1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦባማ ጉብኝት ሕንድና ፓኪስታን

ሰኞ፣ ጥቅምት 29 2003

ሙባይና ደልሒ ላይ ያሉ-ያደረጉት፣የሚሉ-የሚያደርጉት ኢስላም አባዶችን አስቆጥቶ፣ካቡል ላይ ያነጣጠረዉን የዉጪ መርሐቸዉን እንደ ሐገር ዉስጡ እንዳያጠወልገዉ-ነዉ የቅርቦቻቸዉ ሥጋት-የሩቆቻቸዉ ትዝብት

https://p.dw.com/p/Q1kH
ኦባማና ሲንጌሕምስል AP

ከግዛት-ግዛት ባባተላቸዉ የምክር ቤት የምርጫ ዘመቻ እንደላተቱ፣ጎምዛዛዉን ሽንፈት-ዋሽንግተን ላይ ጨልጠዉ በሳልስቱ ሙባይ ገቡ።ፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ።የምርጫ ዘመቻ ልፋት-ድካማቸዉን ለድቀት፣ ፓርቲያቸዉን ለሽንፈት የዳረገዉ ብዙዎች እንደመሰከሩት የሐገር ዉስጥ በጣሙን የምጣኔ-ሐብት መርሐቸዉ በጎ ዉጤት መጫጫት ነዉ።ከቅዳሜ-እስከ ዛሬ ሙባይና ደልሒ ላይ ያሉ-ያደረጉት፣የሚሉ-የሚያደርጉት ኢስላም አባዶችን አስቆጥቶ፣ካቡል ላይ ያነጣጠረዉን የዉጪ መርሐቸዉን እንደ ሐገር ዉስጡ እንዳያጠወልገዉ-ነዉ የቅርቦቻቸዉ ሥጋት-የሩቆቻቸዉ ትዝብት። የኦባማን ጉብኝት አለማ፣ የሥጋት ትዝብቱን ምክንያት ላፍታ እንቃኛለን አብራችሁኝ ቆዩ።

ጉብኝቱ ሕንድ-።አላማዉም በጥቅል-አገላለፅ የሁለቱን ሐገራት ግንኙነት ማጠናከር የሚል ነዉ።መልዕክት-ጥያቄ መልሱ የደመቀዉ ግን-ለፓኪስታንና ሥለ-ፓኪስታን ነዉ።

«እና በፓኪስታኖች በራሳቸዉ ድንበር ዉስጥ የአሸባሪዎች (አደጋ) ሥጋት መኖሩን የፓኪስታን መንግሥት እንደሚያዉቀዉ መናገር እችላለሁ።ምናልባት ከየትኛዉ ሐገር ይበርልጥ በርካታ ፓኪስታናዉያን ፓኪስታን ዉስጥ በአሸባሪዎች ተገድለዋል።አሸባሪዎችን መዋጋቱ ግን የምንጠብቀዉን ያሕል ፈጣን አይደለም»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ።ቅዳሜ።ሙምባይ።

እርግጥ ነዉ-አለም አቀፉ የፀረ-ሽብር ዘመቻ ከታወጀ ከ2001 ጀምሮ-ለአሸባሪዎች ቦምብ-ጥይት ፓኪስታን የገበረችዉን ያክል ሰላማዊ ሰዉ የገበረ ሐገር የለም።የዚያኑ ያክል በርካታ አሸባሪዎችን በተለይ የአል-ቃኢዳ መሪዎችን በመግደል በማሰር፥ ለዩናይትድ ስቴትስ አሳልፎ በመስጠት ፓኪስታን የሚወዳደር ሐገር የለም።

Barack Obama am Mahnmal für die ermordeten der terroristischen Angriffe vom November 2008
ኦባማ-በአሸባሪዎ ሰለቦች መታሰቢያምስል AP

ፕሬዝዳት ኦባማ የመጀመሪያዉን እንጂ ሁለተኛዉን አልጠቀሱትም።ያለመጥቀሳቸዉ ምክንያት በርግጥ እንዳሉት በፓኪስታን የፀረ-ሽብር ዘመቻ ጥረት ዉጤት ባለመርካታቸዉ ወይም ሕንዶችን እንዳማያስደስት አዉቀዉ ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።የኦባማ-ገሚስ አስተያየት ግራ-ማጋባት ከዚያዉ ከሙባይ ጥያቄ ማስነሳቱ ግን አልቀረም።

ኦባማ ከሙባይዋ ተማሪ ጋር ሲወያዩ-ጠየቀች-አንዷ

«እርስዎን የምጠይቀዉ ፓኪስታን ለዩናይትድ ስቴትስ ይሕን ያክል አስፈላጊ ተባባሪ የሆነችበት ምክንያት ምንድ ነዉ።ለምንድነዉ ዩናይትድ ስቴትስን ፓኪስታንን በአሸባሪ ደጋፊነት ያልፈረጀቻት።»

በዩናይትድ ስቴትስ ብያኔ መሠረት ኩባ፥ ኢራን፥ ሶሪያ እና ሱዳን አሸባሪዎችን የሚደግፉ ሐገራት ወይም መንግሥታት ናቸዉ።ኦባማ እንዳሉት ፓኪስታን ዉስጥ ከየትም ሐገር የበለጠ ሰላማዊ ሰዉ በአሸባሪዎች ከተገደለ፥ የፓኪስታን መንግሥት አሸባሪዎችን ለመከላከል ማድረግ የሚገባዉን ያክል ካላደረገ ፓኪስታን ከአራቱ ሐገራት የምትለይበት ምክንያት ቢያንስ በምክንያት ማመን ለምትፈልገዉ ለሕዳዊቷ ወጣት ግልፅ አይደለም።

ብቻ ፕሬዝዳንቱ መልስ-የሚሉት ነገር አላጡም።

«ደሕና የለም--የለም ጥሩ ጥያቄ ነዉ።እጠብቀዉ እንደነበርም ማመን አለብኝ።---ከተረጋጋች፥ ከበለፀገችና ከሰላማዊት ፓኪስታን ባለፍ የምንሻዉ የለም።ሐገሪቱን ሙሉ በሙሉ ሊያቀጣጥል የሚችለዉን እኛ እንደነቀርሳ የምናየዉን ይሕ ፅንፈኝነት-ለማጥፋት ከፓኪስታን መንግሥት ጋር እንሰራለን።»

እና ከተማሪዎቹ ጋር ሙዚቃ-ጭፈራዉ ቀለጠ።

ከባለሥልጣናት ጋር ዉይይት-ጉብኝቱም ቀጠለ።የኢስላማባዶች ጆር አይን ደልሒ-ሙባይ እንደተንጠለጠ ነዉ።ኦባማ ከምረጡኝ ዘመቻቸዉ ጊዜ ጀምሮ እንዳሉት ከመንግሥታቸዉ የዉጪ መርሕ ቀዳሚዉ አፍቃኒስታንና ፓኪስታን ዉስጥ የመሸጉ አሸባሪዎችን ማጥፋት ነዉ።ፓኪስታንን ሳይዙ ይሕን ማድረግ እንደማችሉ ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።

በዚሕም ሰበብ የሕንድ ጉብኝታቸዉን ካሰቡበት ጊዜ ጀምሮ በቀጭን ክር ላይ መረማመድ እንዳለባቸዉ አላጡትም።የፓኪስታን ጉዳይ አዋቂዎች እንደሚሉት ኦባማ በተለይ ሕንድ ላይ ቆመዉ ሥለ ፓኪስታን ያሉትን መጥፎ በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፈዉ የፓኪስታን መንግሥት አለባብሶ ያልፈዉ ይሆናል። ፅንፈኞችን ይደግፋሉ የሚባሉት ወይም በዩናይትድ ስቴትስና በመንግሥታቸዉ መርሕ ብዙም የማይደሰቱት የፓኪስታን የጦርና የሥለላ ባለሥልጣናት ወይም ፖለቲከኞች ግን መንግሥታቸዉን ለማጥላያ፥ ሕዝቡን ለማነሻሻነት አይጠቀሙበትም ማለት ጅልነት ነዉ።

የፓኪስታን የዉጪ ጉዳይና የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትሮች ገና ከጉብኝቱ በፊት ባወጡት መግለጫም ኦባማ ለሕንድ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት እንዳይከጅሉ አስጠንቅቀዋል። በተለይ ሕንድ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት የምታደርገዉን ጥረት ኦባማ ከደገፉ «የአካባቢዉን ፀጥታ» ያዉካል በማለት አስጠንቅቀዋል።

የሕንድ መንግሥት የቀድሞ የፀጥታ ብራጃሽ ሚሽራ እንደሚሉት ደግሞ ሕንድ የምትፈልገዉ ዩናይትድ ስቴትስ ፓኪስታንን እንድታወግዝ ነዉ።

«የኛ ትልቅ ችግር ከፓኪስታን የሚመነጨዉ አሸባሪነት መሆኑን ከዚሕ ቀደም ለዩናይትድ ስቴትስ በተደጋጋሚ ተናግረናል።ፓኪስታን መንታ ጨዋታ-እየተጫወተች መሆንዋን ዩናይትድ ስቴትስ ቢያንስ አሁን ትገዘበዋለች ብዬ እገምታለሁ።»

ከአጣብቂኙ ለመዉጣት ኦቦማ የምጣኔ ሐብት ትብብር፥ የፀረ-ሽብር ትግል፥ የቴክኖሎጂ ልዉዉጥ እያሉ በቀጭኑ ክር ላይ ሳይንገዳገዱ ለማለፍ እየሞከሩ ነዉ።ግን ሁለቱን ሐገራት ለዘመናት የሚያናጨዉን የካሺሚርን ጉዳይ ሊያልፉት አልቻሉም።ችግሩን ለማስወገድ አሜሪካ ትረዳችኋለች ማለታቸዉ ከሕንድ ቀዝቃዛ መልስ ሲያገኝ፥ ሕንድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ለመሆን ፍላጎትዋ ኦባማ ለሰለስ ያለ ድጋፍ ማሳየታቸዉ የፓኪስታንን ብቻ ሳይሆን የቻይናንም አይን-ጆሮ አቁሟል።

ከአዲሲቱ ሰፊ ሐገር ወደ ጥንታዊቱ ንዑስ ክፍለ-ዓለም መጀመሪያ የተጓዘዉ ሰዉ የተጓዘበት መንገድ ወጪ፣ ዘመን፣ ምክንያቱ አይደለም ማንነቱም በግልፅ አይታወቅም።በተቃራኒዉ ግን እስከ 1940ዎቹ ማብቂያ ድረስ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የንዑስ ክፍለ አለሚቱ ግማደ ግዛት የነበረችዉ የዛሬዋ ባንግላዴሽ ተወላጅ እንደሆነ የሚታመነዉ ስዋሚ ቪቬካናንዳ አሜሪካን የረገጠ የመጀመሪያዉ ሕንዳዊ ነዉ።

የምሥራቆችን ፍልስፍና በጣሙን የቬዳንታ እና የዮጋ ጥበብ-ባሕልን ለአሜሪካኖች ያስተዋወቀዉ ቪቬካናንዳ በአዉሮጳ አቋርጦ በ1893 ቺካጎ እኪገባ ድረስ የእንግሊዝ ቅኝ ፤ ባብዛኛዉ የእንግሊዝ ዉልዶች የነበሩት-አሜሪካኖች የእንግሊዝ ቅኝ ሥለነበረችዉ ትልቅ፣ጥንታዊ ዉብ ሐገርና ሕዝብ የሚያዉቁት ምንም ወይም ትንሽ መሆኑ በርግጥ ፈገግ-ደግሞም ግር ያሰኛል።

ቪቬካናንዳ የአንድ ሐገር ተገዢ ግን የማይተዋወቁ የሩቅ ለሩቅ የአዲስ-የጥንት ትላልቅ ስልጣኔ ትላልቅ ሐገሮችን ባስተዋወቀ በስልሳ-ስድስተኛዉ አመት ዋሽንግተኖች ፈላጊ-ኒዉ ደልሒዎች ተፈላጊ ሆኑና ፕሬዝዳንት ደዊት አይዘናወር ሕንድን ለመጎብኘት ኒዉ ደልሒ-ገቡ።ታሕሳስ 1959።ጉብኝቱ የአዲሲቱ ነፃ ሐገርና የአዲሱቱ ልዕለ ሐያል ሐገርን ግንኙነት ማጠናከሩን የተጠራጠረ አልነበረም።

ይሁንና ሕንድ የኮሚንስት ቻይናን ተፅዕኖ እንድትገታ አይዘናወር ላቀረቡት ጥያቄ-የሕንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ጃዋሐር-ላል ኔሕሩ ቀዝቃዛ መልስ መስጠታቸዉ አይዘንአወር አናዶ-ኒዮርክ ታይምስ ያኔ እንደዘገበዉ ለዛቻ ጋበዛቸዉ።«ኮሚንስት ቻይናን ከሕንድ ጋር ተባብረን ለመግታት የሚያስፈልገን፣ የኔሕሩ ፍቃድ ሳይሆን-የሕንድና የአሜሪካ ሕዝቦች ጠንካራ ግንኙነት ነዉ።» አሉ-የጥንቱ ባለ አምስት ኮኮብ ጄኔራል-የያኔዉ ፕሬዝዳንት።

የመጀመሪያዉ የመሪ ጉብኝት የሁለቱ ሐገሮች አዲስ ግንኙነት ወዳጅነትን-ከዛቻ የተቃርኖ መልዕክት የቀጠ-የጥንቱን አስፈጋጊ-አደናጋሪ እዉነት የሚያጅብ አዲስ ግርምት አተረፈ። አይዘናወር ሕንድን ጎብኝተዉ እንደ ቀድሞ ጄኔራል-እንደ ሐገር መሪም የኮሚንስቶችን ሐይል-በሐይል የመመከትን አስፈላጊነት ተናገረዉ ዋሽንግተን በተመለሱ በሰወስተኛዉ ወር አሜሪካዊዉ የመብት-እኩልነት ሰላማዊ ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ትንሹ የመሐተመ ጋንዲን የሰላማዊ ትግል ፍልስፍናን ለመማር ሕንድ ሔዱ።የካቲት-1959።

የአይዘናወር ጉብኝት-መልዕክት እና የኪንግ ጉብኝት አላማ ተቋርኖ የአዲሲቱን ልዕለ-ሐያል ሐገር የጦር ሐይል-የሰላማዊ ትግል ስብጥር ፍልስፍናን አጣምሮ የመያዙ ሐቅ ለያኔዉ አስተንታኝ አስደማሚ አይነት ነበር።ዛሬ ግን አንዱ መሪ ፕሬዝዳት ኦባማ የድሮዎቹን ሁለቶች-ሁለት ተቃራኒ መልዕክት ከሙባይ አሰሙ።

ከሁለት አመት በፊት ከፓኪስታን ሰርገዉ የገቡ አሸባሪዎች ለገደሏቸዉ ሰዎች የተሠራዉን መታሰቢያ ሲጎበኙ-በቦምብ ጥይት ሰዉ የሚገድሉ አሸባሪዎችን በሐይል እንደሚወጉ አስታወቁ።

«ከነዚያ ከሁለት አመት በፊት ከነበሩት አሰቃቂ ዕለታት ወዲሕ ታጅ (መሐል) ለሕንድ ሕዝብ የጥንካሬና የፅናት ምልክት ነዉ።እና አዎ! እዚሕ በምናደርገዉ ጉብኝት ለሕዝቦቻችን አሰተማማኝ ደሕንነትና ብልፅግናን ለማጎናፀፍ ሕንድና ዩናይትድ ስቴትስ በጋራ እንደሚቆሙ ሥለመወሰናችን ግልፅ መልዕክት ለማስተላለፍ ነዉ»

አይዘናወርን መሰሉ።እዚያዉ ሙባይ የጋንዲን መታሰቢያ ሲጎበኙ ደግሞ በክብር መዝገቡ ላይ እንዲሕ ፃፉ። «ይሕን የጋንዲን ሕይወት የሚገልፀዉን መታሰቢያን የየመልከት ክብር ሳገኝ በታላቅ ተስፋና መንፈስ እሞላለሁ።(ጋንዲ) ጀግና ነበሩ።ለሕንድ ብቻ ሳይሆን ለመላዉ አለም ጭምር»

የኦባማ መልዕክት የሰላማዊ ታጋዩ፥ የእኩልነት ተሟጋቹን የማርቲን ሉተር ኪንግን መሰለ።የነጭ-ጥቁር ክልሱ ፕሬዝዳንት ባንዴ-ባንዲት ከተማ ሁለቱን ተቃራኒዎች አሉ-አደረጉትም።

ሕንድ የገለልተኞች ንቅናቄ የተሰኘዉ ማሕበር መስራች አባል ናት።ኮሚንስትም አይደለችም።ግን ጠላትዋ ፓኪስታን የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ እንደነበረች ሁሉ እሷም የሶቬት ሕብረት የቅርብ ወዳጅ ነበረች።

ሕንድና ፓኪስታን በ1965 እና በ1971 ሲዋጉ ዩናይትድ ስቴትስ ሁለቱን ሐገሮች ከመሸምገል ይልቅ ፓኪስታንን እየረዳች ሕንድንም ላለማጣት መሸነጋገሏ ለሰወስቱም ሐገራት አልበጀም።ሁለተኛዉ ጦርነት በተደረገበት በ1971 ሕንድን የጎበኙት ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ሕንዶችን ከሚያስጨንቀዉ ጦርነት ይልቅ የቻይናን ተፅዕኖ በተለይም ለቬትናሙ ዘመቻ የሕንድን ድጋፍ መጠየቃቸዉ የምሩ ሁነት አስፈጋጊ ክስተት ለማያጣዉ ለሁለቱ ሐገራት ግንኙነት ሌላ አስደማሚ ሐቅ ነበር።

Obama in Indien Parade Flash-Galerie
ምስል AP

በ1998 መጀመሪያ፥-ሕንድ አከታትላ ፓኪስታን የኑክሌር ቦምብ በመሞከራቸዉ ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ በሁለቱም ሐገራት ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጣሉ።በሁለተኛዉ አመት ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ሕንድን ጎበኙ።ከሕንድ ጋር የኢኮኖሚና የምጣኔ ሐብት ትብብር ተፈራረሙ።የኢኮኖሚ ማዕቀብና የኢኮኖሚ ትብብር።አስገራሚ-ግራም ነዉ።ግን ሆነ።

ዩናይትድ ስቴትስ በ2001 በአሸባሪዎች ከተመታች በሕዋላ የፕሬዝዳት ጆርጅ ቡሽ መስተዳድር በሕንድም በፓኪስታንም ላይ ተጥሎ የነበረዉን ማዕቀብ አንስቶ-አስነስቶ ከሕንድ ጋር ጠንካራ ግንኙነት-ከፓኪስታን ጋር ደግሞ ጠንካራ ትብብር ፈጥሯል።ቡሽም ሕንድን ጎብኝተዉ ሁለቱ ሐገሮች የኑክሌር ቴክኖሎጂ እንዲለዋወጡ ተዋዉለዋል።

ዛሬ ከሁለት ሚሊዮን ሰባት መቶ ስልሳ-አምስት ሺሕ በላይ ሕንዶች ወይም የሕንድ ዝርያ ያላቸዉ ሰዎች አሜሪካ ዉስጥ ይኖራሉ።ሕንድ ዉስጥ ስልሳ ሺሕ አሜሪካዉን አሉ።ሁለቱን ተጎራባች-በላኑክሌር ጠላቶችን እኩል ወዳጅ ለማድረግ በሚሻዉ የዋሽግተን መርሕ-የሚዘወረዉ የመንግሥታት ግንኙነት ግን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ያክል- አልጠነከረም።በነገራችን ላይ ፕሬስ ትረስት ኢንዲያን ከማለለዉ አንዱ የኦባማ ጉብኝት በየቀኑ ሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር መዉጣቱ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ