1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤውሮ-እሢያ ጉባዔና የዓለም ኤኮኖሚ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 19 2001

የአውሮፓ ሕብረትና የእሢያ መንግሥታት በአህጽሮት የአሰም የመሪዎች ጉባዔ ባለፈው ሣምንት ማብቂያ ላይ በቤይጂንግ ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/FjoI
የቤይጂንግ ጉባዔ
የቤይጂንግ ጉባዔምስል AP

የመንግሥታቱ መሪዎች በጉባዔው ፍጻሜ ቀውሱን በጋራ ለመታገል ተስማምተዋል። በፊታችን ሕዳር 6 ቀን ዋሺንግተን ላይ ሊካሄድ በታቀደው የዓለም መንግሥታት የፊናንስ ጉባዔ ላይ አንድ ወጥ ሃሣብ ይዘው እንደሚቀርቡም ነው የሚጠበቀው። በሌላ በኩል የፊናንሱ ገበያ ሁኔታ ውዥቀት የተጣባው ሆኖ እንደቀጠለ ሲሆን የለየለት የኤኮኖሚ ቀውስ ዓለምን እንዳያዳርስ የተፈጠረው ስጋትም ገና አልተወገደም። የአሰም ጽንሰ-ሃሣብ፤ እንዲያም ሲል መጪው የዋሺንግተን ጉባዔ በመፍትሄ ፍለጋው ረገድ ጭብጥ ዕርምጃ ያሣይ ይሆን?

የዘንድሮው ሰባተኛ የአውሮፓ ሕብረትና የእሢያ መሪዎች ጉባዔ የአሰም ስብሰባ የተካሄደው “ራዕይና ተግባር” በሚል መርሆ ነበር። የአሰም መድረክ እስካሁን ሁለት ጊዜ ሲስፋፋ በወቅቱ ቻይናን፣ ሕንድን፣ ጃፓንንና ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ 43 ሃገራት ይሳተፉበታል። ዓባል ሃገራቱ ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ የሚበልጠውን የሚጠቀልሉ ሲሆን በጋራ 60 ከመቶውን የዓለም ንግድ፤ እንዲሁም ከብሄራዊው አጠቃላይ ምርት ግማሹን ድርሻ የሚይዙ ናቸው። ይህም በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ወሣኝ፤ ወይም ቢቀር በቀላሉ የማይገመት ተጽዕኖ እንዳላቸው የሚያመለክት ነው። የወቅቱን ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ በመታገሉ ረገድም እጅግ ጠቃሚ ሚና ይኖራቸዋል።
ያለፈው ሣምንት የአሰም መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ ይበልጡን ያተኮረውም በዚሁ የፊናንስ ችግር ላይ ነበር። መንግሥታቱ ቀውሱን በጋራ ለመታገል ከመነሣት ባሻገር ዓለምአቀፉን የምንዛሪና የፊናንስ ስርዓት ፍቱን አድርጎ ለመጠገንም ተስማምተዋል። እንደ ኤውሮ-እሢያው ጉባዔ ቢሆን የፊናንሱ ቀውስ ብዙ ሣይቆይ በቅርብ ሊወገድ የሚችል ነው። የአውሮፓ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ የቤይጂንጉ ጉባዔ እንዳበቃ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ስብሰባው ለዚሁ የሚያበቃ ተሥፋ ሰጭ አንድነት ታይቶበታል።

“አውሮፓና እሢያ ዓለምአቀፍ ቀውስ በሰፈነበት በዚህ ወቅት ተገቢውን አንድነት አሣይተዋል። በእርግጥም ጊዜው የተባበረ ዓለምአቀፍ ተግባርን የሚጠይቅ ነው። ቀደም ሲል እንዳልኩት ምርጫችንም አብሮ መቅዘፍ ወይም አብሮ መስጠም ብቻ ነው የሚሆነው። እናም በዚህ በቤይጂንግ ጉባዔ የፊናንሱን ቀውስ ለመታገል ያደረግነው ጥረት አብሮ ለመሥራት ያለንን ብርቱ ፍላጎት የሚያመለክት ነው። ይህ ደግሞ በጣም አስደስቶኛል”

ከዚህ ከኤውሮ-እሢያው ጥረት በኋላ ችግሩን ለመፍታት ታላቅ ተሥፋ የተጣለበት ሰብሰባ በፊታችን ሕዳር ወር የመጀመሪያ አጋማሽ ዋሺንግተን ላይ የሚካሄደው ሃያ ቀደምት በኤኮኖሚ የተራመዱ ሃገራት የሚሳተፉበት የዓለም የፊናንስ ጉባዔ ነው። የወቅቱ የአውሮፓ ሕብረት ርዕስ የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ኒኮላይ ሣርፖዚይ እንዳሉት የዋሺንግተኑ ጉባዔ ጭብጥ ውሣኔ የሚወሰድበት እንጂ የመንግሥታት መሪዎች እንዲያው ተወያይተው የሚበተኑበት መሆን የለበትም። የቻይናም ሃሣብ’ ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ እንዳስረዱት ይሄው ነው።

“በወቅቱ ቀውስ ላይ የቻይና ዓለምአቀፍ አስተዋጽኦ የተረጋጋ የኤኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ ነው ብለን እናስባለን። በዋሺንግተኑ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ጉባዔ ላይ እንሳተፋለን። የትብብር አቁዋምና ተጨባጩን ሁኔታ ያገናዘበ አመለካከትም ይዘን ነው የምንቀርበው። በአጠቃላይ ጉባዔው የተሣካ እንዲሆን ከሌሎቹ ሃገራት ጋር በመፍትሄ ሃሣቦች እንመክራለን”

ዌን ጂያባዎ የሚያምኑት መፍትሄ የሚገኘው እርግጥ ትክክለኛው ሚዛን ሲኖር ብቻ እንደሆነ ነው።

“ኤኮኖሚን ወደፊት ለማራመድ የፊናንስ ተሃድሶ የግድ ያስፈልጋል። የፊናንስ ዋስትናን ለማረጋገጥ የበለጠ የፊናንስ ቁጥጥር መኖሩም ግድ ነው። የኤኮኖሚና የፊናንስ ግንኙነትን በአግባብ ልንይዝ ይገባናል። ኤኮኖሚው እንዲያድግ ደግሞ የፊናንሱ ሂደት ጤናማ ሆኖ መራመዱ አስፈላጊ ነው። አንዱ ሌላውን የሚያሟላ እንጂ የሚጎዳ መሆን የለበትም። በቁጠባና በፍጆት መካከል ያለው ግንኙነትም እንዲሁ በአግባብ መያዝ ያለበት ጉዳይ ነው። ይህ ሚዛን ከተጠበቀ የኤኮኖሚ ዕርጋታን ማስፈኑ የሚገድ አይሆንም”

ጥያቄው ይህ እንዴት ዕውን ይሆናል ነው። በአሰም ጉባዔ ላይ እንደተነሣው ከሆነ በዓለም የምንዛሪ ተቁዋም አማካይነት በፊናንስ ገበዮች ላይ ቁጥጥርን ማጠናከሩና ግልጽነት እንዲሰፍን ማድረጉ አማራጭ የለውም። በሌላ በኩል አዲስ ዓለምአቀፍ የፊናንስ ስርዓት ማስፈን መቻሉ ግን ገና ያጠራጥራል። በፊታችን ሕዳር 6 ቀንና ከዚያ በኋላ በሚከተሉት የዓለም የፊናንስ ጉባዔዎች ግቡ ይህ ካልሆነ ቀወሱን ለማሸነፍም ሆነ የተፈራውን የኤኮኖሚ ማቆልቆል ለመግታት መቻሉ ዘበት ነው።

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ገበዮች ለሣምንታት በውዥቀት እንደቀጠሉ ቢሆንም የኤኮኖሚ ቀውስ ሥር እየሰደደ መሆኑን በይፋ ለመቀበል የደፈረ ብዙም የለም። ይሁንና የምዕራቡ ዓለም ቀውስ ተጽዕኖ ገደብ ሳይለይ ቀስ በቀስ ሌሎች አካባቢዎችን ፈተኝ ከሆነ ሁኔታ ላይ እየጣለ መሆኑ አልቀረም። ለምሳሌ የምሥራቅና ማዕከላዊ አውሮፓ ሃገራት ችግሩ ይበልጥ እየተሰማቸው በመሄድ ላይ ነው። በቡልጋሪያና በባልቲክ አገሮች የኤኮኖሚው ቀውስ በር እያንኳኳ ሲሆን ኡክራኒያን ወይም ሰርቢያን የመሳሰሉት ደግሞ የኤኮኖሚ ስርዓት መዋቅራቸውን መቀየር ግድ ሣይሆንባቸው የሚቀር አይመስልም።
ለወትሮው በቁጠባና በማለዘቢያ ፖሊሲው በምሥራቅ አውሮፓ ብዙም የማይወደደው ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም ሰሞኑን በነዚህ አገሮች ተፈላጊው ሆኗል። የዕርዳታ ያለህ እየተባለ ነው። የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ብርቱ ችግር ላይ ናቸው። ተቁዋሙም ለኡክራኒያ 13 ሚሊያርድ፤ ለሁንጋሪያ ደግሞ 10 ሚሊያርድ ኤውሮ አስቸኳይ ዕርዳታ መድቧል። ለነገሩ በሽግግር ላይ የሚገኙት የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ባለፉት ዓመታት ጠን’ካራ ዕድገት ሲያደርጉ ነበር የቆዩት። ግን አሁን የለየለት የኤኮኖሚ ቀውስ እያሰጋቸው ነው። በቪየና ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ጥናት ኢንስቲቲዩት የምሥራቅ አውሮፓ አዋቂ የሆኑት ቫሢሊይ አስትሮቭ ሁኔታውን ቀላል አድርገው አይመለከቱትም።

“ከችግሩ በተሻለ ሁኔታ ለመላቀቅ የሚችሉት አገሮች ፈታ ያለ ምንዛሪ ያላቸው ወይም የውጭ ንግዳቸውን ብዙ-ወጥ ያደረጉት አገሮች ብቻ ይሆናሉ። የውጭ ንግድ ዕድገት እጅግ አስፈላጊ ነው። ሆኖም እነዚሁ ሃገራት ዕድገታቸውን ያራመዱት ከምዕራቡ ዓለም ብድር በመውሰድና ካፒታልን በማስገባት፤ ከዚያም ምርታቸውን መለሶ በመሸጡ ላይ ነበር። ግን የምዕራቡ ስርዓት በነበረው መንገድ ሊቀጥል ካልቻለ ችግር ነው የሚፈጥርባቸው”

አስትሮቭ ጨምረው እንደገለጹት አብዛኛው ችግር የሚገጥማቸው የአልግሎት ዘርፋቸውን ለመደጎም ሲሉ የምንዛሪያቸውን ዋጋ ከፍ አድርገው ያስቀመጡት አገሮች ይሆናሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ አሁን በባልካን እንደሚታየው የውጭ ንግድ በከፍተኛ መጠን ሲያጋድል ደግሞ ሁኔታውን ለማሻሻል የምንዛሪውን ዋጋ ማረሙ ግድ ይሆናል። አለበለዚያ በቀላሉ ብድር ለማግኘት አይችሉም። በአጠቃላይ የምሥራቁ ችግር መፍትሄ ቁልፍ ያለው በምዕራቡ ዓለም ነው። የምዕራቡ የፊናንስ ዘርፍ ምሥራቁን ለመደገፍ እንዲችል ግን ራሱ መልሶ መጠናከር ይኖርበታል። ጉዞው ረጅም እንዳይሆን የሚያሰጋ ነው።

የታዳጊ ዓለም የወደፊት ዕርምጃም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ፈተና ሳይደቀንበት አልቀረም። የፊናንሱ ቀውስ ተጽዕኖ የልማት ሂደቱን ካበረደው አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል የሚያስጠነቅቁት ባለሚያዎች ብዙዎች ናቸው። የጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲቱት ሃላፊ ዲርክ ሜስነር ለምሳሌ ድህነትን የመታገሉና የአካባቢ ተፈጥሮን የመንከባከቡ ፖሊሲ በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ ችላ እንዳይባል ያስጠነቅቃሉ። አለበለዚያ ቀውሱ ይህን አካባቢ በጣሙን ነው የሚጎዳው። እንደ ባለሙያው ከሆነ አዲስ የኤኮኖሚ ስርዓት ሳይውል ሳያድር መስፈን ይኖርበታል።

“እንደማስበው እነዚህን ሁለት ነገሮች አሁን የግድ ማስተሳሰር ይኖርብናል። የዓለም የፊናንስ ስርዓት መረጋጋትና ከውድቀት መዳን አለበት። በዚህ በኩል አዲስ የቅንጅት ዘዴ የሚያስፈልገን ሲሆን በዚያው መጠን የኤኮኖሚ ቀውስ ሥር እንዳይሰድ ጥረት መደረጉም ግድ ነው። ይህ ካልሆነ በተለይ በታዳጊው ዓለም የሚያስከትለው የኤኮኖሚ ችግርን ብቻ ሣይሆን የሕልውና ፈተናን ጭምር ይሆናል። የበለጠ ድህነትና ረሃብ እናያለን ማለት ነው። ከዚህ የተነሣም በልማት ፖሊሲው ዘርፍ ገንዘብን በሥራ ማዋሉ የፊናንስ ገበያውን ችግር የመፍታቱን ያህል ጠቃሚነት ይኖረዋል”

ዞሮ ዞሮ ከተቀየረው የዓለም ኤኮኖሚ ሁኔታና የሃይል አሰላለፍ አንጻር አዲስ የኤኮኖሚ ስርዓት ማስፈኑ ጊዜ የማይሰጥ ጥያቄ እየሆነ በመሄድ ላይ ነው። በዓለም የኤኮኖሚ አጽናፋዊነት ዘመን ላይ የምንገኝ ቢሆንም ስርዓቱን መቆጣጠሩ ከቀደምቱ የበለጸጉ መንግሥታት ዕጅ አልወጣም። በሌላ በኩል የዓለም ኤኮኖሚ ዕርምጃ ዛሬ እሢያን እንደምሳሌ ብንወስድ በብዙ ዋልታዎች ላይ የቆመ ነው።

“የሃይል አሰላለፉ በብዙ ዋልታዎች ላይ በቆመባት ዓለም መኖር ከጀመርን ቆይተናል። ልብ አላልነው እንደሆን እንጂ! ቀደምቱ የኢንዱስትሪ መንግሥታት ቡድን-ስምንት የሚቆጣጠሩትን የዓለም ኤኮኖሚ ስርዓት አለን በለን ኖረናል። በሌላ በኩል ግን በአጽናፋዊው የዓለም ኤኮኖሚ ያለፉት ሃያ ዓመታት ተጠቃሚዎች ከሁሉም በላይ እሢያውያን መሆናቸውን አላስተዋልንም። ቻይና አንደኛዋ ናት። ሕንድም በጠንካራ ዕድገት ትከተላለች። በ 2020, 2030 ሁለቱ አገሮች ከ 30 እስከ 40-ው የዓለም ኤኮኖሚ ባለድርሻዎች ይሆናሉ። የዓለም ኤኮኖሚ ሚዛን እየተለወጠ የሚሄድ እንደመሆኑ መጠን ታዲያ ሁኔታችንን ከዚህ ማጣጣም አለብን”

እንግዲህ ስርዓቱን በአዲስ መክክ ከማቀናጀት ሌላ የሚበጅ አማራጭ የለም። የዋሺንግተን የዓለም የፊናንስ ጉባዔ ለዚህ መሠረት ሊጥል ቢችል ምንኛ ግሩም በሆነ ነበር።