተግባርና በትራንስፖርት፤ የማጓጓዝ ሂደት የሚከተለው የአካባቢ ተፈጥሮ መበከል ግምት አይሰጠውም። የምግብ፥ የጦር መሣሪያ ምርትና ከኤኮኖሚ ዕድገት ጋር ትስስር ሊኖራቸው የሚችሉ ማሕበራዊ ተጽዕኖዎችም እንዲሁ ከቁጥር ውስጥ አይገቡም። ታዲያ እነዚህ የቀድሞው የኤኩዋዶር የኤነርጂ ሚኒስትር አልቤርቶ አኮስታ እንደሚያስረዱት የእስካሁኑን የዕድገት ሞዴል ወይም ዘይቤ ለትችት የሚያጋልጡ ናቸው።

«የኤኮኖሚ ዕድገት በቀጥታ ልማት ማለት አይደለም። እያንዳንዱ አይነት ዕድገት የራሱ ማሕበራዊና የተፈጥሮ ይዞታ መሠረት አለው። ይህ ደግሞ ጥሩ ዓይነትም መጥፎም የዕድገት ዓይነት አለ ማለት ነው»

Bildergalerie Debatte Nachhaltigkeit Rio
ምስል AP

አልቤርቶ አኮስታ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ለተለመደው ብልጽግና ሲሉ የቀጣይ ዕድገትን ፈለግ በመከተል መራመዱን እንደሚመርጤጡ ያምናሉ። በኤኩዋዶሩ ተወላጅ አመለካከት የመንግሥታቱ አስተሳሰብ የራሳቸውን ሕዝብ ዕውነተኛ ፍላጎት የሚከተል ካለመሆኑም በላይ በታዳጊ አገሮች ትከሻ የሚራመድ ነው። ስለዚህም መፍትሄው የዕድገትን ፍጥነት ማለዘብ ነው ይላሉ።

ይሁንና የፍጆት ሕብረተስብን ደስታ ለማረጋገጥ ቢያድግ፤ ቢጨምር አልበቃ በሎ ስለሚታየው ፍላጎት መጽሐፍ ያሳተሙት ደራሲ ፔትራ ፒንስለር እንደሚሉት ዝቅ ያለ የኤኮኖሚ ዕድገት በበለጸገው ዓለም የምጣኔ-ሐብት ዘርፍና በመንግሥታቱ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥም እስካሁን ሊነሣ የማይፈለግ ጥያቄ ነው።

«የቆየውን ልምድ የሚከተሉ የኤኮኖሚ ጠበብት ዕድገት ማለቂያ፤ ማብቂያ የሌለው ነው የሚል አስተሳሰብ አላቸው። እንደነርሱ ያድጋል፣ ከፍ እያለም ይቀጥላል። በአንጻሩ በተፈጥሮ ይዞታ ላይ በሰፊው የሚያተኩሩ ሌሎች የኤኮኖሚ አዋቂዎች የሚያስረግጡት ግን ኤኮኖሚና የኤኮኖዊው ሣይንስ የዓለማችን አንድ አካል መሆናቸውን ነው። ዓለም ደግሞ ክብ እንጂ ጠፍጣፋ አይደለችም። እናም እንደ ምድራችን ውሱን በሆነች ቦታ ላይ አንድም ነገር በዘላቂነት ማደግ አይችልም»

የኤኮኖሚ ዕድገት የአገልግሎት ሰጨውን ዘርፍ በማስፋፋት ሊደረስበትም የሚችል ነገር ነው። ሆኖም ግን ፔትራ ፒንስለር እንደሚያሳስቡት ችግር የሚፈጥረው በዚህ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ ለማጋበስ የሚጥሩ የፊናንሱ ንግድ ተጠሪዎች መኖራቸው ነው። ደራሲዋ የሕብረተሰብ እርካታን ወይም ዕድልን የተመለከተ ምርምርን መሠረት በማድረግ ብልጽግናን ከቁቁሳዊ ሃብት ጋር ማዛመዱ እንዲቀር ያሳስባሉ።

Symbolbild Wirtschaft Export Wachstum Globalisierung
ምስል Fotolia

ምርምሩ በጣም ድሃ በሚባሉ ሃገራት በጥሩ ስሜትና በኤኮኖሚ ዕድገት መካከል ግንኑነት እንዳለ ነው። በሌላ በኩል ከተወሰነ የዕድገት ደረጃ በኋላ ጥሩው ስሜት ያለገደብ እየጨመረ ሊሄድ እንደማይችልም ያመለክታል። ለምሳሌ የሶሥት አውቶሞቢሎች ባለቤት የሆነ ስው አንድ ተሽከርካሪ ብቻ ካለው ሶሥት እጥፍ ደስተኛ ሊሆን አይችልም። ለማንኛውም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት እስካሁን በደረሱበት ረክተው ዕድገቱን ለማለዘብ ዝግጁ መሆናቸው ብዙ የሚያጠያይቅ ነው።

ይህን የሚሉት የተፈጥሮ ሃብት ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት ጉንተር ሽሚት ግሪክ ውስጥ በወቅቱ የዕድገት እጦት ብልጽግናንና የሕዝብን የእርካታ ስሜት እጅጉን ወደ ኋላ እየመለሰ እንደሆን እንደ ምሳሌ ያቀርባሉ። የዓለም ባንኩ ባለሙያ በቅርቡ በጀርመን የዓለም የረሃብ ዕርዳታ ድርጅት ስብሰባ ላይ በሰነዘሩት አስተያየት የኤኮኖሚ ዕድገት ወደፊትም የዓለም ኤኮኖሚ መንኮራኩር ሆኖ ይቀጥላል ነበር ያሉት።

«የሆነው ይሁን ዕድገት ወደፊትም የማይቀር ነገር ነው። በጥቂት ዓመታት ውስጥ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ዘጠኝ ሚሊያርድ ይደርሳል። ከዚሁ ሌላ የሕዝብ ገቢ በመላው የዓለም ሃገራት፤ በተለይም በሕንድና በቻይና የሚጨምር ነው የሚሆነው። እነዚህ ሕዝቦች ደግሞ ከፍ የሚል የምግብም ሆነ የሌሎች ምርቶች ፍላጎት ይኖራቸዋል። ታዲያ ማነው፤ ተዉ!አያስፈልጋችሁም ሊል የሚችለው!»

የሰውልጅ በመሠረቱ የፈጠራ ችሎታ ያለው ነው። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሲያዳብርና በባንክ ብድርነት መልክ ለምርምርና ለልማት ተግባር የሚፈስ ገንዘብ ሲቆጥብ ኖሯል። ይህም ለዕድገት አስተዋጽኦ ያደረገና የሚያደርግም ነገር ነው። ግን አሁን ዕድገትን እንዴት ነው ገደብ አድርጎ መያዝ የሚቻለው? የዓለም ኤኮኖሚ ወሰን እንዲኖረው ጥያቄ የሚሰነዘረው በተለይ ከታዳጊው ዓለም ነው። በሪዮው ጉባዔ ላይ «አረነጓዴ ኤኮኖሚ» የሚል ስያሜ የተሰጠው ለማሕበራዊና ለተፈጥሮ ጥበቃ የሚበጅ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ትልቁ የአጀንዳ ርዕስ እንደሚሆን ይጠበቃል።

Green Economy
ምስል Auswärtiges Amt/ Jürgen Gebhardt

ሪዮን ካነሣን የተባበሩት መንግሥታት ዓባል ሃገራት የተፈጥሮ ጥበቃን ያከበረ የኤኮኖሚ ዕድገትን ለማራመድ እንደገና ለመነጋገር በዚያው የሚሰበሰቡት ከምድራችን ዓቢይ ጉባዔ ከሃያ ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። አረንጓዴ ኤኮኖሚ የሚለው መፈክርም አሁን በሪዮ-ፕላስ 20 ጉባዔ ዋዜማ በየስብሰባው ተደጋግሞ መሰማት ይዟል። አረንጓዴ ኤኮኖሚ ሲባል ታዲያ የተለያየ ግንዛቤ መኖሩም አልቀረም።

ይሄው የቋንቋ ግንዛቤ ልዩነት ደግሞ በጉባዔው ላይ ዋና የጭቅጭቅ ነጥብ እንዳይሆን በጣሙን ያሰጋል። አረንጓዴ ኤኮኖሚን ለማራመድ የበለጸጉት መንግሥታት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙትና የታዳጊዎቹ ሃገራት ፈንታ ምንድነው፤ ሰሜኑ ዓለም ዕድገቱን ገትቶ ደቡቡ ዓለም በዕድገቱ ይቀጥል ሊባል ይቻልስ ይሆን? ጉዞው ቀላል የሚሆን አይመስልም።

በመጀመሪያ ዕድገት ኪዚያም የተፈጥሮ ጥበቃ የሚለው ያልተጻፈ ሕግ ከሪዮው የተባበሩት መንግሥታት የምድራችን ጉባዔ በኋላ የአካባቢን ጥበቃ ጉዳይ መውጫ ከማይገኝለት ጉራንጉር ውስጥ ጥሏል። ይህን የሚሉት ለተባበሩት መንግሥታት የተፈጥሮ ጥበቃ ዕቅድ በተፈጥሮ ጸጋ የምጣኔ-ሐብት ባለሙያነት የሚያገለግሉት ፕሮፌሰር ኤርንስት-ኡልሪሽ-ፎን ቫይትሴከር ናቸው።

«ንግድ ቅዱሱ ነገር ነው። የተፈጥሮ ጥበቃ ግን ከካበትን በኋላ የምናተኩርበት ሆኖ ተወስዷል። ሁኔታው በወቅቱ ይሄን የመሰለ ነው»

ታዲያ ይህ የበለጸገው ዓለም ፍልስፍና ቫይትሴከር እንደሚያመለክቱት በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ በሚገኙት ሃገራትም እየተወሰደ መሄዱ አልቀረም። በመሠረቱ የኤኮኖሚ ስኬትና የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ እርስበርሳቸው የሚቃረኑ ነገሮች አይደሉም። አረንጓዴው ኤኮኖሚ እንዲያውም በተለይ በተፋጠነ ዕድገት ላይ በሚገኙት ሃገራት የወደፊቱ የሥራ መስክ ምንጭ እንደሚሆን ሰፊ ዕምነት አለ።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ