1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእሥራኤል የጋዛ ዘመቻ በምድርና በባሕር ተስፋፋ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 26 2001

በጋዛ ሰርጥ ላይ ከሣምንት በላይ ሲካሄድ የሰነበተው የእሥራኤል የአየር ድብደባ በምድርና በባሕር የጥቃት ዘመቻ ተጠናከረ። እሥራኤል በታንኮች የታጀበ ጦሯ ወደ ጋዛ ሰርጥ ሰርጎ እንዲገባ በማድረግ የምድር ውጊያ የጀመረችው ባለፈው ምሽት ነው።

https://p.dw.com/p/GRoy
የእሥራኤል ወታደሮች ወሰን ሲሻገሩ
የእሥራኤል ወታደሮች ወሰን ሲሻገሩምስል AP
የአካባቢው የዜና ምንጮች በውጊያው ሳቢያ በርካታ ፍልሥጤማውያን መገደላቸውን ይናገራሉ። ይሁንና በተጨባጭ የተጠቀሰ አሃዝ ለጊዜው የለም። የእሥራኤል ጦር በበኩሉ ከሃማስ ተዋጊዎች ጋር በተካሄደ ከባድ ፍልሚያ ሰላሣ ወታደሮቹ መቁሰላቸውን አመልክቷል። የአረብ የዜና ምንጮች እንደጠቆሙት ደግሞ የእሥራኤል ታንኮች ጋዛ ከተማ ደርሰዋል። በእሥራኤል አባባል የጦሯ ዘመቻ ያተኮረው የሐማስን የሮኬት መተኮሻ ይዞታዎች በመደምሰስ ተግባር ላይ ነው። ሆኖም ፍልሥጤማውያኑ በእሥራኤል አቅጣጫ ቃሣም ሮኬቶችና ከባድ መሣሪያዎችን መተኮሳቸውን ቀጥለዋል። እሥራኤል በሺህ ለሚቆጠሩ ተጠባባቂ ወታደሮች የዝግጁነት ጥሪ ስታደርግ ጦርነቱ ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል መሆኑ እየተነገረ ነው። በሌላ በኩል የእሥራኤልን የጦር ዘመቻ በመኮነን በዓለም ዙሪያ በርካታ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል። በዚህ በአውሮፓ ፈረንሣይ ርዕስ-ከተማ ፓሪስ ላይ ሃያ ሺህ ሰዎች አደባባይ ሲወጡ በጀርመን፣ በብሪታኒያ፣ በግሪክና በስፓኝም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች ታይተዋል። የእሥራኤል የጥቃት ዘመቻ ከዚሁ ሌላ ቱርክን፣ ሊባኖስንና ኢንዶኔዚያን ጨምሮ በርከት ባሉ ሙስሊም ሃገራትም በአደባባይ ተኮንኗል። ይህ በዚህ እንዳለ ከኒውዮርክ እንደተገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ም/ቤት በውዝግቡ ላይ ከአንድ ውሣኔ ለመድረስ እንደገና ያደረገው ሙከራ አልሰመረም። ዲፕሎማቶች እንደጠቆሙት ለዚሁ ምክንያት የሆነው አሜሪካ በሊቢያ የቀረበውን የአስቸኳይ ተኩስ-አቁም ውሣኔ ረቂቅ አልቀበልም ማለቷ ነው።