1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእጅ አዙር ጦርነት ያመሳት የመን

ሰኞ፣ ሐምሌ 13 2007

ፕሬዝዳንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ መንግስት የየመን ሁለተኛ ከተማ የሆነችውን ኤደን ነጻ አውጥቻለሁ ባለ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሑቲ አማጽያን በከተማዋ ዳር ሳድ የተሰኘ የመኖሪያ መንደር በጣሉት ጥቃት 43 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። የመን በሑቲ አማጽያን፤የስደተኛው መንግስት ወታደሮች፤

https://p.dw.com/p/1G1nL
Flughafen Aden Yemen Kampf zwischen Houthi Rebellen und Militär
ምስል picture-alliance/AA/Str.

የእጅ አዙር ጦርነት ያመሳት የመን

የአይሲስ ታጣቂ ቡድንና አልቃዒዳ ከውስጥ በኢራንና ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ ከውጭ መታመሷን ቀጥላለች።

ዘመናዊ የአሜሪካን ተዋጊ የጦር ጀቶችና ተተኳሾች በታጠቀችው ሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿ የሚታገዙት የስደተኛው የየመን መንግስት ወታደሮችና ደጋፊዎች የኤደን ከተማን «ነጻ አውጥተናል» ያሉት ባለፈው ሳምንት ነበር። 100 የጦር ጀቶች፤150 ሺህ ወታደሮችና ተዋጊ የጦር መርከቦች ያካተተውና በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ቅንጅት ዋንኛ ዒላማ የሑቲ አማጽያንና የቀድሞ የየመን ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳላህ ታማኞች ናቸው። ኩዌት፤ባህሬን፤ኳታር፤ሞሮኮ፤ሱዳንና ግብጽ እጃቸውን ያስገቡበት የአየር ጥቃት የሑቲ አማጽያን የጦር ሰፈሮችን፤ስኩድ ሚሳዔሎችን፤የአየር ጥቃት መከላከያዎችን ሲደበድቡ ቢከርሙም አንዳች የረባ ውጤት ለማስመዝገብ ወራት ወሰደባቸው።

አሁን በሳዑዲ አረቢያ በስደት ላይ የሚገኘው የየመን መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ኻሊድ ባሃህ ከባብ ኤል ማንደብ የባህር ወሽመጥ 170 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን የኤደን ከተማ ነጻ መውጣት ያስታወቁት በፌስቡክ ማህበራዊ ገጻቸው ነበር። ሳዑዲ አረቢያ ላይ ሆነው የመንን ለመምራት የሚታትሩት ፕሬዝዳንት አብድ ረቦመንሱርሐዲ የአገር ውስጥ ጉዳይና የትራንስፖርት ሚኒስትሮቻቸውን ወደ ኤደን መላካቸውን ተሰምቷል። እንደ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ከሆነ ለአራት ወራት በዘለቀው የርስ በርስ ጦርነት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የኤደን ነዋሪዎች መመለስ ጀምረዋል። ከተመላሾቹ አንዱ የሆኑት ሞዓቴዝ አል ማይዙሪ የክራተር ነዋሪ ናቸው። «ህይወት የለም፤ሆስፒታል የለም። መብራትና ውሃም የለም።» የሚሉት ሞዓቴዝ በመንደራቸው አቅራቢያ ሁለት የውሃ ምንጮች ባይኖሩ ኖሮ ነዋሪዎች በውሃ ጥም ባለቁ ነበር ሲሉ ይናገራሉ። የኤደን ከተማን ከሑቲ አማጽያን አስለቅቀናል የሚሉት የየመን መንግስት ታማኞች መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱት ነዋሪዎች እንዲመለሱ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

Jemen Kämpfe um Aden
ምስል Reuters/Str

«እግዚአብሄር ይመስገንና ይህ የመኖሪያ አካባቢ ሙሉ በሙሉ ነጻ በመሆኑ ነዋሪዎች ተመልሰው እንዲመጡ ጥሪ አድርገናል። ካሁን በኋላ የዜጎችንና የነዋሪዎችን ንብረት እንጠብቃለን። ስለዚህ የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው የሄዱ ዜጎች ሁሉ ተመልሰው በመምጣት በሰላም መኖር ይችላሉ።»

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሁማን ራይትስ ዎች ባለፈው ግንቦት ወር ባወጣው ዘገባ ሳዑዲ አረቢያ በምትወስደው የአየር ጥቃት የጦር ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል መክሰሱ አይዘነጋም። በተቋሙ መሰረት ሳዑዲ አረቢያ ከዘጠኝ አጋሮቿ ጋር የምትወስደው ጥቃት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ህግጋት ተጥሰዋል።ይሁንና በየመን የሚገኘው ቢሮው በአየር ጥቃቱ የወደመበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ለሳዑዲ አረቢያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የምታቀርበው አሜሪካንም ይሁኑ ደብዳቢዎቹ ከአየር የሚዘንበውን ቦምብና ሚሳዔል አላስቆሙም። እናም ኤደንን ጨምሮ የየመን ከተሞች ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸዋል።የኤደን ከተማ የአየር ማረፊያ ሰራተኛ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ሲያነጋገራቸው በጽዳት ስራ ላይ ነበሩ።

«የአየር ማረፊያው ከሑቲ አማጽያንና የሳሌህ ታማኞች ከለቀቁ ከሁለት ቀናት በኋላ የጽዳት ዘመቻ ጀምረናል። እግዜር ከፈቀደ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያው በመላ አገሪቱ ካሉት ሁሉ ምርጡ ይሆናል።»

የሑቲ አማጽያን ተዋጊዎቻቸው ከኤደን ከተማ ማፈግፈጋቸውን ቢናገሩም የመንግስቱ ወታደሮችና ደጋፊዎች ግን ከተማዋንን ሙሉ በሙሉ አተቆጣጠሩም ሲሉ መናገራቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።የፕሬዝዳንት አብድ ረቦመንሱርሐዲ መንግስት ግን ከኤደን በመነሳት ሙሉ የመንን ከሑቲ አማጽያን የማጽዳት እቅድ ሰንቋል።

Karte Jemen Aden englisch
ምስል DW

በሳዑዲ አረቢያ የአየር ጥቃት የሚታገዘው የመንግስት ወታደሮች ዘመቻ ከኤደን ከተማ በስተሰሜን በላሃጅ ግዛት የላቡዛ የጦር ሰፈርን መቆጣጠራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። የሁለቱ ወገኖች ግፋ በለው በተጫናት የየመን ዋና ከተማ ሰንዓ የሚገኘው የዶይቼ ቨሌ ተባባሪ ዘጋቢ ግሩም ተ/ሐይማኖት ግን የመንግስት ወታደሮች እንደሚሉት የሑቲ አማጽያንን በቀላሉ ማሸነፍ እንደማይቻል ይናገራል።

የሑቲ አማጽያን የሺዓ እስልምና እምነት ይከተላሉ።በአሜሪካ እና እስራኤል ላይ ያላቸው አቋምም የተለየ አይደለም። ነገር ግን ከውስጥም ይሁን ከውጪ ብዙ ጠላቶች አሏቸው።በሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿና ከሐዲ ስደተኛ መንግስት ጦርነት የገጠሙት ሰሜናውያኑ ሑቲዎች በአረብ ባህረ-ሰላጤ የአልቃኢዳን ክንፍ (al-Qaeda in the Arabian Peninsula) ጋር ጠበኛ ናቸው። በኢራቅና ሶርያ በእስላማዊ ህግጋት የሚተዳደር አገር መስርቻለሁ የሚለው የአይሲስ ታጣቂ ቡድን በየመን ጠናካራ መሰረት ከማግኘቱ ባሻገር ተከታታይ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች በመፈጸም በርካቶችን ለህልፈት እየዳረገ ነው። አል-ሂራቅ የተሰኘው ቡድንና ደቡብ የመናውያን መገንጠልን ያቀነቅናሉ። የቀድሞው ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳሌህ ግን ከሑቲዎቹ ጋር አብረው ይሰራሉ እየተባሉ ይታማሉ። ዛሬም ድረስ ጠንካራ ተሰሚነት ያላቸው ሳሌህ የሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿን ጥቃት አጥብቀው የሚቃወሙ ናቸው።ለግፉዓን ቆመናል ኢ-ፍትሃዊነትን እንታገላለን ሲሉ የሚደመጡት የሑቲ አማጽያን እስካሁን በይፋ መንግስት አልመሰረቱም። ይሁንና በመንግስት ተቋማት ውስጥ አብዮታዊ ኮሚቴ ተብለው የሚጠሩትንና ከፍተኛ የውሳኔ ሰጭነት ጉልበት ያላቸው አባሎቻቸውን መረብ ዘርግተዋል። ቀድሞ የሱኒ እስልምና ተከታዮች የነበሩ መስጊዶችን ሼኮች የጸሎት ስርዓቱንም ቀይረዋል እየተባሉ ይተቻሉ-በየመናውያን ዘንድ። አማጽያኑ ሰንዓንም ሆነ መላ የመንን በቀላሉ ቢቆጣጠሩም ብዙ ፈተና እንዳለባቸው ግሩም ተ/ሐይማኖት ይናገራል።

Kämpfe um den Hafen von Aden
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Muhammed

የየመን ቀውስ ሲነሳ ወሬው ሁሉ የሱኒና ሺዓ፤የሑቲና የመንግስት፤የሳዑዲ አረቢያና ኢራን ትርክት ይበረታል። ሞት እና ስደት የተረፋቸው የመናውያን ግን ሰሚ አጡ አንጂ ሰላም ይፈልጉ ነበር።የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን የየመን አስተባባሪ ክሪስቲን ቡዘር ድርጅታቸው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታም ይሁን መሰረታዊ የህክምና ግልጋሎት ለመስጠት መገደዱን ይናገራሉ።

የመናውያን አሁን በህይወት የመኖር እና ያለመኖር፤ በቂ የምግብና የውሃ አቅርቦት ያሳስባቸዋል የሚሉት ክሪስቲን ቡዘር አገራቸው ወደ ሰላማዊ ህይወት የምትመለስበት ቀን ይናፍቃቸዋል ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

በኤደን ከተማ በሚገኘው የአልናኪብ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሂሽማን ባሽራሄል በቂ ግልጋሎት ለየመናውያን ማቅረብ መቸገራቸውን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

«አልናኪብ ሆስፒታል በሞርታር ጥይትና የቦምብ ፍንጥርጣሪ በቆሰሉ ሰዎች ተጨናንቋል። ከዚህ በተጨማሪ ትኩሳት እና ወባ ለያዛቸውም የህክምና አገልግሎት ይሰጣል። ሆስፒታላችን ትንሽ በመሆኑ ለሁሉም በቂ የሆነ ግልጋሎት ለማቅረብ የሚያስችል አቅም የለንም።»

የመን ሰላም ቢርቃትም ዜጎቿ በሰላም እጦት ቢሰቃዩም ለምስራቅ አፍሪቃውያን ስደተኞች ግን በሯን አልዘጋችም። ወይም መዝጋት አልቻለችም። የኢትዮጵያ፤ሶማሊያ እና ኤርትራ ዜጎች በየመን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት መጠለያዎች ይገኛሉ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ መሰረት አሁን በአገሪቱ 257,645ስደተኞችና 8,674ተገን ጠያቂዎችም ይገኛሉ። የቀይ ባህርን አቋርጠው በየመን ሳዑዲ አረቢያ መግባት ያለሙት ስደተኞች ጉዞ ግን አገሪቱ ወደ ውጥንቅጥ ከገባች በኋላም ጋብ አላለም።የኮሚሽኑ የየመን ቃል አቀባይ አንድሪያስ ኔድሃም የየመን የር በርስ ጦርነት ከተጀመረበት ከወርሃ መጋቢት ጀምሮ ከ10 ሺህ በላይ ስደተኞች የመን መግባታቸውን ይናገራሉ።

«እነዚህ ሰዎች ስደተኛና ተገን ጠያቂዎች ሲሆኑ በዋናነት የሚመጡት ከጅቡቲና ከሶማልያ ነው። የሚያስገርመው ነገር በገሪቱ በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት ምክንያት 16 ሺህ ስደተኞች የመንን ጥለው የሄዱ ሲሆን በዚሁ ጊዜ ውስጥ ደግሞ 10 ሺ ስደተኞች ወደ የመን ገብተዋል። በሚያሳዝን ሁኔታ እነዚህ ሰዎች በህገ-ወጥ የሰዎች አሸጋጋሪዎችና የጀልባ ባለቤቶች በየመን ሁሉም ነገር ጥሩ መሆኑና ሲደርሱ ጥሩ እድል እንደሚገጥማቸው ተነግሯቸው ተታለው ነው የሚሄዱት።»

Dschibuti Flüchtlinge
ምስል DW/A. Stahl

ይህ ታሪክ ሰንዓ ላይ ለከተመውና የበርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ሰቆቃ ለተመለከተው ግሩም ተ/ሐይማኖት አዲስ አይደለም። ግሩም በየመን ከየመን ቀውስ ሸሽተው የሄዱትም እየተመለሱ መሆኑን ይናገራል።

ሳዑዲ አረቢያ የመንግስት ወታደሮችን ግፋ በለው ስትል ኢራን በበኩሏ ለየመን ማገዟን እንደምትቀጥል አስታውቃለች። ባለፈው ቅዳሜ የኢራኑ ታላቅ መሪአያቶላ አሊ ኻሚኒ በአንድ መስጊድ ባደረጉት ንግግር ኢራንን ከኑክልየር ጦር መሳሪያ ባለቤትነት የሚከለክለው ስምምነት ጸደቀም አልጸደቀ በቀጣናው የሚገኙ ወዳጆቻችንና የፍልስጤም፤የመን፤ሶርያ፤ኢራቅ፤ባህሬን እና ሊባኖስ የሚገኙ ሰዎችን ማገዛችንን አናቆምም ብለዋል። በእርግጥ እርሳቸው ሱኒ አሊያም ሺዓ ብለው አልከፋፈሉም። አንዱ ጋ ግን ኢራን ለመኖሯ፤የእጅ አዙሩም ጦርነት ስለመቀጠሉ ጥቆማ ሰጥተዋል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሠ