1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእጅ ስልክ በጤና ላይ ሊያስክትል የሚችለው ሳንክ፣

ረቡዕ፣ ግንቦት 24 2003

በእጅ ስልክ ተጠቃሚ ነዎት? የአጅ ስልክ ፤ ለጤና ጠንቅ ይኖረዋል የሚለው መላ- ምት በተማራማሪ ጠበብት ፣ሙሉ በሙሉ እስኪረጋገጥ ፣ አንዳንድ ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም ። እንዴት ጥንቃቄ ማድረግ ይቻላል? የዛሬውን ሳይንስና ኅብረተሰብ ጥንቅር ይከታተሉ--

https://p.dw.com/p/RRLv
የእጅ ስልክ በጤና ላይ ሊያስክትል የሚችለው ሳንክ፣
ምስል picture-alliance / maxppp

ምርምሩ፤ ከእነአካቴው አልተጠናቀቀም ስለሚባል እንጂ የእጅ ስልክ በጤና ላይ የሆነ እክል ሊኖረው እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል። የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት፣ ትናንት እንደገለጠው ፤ የእጅ ስልክ ምናልባት ለሳንባ ካንሰር ያጋልጥ ይሆናል። በተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም በእጅ ስልክ መጠቀም፤ የሆነ የጭንቅላት እባጭ ሊያስከትል ይችላልና የእጅ ስልክ ተጠቃሚዎች፣ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት የነቀርሳ«ካንሰር» ጠበብት መምከራቸው ተመልክቷል። ከ 14 አገሮች የተውጣጡ 31 የሳይንስ ጠበብት፣ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ቅርንጫፍ በሆነው ዓለም አቀፍ የነቀርሳ ምርምር (IARC) ማዕከል ስብሰባ ካካሄዱ በኋላ ነበረ፤ የእጅ ስልክ ለጤና ጠንቅ የሚሆን ጨረር ከሚፈነጥቁት መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችል መግለጫ የሰጡት። ዓለም አቀፉ የነቀርሳ ተመራማሪ ድርጅት ፤ የእጅ ስልክን ፤ ከሌሎች አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ከሚነገርላቸው ፤ከአስቤስቶስ ፤ እርሳስ፤ ክሎሮፎርም የተሰኘው የክሎሪን ፣ ካርበንና ሃይድሮጂን ቅልቅል ፣ ዳዮክሲን የትምባሆ ጢስና ከመሳሰሉት፣ ለነቀርሳ (ካንሠር ) መነሻ ሰበብ ከሚሆኑት ጋር ነው የደመረው።

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት፤ በተለይም ቅርንጫፉ፤ ዓለም አቀፉ የካንሰር የምርምር ተቋም አሁን ከዘረዘርናቸው ጋር በማያያዝ ፤ ለነቀርሳ (ካንሠር) በቀጥታ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ካላቸው በእንግሊዝኛው አገላለጽ (Carcinogenic)ከሚሰኙት አንዱ የእጅ ስልክ ነው። ጠበብቱ ይህን ሲሉ በእርግጥ ምን ማለታቸው ይሆን? በበርሊን የጀርመን የአደገኛ ጨረር መከላከያ መ/ቤት ቃል አቀባይ ሄር ፍሎሪያን ኤምሪኽ--

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ቅርንጫፍ ፤ የካንሠር ተማራማሪው ተቋም የቡድን አባላት ፣ ሊቀመንበር ጆናተን ሳሜት እንደገለጡት፤ የኤልክትሮ-መግነጢሳዊ መነሻና መድረሻየራዲዖ ሞገድ ፤ በቀጥታ ለካንሠር መነሻ ሰበብ ሊሆን ይችላል። የእጅ ስልክ በመጠቀም «ግሊዮማ» የተሰኘው የጭንቅላት የካንሠር ዓይነት ሊያጋጥም እንደሚችል የምርምር ሂደቶች ይጠቁማሉ ነው የሚባለው።

እንደሚታወቀው ፤ የእጅ ስልክ እ ጎ አ በ 1980ኛዎቹ ዓመታት መግቢያ ላይ ለህዝብ ከቀረበ ወዲህ ፣ በዓለም ዙሪያ እጅግ ተስፋፍቶ በአሁኑ ጊዜ ቁጥሩ 5 ቢሊዮን ደርሷል።

በአሁኑ ጊዜ፣ ለዕለታዊ ኑሮ እጅግ ተፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም፣ የኢንዱስትሪ ጠበብት እንደሚሉት፤ በጤንነት ላይ አደጋ ይደቅናል ተብሎም ቢነገረው ተጠቃሚው ህዝብ አይሰማም።

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት የአጅ ስልክን በተመለከተ ምን ዓይነት መግለጫ እንደሚደሚሰጥ ወይም ምን ዓይነት አቋም እንደሚይዝ በጉጉት ነበረ የሚጠበቀው። ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚሠሩ ኢንዱስትሪዎች፣ አንዳንድ ለምግብነት የሚውሉ አትክልቶችም ምናልባት በቀጥታ ካንሠር ሊያመጡ ይችላሉ በማለት ከእጅ ስልክ በኩል ሊከሠት የሚችል አደጋን አቃለው ለማየት ሞክረዋል።

ከዚህ ቀደም የተካሄዱ የምርምር ውጤቶች ፤ የእጅ ስልክ ከካንሠር ጋር ግንኙነት እንዳለው በግልጽ ያስቀመጡበት ሁኔታ የለም ። ባለፈው የካቲት በዩናይትድ እስቴትስ የተካሄደ ጥናት ደግሞ ፤ በእጅ ስልክ መጠቀም በጭንቅላት ህዋሳት ተግባር ላይ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል ይላል። የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ፤ ቅርንጫፍ፣ ዓለም አቀፉ የካንሰር ምርምር ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ክሪስቶፈር ዋልልድ፤ በይበልጥ ምርምር መቀጠል ተፈላጊነት አለው። በተለይ ከመጠን በላይ በአጅ ስልክ መጠቀም ምን ሊያስከትል እንደሚችል ሊተኮርበት ይገባል ማለታቸው ተጠቅሷል። የእጅ ስልክ ለጤንነት ጠንቅ ሊኖረው ይችላል ሲባል እንዲሁ ለመናገር ያህል የተነገረ ነው ብሎ ማቀለል ሊጠቅም አይችልም ። ተመራማሪ ጠበብት ምርመራቸውን በይበልጥ አጠናክረው ቁርጡን እስኪያሳውቁ ድረስ ፤ ጎጂ የሚሰኘውን የጨረርን ዓይነት ለመቀነስ በሚረዱ መሣሪያዎች መገልገሉ ሊበጅ ይችል ይሆናል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ