1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦባማ ድጋሚ መመረጥ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 28 2005

ባራክ ኦባማ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝደንትነት ስልጣን የሚያበቃቸዉ የምርጫ ዉጤት ይፋ መሆን ዓለም ዓቀፍ ከተጓዳኞቻቸዉን ብቻ ሳይሆን የተቺዎችንም ጭምር ድጋፍ ማስከተሉ ነዉ የታየዉ።

https://p.dw.com/p/16fAG
ምስል AP

እንዲያም ሆኖ የዛሬ አራት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ኦባማ በፕሬዝደንት ሲመረጡ የታየዉ ዓይነት ተስፋና የተጠበቀዉን ያህል ምኞት ከአባታቸዉ ትዉልድ መንደር ከኬንያዋ ኮጌሎ በቀር እጅግም አልተሰማም። አድናቂና ተጓዳኞቻቸዉ ዛሬም ለፍትህና ርትዕ፤ ለህዝቦች መቀራረብ የተሻለ ይሰራሉ የሚል ተስፋቸዉን ነዉ የገለፁት። ተቺዎች ባንፃሩ የገቡትን ቃል በተግባር አላሳዩም በሚል ከመልዕክታቸዉ በተጓዳኝ ዓለምን የሚንጧን ችግሮች ለማስወገድ እንዲጥሩ ግፊቱን አጠናክረዋል። ሆኖም ግን ዳግም ድላቸዉ የደስታ መልዕክትን ለኦባማ ከየአቅጣጫዉ አስጎርፏል። የአዉሮጳ ሀገራት በተናጠል የደስታ መልዕክቶቻቸዉን ቢያስቀድሙም የአዉሮጳ ኅብረት በፋንታዉ የጋራ ድምፅ አሰምቷል።

USA Wahl Wahltag 2012 Barack Obama als Wahlsieger
ምስል Reuters

የኅብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ማርቲን ሹልዝ የኦባማ መርህ ተጨማጭነት ይታይበታል በማለትሉ ዉጤቱ አመላክቷል ያሉትን ገልፀዋል፤

«እንደሚመስለኝ በእቅድ ከሚመሩትና ተጨባጭ ፖለቲካዊ ምርህ ከሚመከተሉት ፕሬዝደንት ኦባማ አዉሮጳዉያን ለማኅበራዊ ፍትህ፤ ለህዝቦች መቀራረብ ተጨማሪ ርምጃዎችን ይወስዳሉ ብለዉ ይጠብቃሉ። ከዚህም ሌላ የኦባማ ሃሳቦች ከሚት ሮምኒ ይልቅ ወደተጨባጭነት የቀረቡና ተዓማኒነት ያላቸዉ ይመስላሉ። እንደሚመስለኝ ኦባማ ያሸነፉበት የምርጫ ዉጤት አክራሪ የፖለቲካ መርህ የሚከተሉ አንዳንድ ሪፑብሊካን የሚያራምዱትን ብዙሃኑ የአሜሪካን ዜጋ እንደማይቀበለዉ አሳይቷል።»

የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ጊ ሙንም ከደስታ መልዕክታቸዉ በተጓዳኝ የሶርያና የመካከለኛዉ ምስራቅን ችግር ለማስወገድ በቅርበት ለመስራት መዘጋጀታቸዉን ገፀዋል። ወደበርሊን ብቅ እንዲሉ የጋበዙት የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በበኩላቸዉ ከኦባማ ጋ አብረዉ መስራቱ እንደሚያስደስታቸዉ ነዉ የተናገሩት።

«ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማን ዳግም በመመረጣቸዉ ከልብ እንኳን ደስ ያልዎት የሚል መልካም ምኞቴን መግለፅ እፈልጋለሁ። በደንብ እንተዋወቃለን። በጋራ ለሚኖረን ተጨማሪ የትብብር የሥራ ጊዜም ደስተና ነኝ።»

ከተቃዋሚዉ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ የቀድሞዉ የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር በበኩላቸዉ ኦባማን ትክክለኛዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ነዉ ያሏቸዉ፤

USA Wahlen Präsident Barack Obama wiedergewählt Rede und Konfetti
ምስል dapd

«ኦባማ የዩናይትድ ስቴትስን ፕሬዝደንት ይዘዉ በመቀጠላቸዉ ተደስቻለሁ፤ ከግሌ የአዉሮጳዊ አመለካከትም ትክክለኛዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት መሆናቸዉን አምናለሁ። ስጋቴ ፕሬዝደንት ራምኒ የተለያየችዉን ሀገር ፈፅመዉ ይበትኗታል የሚል ነበር። ኦባማ ሀገሪቱ ዉስጥ የተለያዩ ፍላጎቶችን፤ የተለያዩ መደቦችን፤ የተለያዩ ጎሳዎችን ወደአንድነት የማምጣት አቅሙ አላቸዉ፤ እናም ይህ ነዉ ብዙዎች ቢጠራጠሩም በመጨረሻ በአብላጫ ድምፅ ዳግም እንዲመረጡ ምክንያት የሆነዉ ብዬ አምናለሁ።»

የኦባማ ድል ይፋ ሲሆን ወደመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዞ ላይ የነበሩት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምሮን ከእሳቸዉ ጋ በትብብር መስራታቸዉን እንደሚወደዱት አመልክተዋል። ነገሮችን የሚረዱና አስተማማኝ ተጓዳኝ ሲሉ ኦባማን ያሞካኩት የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ የዓለማችን የኃያላን ቁንጮ ያሏት አሜሪካ ሩሲያን እንደ ዋነኛ ጠላት አድርጎ የማይመለከት መሪ መምረጧ እንዳስደሰታቸዉ ተናግረዋል። በፕሬዝደንትጆርጅቡሽዘመንየነበረዉንየወዳጅዘመድጉብኝትእንዲሁምከዜጎቿየሚላክገንዘብእገዳንሚትሮምኒይደግሙታል ከሚልስጋትየተላቀቀችዉኩባ፤ዉጥረቱንያረገቡላት ኦባማ በማሸነፋቸዉ እፎይ ብላለች።

USA Wahlen Präsident Barack Obama wiedergewählt Reaktionen Kenia Kogelo
ምስል dapd

የአረብ ሊግ ኦባማ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸዉን ተጠቅመዉ በመካከለኛዉ ምስራቅ ሰላም እንዲሰፍን እንዲጥሩ ጠይቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናትንያሁ እስራኤል ስልታዊ ያለችዉ የሜሪካን እስራኤል ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሲመኙ፤ የፍልስጤሙ መሃሙድ አባስ በበኩላቸዉ ኦባማ የሰላም ዉይይቱን አጠናክረዉ ያስቀጥላሉ የሚል ተስፋቸዉን ገልጸዋል። ቀዝቀዝ ብላ ድምጿን ያሰማችዉ ኢራን ለ30ዓመታት የተቋረጠዉን ግንኙነት ያሻሽላሉ ብላ ስትጠብቅ በኒኩሊየር መርሃግብሯ ምክንያት የተጣለባት ማዕቀብ ህዝቧን ቤዛ ፍለጋ የታገተ አስመስሎታል በሚል ተችታለች። ሪፑብሊካንም ሆነ ዴሞክራት ቢመረጥ ሀገራቸዉን የሚመለከተዉ መርህ እንደማይለወጥ የጠቆሙት የአፍጋኒስታን ፕሬዝደንት ሃሚድ ካርዛይ ድል የኦባማ መሆኑ ይፋ ሲሆን የሀገራቱ ግንኙነት እንዲጠናከር ጠይቀዋል። ታሊባን በበኩሉ ኦባማ በሀገራቸዉ የዉስጥ ጉዳይ እንዲያተኩሩና ከአፍጋኒስታን ጦራቸዉን እንዲያስወጡ አሳስቧል።

ስልጣን ከያዙ ወዲህ ያልጎበኟት የኦባማ አባት ሀገር ኬንያም በመሪዋ በኩል መልካም ምኞቷን አስተላልፋለች። የዘመዶቻቸዉ መገኛ የሆነችዉ ኮጌሎ መንደር በኦባማ ዘመን መንገዶች፤ መብራትና ዉሃ ለማግኘት በመታደሏ ኗሪዎቿ እንቅልፍ አጥተዉ ዉጤቱን ሲጠብቁ ማደራቸዉ ተሰምቷል።

የህዝቡን ስሜት የዶቼ ቬለ ኪስዋኺሊ ቋንቋ ክፍል ዘጋቢ ሁኔታዉን እንዲህ ገልፆታል፤

«በዚህ መንደር ለኬንያዉያን የደስታ ጊዜ ነበር፤ ሌሊቱን ሙሉ ኦባማ የኬንያ ዝርያ ያለዉ ፕሬዝደንት ለሁለተኛ ጊዜ ተመረጠ እያሉ ሲዘምሩ ነዉ ያደሩት። የኮጌሎ መንደር ይለማል የሚል ተስፋ ነዉ ያላቸዉ፤ ቀድሞ መሰረተ ልማት ያልነበራት ይህች መንደር ባለፉት አራት ዓመታት ለዉጥ አሳይታለች። በዳግም ምርጫዉም ተጨማሪ ልማት ተስፋ ያደርጋሉ።»

ከድጋፍ ትችቱ ባሻገር ግን የኦባማ ቀጣይ የአራት ዓመት የሥራ ዘመን ካለፈዉ ይበልጥ ፈታኝ እንደሚሆን ተገምቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ ዘገባዎች አሳይ