1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእራት ግብዣ ለስደተኞች

ሰኞ፣ ጥቅምት 29 2008

አንድ ላይ ሲበሉ ይጣፍጣል ይላል ማሪያ ኢቼቫ ባለፈው ሰኔ ወር ለቦን ነዋሪዎች እና መጤዎች የጀመሩት ፕሮጀክት። «ich lade Dich ein » ልጋብዝህ ወይም ልጋብዝሽ» በሚል አላማ ኢቼቫ የጀመሩት ፕሮጀክት የቦን ከተማ ነዋሪዎችን ከስደተኞች ጋር ለማቀራረብ ይፈልጋል።

https://p.dw.com/p/1H2QO
Abendessen mit Flüchtlingen
ምስል DW/G. Hamann

[No title]

እስካሁን ወደ 20 የሚጠጉ የቦን ነዋሪዎች ስደተኞችን ወደቤታቸው እየጋበዙ አብረው ይመገባሉ፤ ይወያያሉ። የቦን ነዋሪ የሆነችው ኒና ሶስት ጎደኞቿን እና አዲሱን ሶርያዊ እንግዳ ኒዳል ማታ እራት አብረው እንዲበሉ ብትጋብዝም፤ የቀረበውን ላዛኛ የሚበላው አጥቶ ሰሀን ላይ እየቀዘቀዘ ነው። ምግቡ የምሽቱ ዋና አካል አይመስልም። ጋባዧ ኒና እና የቦን ጓደኞቿ ለስደተኛው ኒዳል ብዙ ጥያቄ አላቸው። እሱም መልስ ለመስጠት ተዘጋጅቷል። ወደ ጀርመን ከመጣ አንድ አመት ተኩል የሆነው ሶርያዊ ፤ጥያቄውን የሚመልሰውም በጀርመንኛ ነው። «ሰው መርዳት ደስ ይለኛል» እያለ ኒዳል የአውሮፓ ካርታን ጠሬቤዛ ላይ መዘርጋት ጀመረ። «እዚህ ጋር ሆምስ ነው፤ እዚህ ጋር ደግሞ እኔ የምማርበት ከፍተኛ ተቋም ነበር እያለ ለጋባዦቹ ያስረዳል።« ሶርያ ውስጥ አንድ ተማሪ ዮኒቨርስቲ ከጨረሰ በኋላ ውትድርና ይሄዳል። ወቅቱ የጦርነት ጊዜ ስለነበር ውትድርናው ማብቂያ አይኖረውም። ውትድርና ከገባሁ ወይ እንደሚገሉኝ ወይም ሌሎች ሰዎችን መግደል እንደሚኖርብኝ ለኔ ግልፅ ነበር። ይህን ደግሞ አልፈለኩም። »
ኒዳል በሀገሩ ደም አፋሳሹ ጦርነት ሲጠናከርም ወደ አሌፖ ይሰደዳል። ኒዳል አውሮፓ እስኪደርስ የነበረውን ረዥም ጉዞ ለእንግዶቹ ይዘረዝራል። ቱርክ፣ ከዛም በአይሮፕላን ወደ አልጄሪያ፣ ከዛም ለ12 ሰዓታት በበረሀ ወደ ሊቢያ ሄዷል። በጉዞ ላይ ከተዋወቃቸው ሌሎች ሶርያውያን ጋር ለበርካታ ቀናት ተሸሽገው ከቆዩ በኋላ እሱ እና ከነዚህ ከተዋወቃቸው ሶርያውያን መካከል የተወሰኑት መጨረሻቸው የሊቢያ ወህኒ ቤት ይሆናል። እዛም 15 ቀናት ከቆዩ በኋላ በሰው በሰው መልሰው ይለቀቃሉ። ኒዳል ትልቁ ፈተናው ወደ ኢጣሊያ በባህር ያደረገው ጉዞ እንደሆነ ይናገራል። የጀልባው መሳሪያዎች የሚገኙበት ጭለማ ክፍል ሆኖ ለ 17 ሰዓታት ሲጓዝ «ሞቴ የተቃረበ እንደሆነ ነበር የተሰማኝ» ይላል። የሶርያ አሌፓ ከተማን ከለቀቀ አንድ ወር በኃላም ጀርመን ይገባል።
ሰሀኑ ላይ የቀረበው ላዛኛ ቀስ እያለ እየተገባደደ ነው። ኒዳል ጀርመን ከገባ በኋላ ስላለው ህይወቱ ያወራ ጀመር፤ ኒዳል ቦን ከተማ በመምጣቱ ምን ያህል ደስተኛ እንደሆነ እራት የጋበዙት ለመረዳት ብዙ ጊዜ አላስፈለጋቸውም። ኒዳል ስደተኛ ከመሆኑ በስተቀል ከእንግዳ ጋር መብላት የለመድኩት ነው ይላል፤የጋባዧ ጓደኛ ዲትማር« ለኔ ምንም እንግዳ ነገር የለውም። ካውች ሰርፊንግ ወይም ሌሎች እንደዚህ ያሉ የማይተዋወቁ ሰዎች የሚሰበሰቡበትን ቦታ ላየ ሰው ፤ አንድ የማያውቁትን ሰው ለራት ጋብዞ አብሮ ማብሰሉ ምንም አዲስ ነገር አይደለም ። እንደማንኛውም ምሽት አንድ የማያውቁትን እንግዳ ጋብዞ ስለ ባህል ሀሳብ መለዋወጥ እንደማለት ነው» ኒዳል ጀርመን ከገባ በኋላ ለተለያዩ ማህበራት ያገለግላል። « ፕሮ ፋሚሊያ» የባህል ፣ የስፖርት ማህበር እያለ አምስት ማህበሮችን ይተነትናል። ከብዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት ስላለውም የቦን ከተማን ከጀርንያኑ የበለጠ ጠንቅቆ ያውቃል። ይሁንና ወደ የ29 ዓመቱ ጎልማሳ ሁሉም ወደ ጀርመን የሚመጡ ስደተኞች ቶሎ ከማህበረሱ ጋር እንደማይቀላቀሉ የአስተርጓሚነት ስራው ያውቃል።
ከእራት በኋላ የቀረበው የቫኒላ አይስክሬም ቀልጦ ሳህኑን መሙላት ሲጀምር በወሬ የተጠመዱት የዕራት ተጋባዦች ማንካቸውን አንስተው መብላት ጀመሩ። ጀርመናውያኑ አሁንም ለኒዳል ለማቅረብ የሚፈልጉት በርካታ ጥያቄዎች አሉ፤«ብዙ እንደጠየቅንህ ይገባኛል፤ ግን አሁንም ልጠይቅህ የምፈልገው ነገር አለ። ጀርመን ወይም አውሮፓ በሶርያ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ወታደራዊ ኃይል ተጠቅመው መዝመት አለባቸው ትላለህ? ከጀርመን ምን ትጠብቃለህ?»
ለኒዳል ከታኒያ የቀረበለት ጥያቄ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ዛሬ ሀገራቸውን ለቀው የሚሰደዱት ሰዎች ተመልሰው አገራቸውን ለመገንባት ይመለሳሉ? ፕሬዚዳንት አሳድ ለምን በቃኝ አይሉም ? የሚሉ እና ሌሎችም፤ ኒዳል ግን « እኔንጃ አላውቅም» ከማለት በቀር ለዕራት ጋባዦቹ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ የለውም።

Abendessen mit Flüchtlingen
ምስል DW/G. Hamann

ግሬታ ሀማን/ ልደት አበበ
አርያም ተክሌ