1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

   የእስራኤል ምክር ቤት ዉሳኔ የገጠመዉ ተቃዉሞ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ የካቲት 6 2009

ወቅቱም ለአክራሪዎቹ አመቺ ነዉ።እንደነሱዉ ሁሉ እክራሪዉ ቱጃር ፖለቲከኛ ዋይት ሐዉስን በተቆጣጠሩበት፤ ሥለዓለም ፖለቲካ ምንም ከማያዉቁበት ከዚሕ ሰሞን የተሻለ አጋጣሚ የለም።«ይሕ፤ ረቂቅ ሕጉ በሚፀድቅበት ወቅት በግልፅ ተነግሯል።ከሕጉ አርቃቂዎች አንዱ ቤዛለል ስሞትሪች ትራምፕን በስም ጠርተዉ አመስግነዋል።»

https://p.dw.com/p/2XFls
Israel Siedlungspolitik Abstimmung im Parlament
ምስል Reuters/A. Awad

M M T/ Israel der Siedlungsbau und die Verfassung - MP3-Stereo

እስራኤል በሐይል በያዘቸዉ የፍልስጤም ግዛት የአይሁድ ቤቶች የተሰሩባቸዉ የፍልስጤማዉያን የግል ቦታዎች የአይሁድ ሕጋዊ ይዞታ እንዲሆኑ የእስራኤል ምክር ቤት ያሳለፈዉ ዉሳኔ፤ እስራኤሎችን ሲያወዛግብ ከዉጪ ተቃዉሞና ዉግዘት ገጥሞታል።ከምክር ቤቱ 120 አባላት በ60ዉ የድጋፍ፤ በ52 የተቃዉሞ እና በተቀሩት ድምፀ ተዓቅቦ በፀደቀዉ ዉሳኔ መሠረት 4000 የአይሁድ ቤቶች የተገነባበት የፍልስጤሞችን ቦታ የአይሁድ ሕጋዊ ንብረት ይሆናል።ዉሳኔዉ እስራኤል ዉስጥ የሕግና የፖለቲካ ዉዝግብ ቀስቅሷል።ከዉጪ ደግሞ ጠንካራ ተቃዉሞና ዉግዘት ገጥሞታል።

ተቺዎቹ ፍትሕን-የደፈለቀ፤ ፖለቲካን-በስሜት ያጣፋ፤ የሁለት መንግሥታት ዕቅድን ያጨናጎለ  ይሉታል።ለደጋፊዎቹ ግን በርግጥ «ፌስታ» ነዉ።የሐገሪቱ ሕግ አዉጪ ምክር ቤት ዉሳኔ ሕጋዊ ለመሆን ብዙ የፍትሕ መሰናክሎችን ማለፍ ግድ አለበት።በእየሩሳሌሙ የሒብሩ ዩኒቨርስቲ የሕግ ምሁር ዩቫል ሻኒይ እንደሚሉት አብዛኞቹ የእስራኤል የሕግ ባለሙያዎች ዉሳኔዉን የእስራኤል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዉድቅ ያደርገዋል ብለዉ ይጠብቃሉ።

«እንደሚመስለኝ የአብዛኞቹ የእስራኤል የሕግ ባለሙያዎች እምነት የሐገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዉሳኔዉን ዉድቅ ያደርገዋል የሚል ነዉ።ምክንያቱም ዉሳኔዉ ከፍተኛ የሕግ ችግር ሥላለበት፤ እና የአንዱን ሕብረተሰብ የመሬት ባለቤትነት በተናጥል ዉሳኔ ለሌላዉ የሚያስተላልፍ በመሆኑ ነዉ።ከዚሕ በተጨማሪ የእስራኤል ጠቅላይ ሐጋቤ ሕግ በጣም ባልተለመደ ሁኔታ ዉሳኔዉ ሕገ-መንግሥቱን እና  ዓለም አቀፍ ሕግን የሚፃረር በመሆኑ ለገበራዊነቱ እንደማይከራከሩ አስታዉቀዋል።»

Israel Siedlungspolitik Ofra in Westjordanland
ምስል Reuters/B. Ratner

በፖለቲካዉ ግንባር የምክር ቤቱ ዉሳኔ በሥልጣን ላይ ያሉትን የቀኝ አክራሪዎችን ፍላጎት ለማርካት ያለመ ነዉ።በጀርመኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም የእስራኤል ጉዳይ አጥኚ ፔተር ሊንትል እንደሚሉት በስልጣን ላይ ያለዉ የቤንያሚን ኔታንያሁ መንግሥት ባለፉት 30 ዓመታት ከነበሩት አክራሪ መንግሥታት ሁሉ እጅግ አክራሪዉ ነዉ።

«በእርግጠኝነት፤ መሠረታዊ ምክንያት በሥልጣን ላይ ያለዉ የእስራኤል መንግሥት ባለፉት ሰላሳ-ዓመታት ከነበሩት በጣም ቀኝ አክራሪዎች አንዱ መሆኑ ነዉ።ገሚስ አባላቱ የፍልስጤሞቹ የምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የእስራኤል አካል መሆን አለበት ባዮች ናቸዉ።ይኸኛዉ ክንፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጣም ተጠናክሯል።»

በዚያ ላይ ባለፉት ሳምንታት ሁለት ነገሮች ታከሉ።የኔታንያሁ መንግሥት «ሕገ ወጥ» ያለዉን የአሞና መንደርን በማፍረሱ ያኮረፉ አሉ።ሐብያት ሐየሁዲ (አይሁድ ሐገራችን) ከተሰኘዉ አክራሪ ፓርቲ ጋርም ጥምረት ፈጥሯል።ሊንተል እንደሚያምኑት ያኮረፉትን ለማባበል፤ የተጣመሩትን ለማስደሰት የኔታንያሁ መንግስት የፍልስጤሞችን መሬት መዉረሱን እንደ ጥሩ መፍትሔ ነዉ ያየዉ።

ወቅቱም ለአክራሪዎቹ አመቺ ነዉ።እንደነሱዉ ሁሉ እክራሪዉ ቱጃር ፖለቲከኛ ዋይት ሐዉስን በተቆጣጠሩበት፤ ሥለዓለም ፖለቲካ ምንም ከማያዉቁበት ከዚሕ ሰሞን የተሻለ አጋጣሚ የለም።«ይሕ፤ ረቂቅ ሕጉ በሚፀድቅበት ወቅት በግልፅ ተነግሯል።ከሕጉ አርቃቂዎች አንዱ ቤዛለል ስሞትሪች ትራምፕን በስም ጠርተዉ አመስግነዋል።»

ወሳኔዉን ለዘብተኛ እና ግራ ዘመም የእስራኤላዉያን ተቃዉመዉታል።የእስራኤል ዴሞክራሲ የተሰኘዉ  ተቋም ይፋ ያደረገዉ ጥናት እንዳመለከተዉ ከአይሁዱ ማሕበረሰብ 53 በመቶ ያሕሉ የአይሁድ ሰፈራ መንደር መስፋፋቱን ይቃወማሉ።ሐሬትስ የተሰኘዉ የእስራኤል ግራ ዘመም ጋዜጣ በበኩሉ የኔታንያሁ መንግሥት  የምክር ቤቱ ዉሳኔ የሚያስከትለዉን መዘዝ ሊያጤነዉ ይገባል ይላሉ።ዉሳኔዉ ለእስራኤልና ለፍልስጤም ጠብ የሁለት መንግስታት መፍትሔ የሚባለዉን የተንጠለጠለ ሐሳብም ጨርሶ የሚገድልም ነዉ።

Israel Siedlungspolitik Proteste in Kofr Qadom
ምስል Reuters/M. Torokman

«ሕጉ የሁለት መንግስታት መፍትሔን የሚያከሽፍ ነዉ።ምክንያቱም ዉሳኔዉ ሕጋዊ የሚያደርጋቸዉ ሰፈሮች የሁለት መንግሥታት መፍትሔ ገቢራዊ እንዳይሆን እንቅፋት  የነበሩ ናቸዉ።ዉሳኔዉን ያፀደቁት ወገኖች ዓላማ የሁለት መንግሥታት መፍትሔን ለማደናቀፍና እስራኤል በሐይል ከያዘችዉ ግዛት እንዳትለቅ ማድረግ ነዉ።»

በዚሕም ምክንያት ጀርመን፤ ፈረንሳይና ብሪታንያ ዉሳኔዉን አጥብቀዉ ተቃዉመዉታል።ቱርክ አዉግዛዋለች። የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር፤ እና የአረብ ሊግ ደግሞ የመሬት «ሌብነት» በማለት አዉግዘዉታል።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ