1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦባማ ጉብኝት እና የአፍሪቃውያን ስሜት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 22 2007

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በአፍሪቃ ያደረጉትን የአምሥት ቀናት ጉብኝት አጠናቀዉ ትናንት ወደሀገራቸዉ ተመስልሰዋል። ከኬንያዊው አባት የሚወለዱት አሜሪካዊ ፕሬዝደንት ስልጣን ሲይዙ መላዉ አፍሪቃ ዐይኑን በተስፋ ጥሎባቸዉ ነበር።

https://p.dw.com/p/1G76U
Kenia USA Rede Präsident Barack Obama in Nairobi
ምስል Reuters/J. Ernst

[No title]

የዶይቸ ቬለው ዳንኤል ፔልስ እንደሚለው፣ የባራክ ኦባማ የምስራቅ አፍሪቃ ጉብኝት ማንኛውንም የውጭ ጉዳይ መምህር የሚያኮራ ነው። ኦባማ መጡ፤ ተመለከቱ ባሉበትም ሆነው ትክክለኛውን ነገር ተናገሩ። ለስለስ ብለውም የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ እንዲከበር ጥሪ አቀረቡ፤ የሲቪክ ማህበራት እውነታንም ተናገሩ። አፍሪቃ ችግሮቿን መፍታት ትችላለች ሲሉም ሰበኩ። ፕሬዝዳንቱ ከኢትዮጵያና ኬንያ ጋር የጸጥታና የንግድ ግንኙነት የማሳደግ ሃሳብም አላቸው።

ኤርፎርስ ዋን ወደ ዋሽንግተን ጉዞ ሲጀምር እና የናይሮቢ ጎዳናዎች ወደ ቀደመው ህይወት ሲመለሱ ግን አንድ ነገር ግልጽ ሆነ። በኦባማ መምጣት የተፈጠረና የሚፈጠር ቅጥ ያጣ የደስታ በሽታ የለም፤ አልነበረምም። በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ.ም. የኖቤል የሰላም ተሸላሚዉ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች አቀንቃኙ በመድረኩ የሉም። አሁን የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ የፖለቲካ የመጨረሻ ግብ ስልጣን መሆኑን አምነው የሚያራምዱ ቦታውን ተረክበዋል። ኦባማ የስልጣን ዘመናቸውን አጠናቀው በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ዋይት ሐውስን ሲለቁ መላዉ ዓለምም ሆነ አፍሪቃ ችግራቸው ተቀርፎ ምቹ አይሆኑም።

ፕሬዝዳንቱ ኬንያውያን የጎሳ ፖለቲካን እንዲያስወግዱ ሙስናን እንዲታገሉ ያቀረቡት ጥሪ የትም አያደርስም። ኬንያውያን አገራቸውን ከሚጎበኙ የውጭ አገር ሰዎች ይህን መሰሉን ጥሪ እና መሪዎቻቸውም የሚገቡላቸዉን ቃል ማመን ካቆሙ ሰነባብተዋል። በእርግጥ ኬንያውያን እንዲህ አይነቶቹን ጥሪዎች ማድመጥ አይፈልጉም፤ እዉነቱን ለመናገር እነሱ ራሳቸዉ ሊኖሩባት ስለሚፈልጓት አገራቸው ጥርት ያለ ህልም አላቸው። እነሱ ያጡት እነዚህን ተግባራዊ የሚያደርጉ ፖለቲከኞች ነው። እንዲህ አይነት ጉብኝቶች እና ንግግሮች የተሻለች ኬንያን አይፈጥሩም።

ባራክ ኦባማ አባታቸው በተወለዱባት አገር ለውጥ ማምጣት ከፈለጉ ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ባልተባበሩ ነበር። ሁለቱ ሰዎች ዓለም አቀፉ የወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓ.ም. የተከከሰተውን የጎሳ ግጭት በማቀነባበር ከከሰሳቸው ሰዎች መካከል ይገኙበታል። የደህንነትና የንግድ ግንኙነቱን እያስቀጠሉ ስለለውጥ መናገር የትም አያደርስም። በሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚታወቁትን የኬንያ የደህንነት ሃይሎች መርዳት ፕሬዝዳንቱ ያሰሙትን ማሳሰቢያም ተዓማኒ አያደርገውም።

ከወሬ ያልዘለለ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት

በፕሬዝዳንቱ ዓላማ እና በአሁኑ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ፖሊሲ መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳየት ኬንያ የማትበቃ ከሆነ፤ ኢትዮጵያም አለች። ኦባማ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ ሁሉንም የምክር ቤት መቀመጫ የተቆጣጠረባትን አገር ጎብኝተዋል። የፕሬስ ነጻነት የከፋ ስጋት የተደቀነበት፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጸጥታ ሃይሎች የሚዋከቡባት -ኢትዮጵያ። ባራክ ኦባማ ሁሉን ኢትዮጵያውያን የሚያሳትፍ የፖለቲካ ምህዳር እንዲኖር፤ የፕሬስ ነጻነት እና ሰብዓዊ መብቶችም እንዲከበሩ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚያም በጎረቤት ሶማልያ ካለው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አሸባብ ጋር ለሚደረገው ፍልሚያ ከኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ጋር ያለውን ትብብር ለማስቀጠል ተስማምተዋል።


ይህ ለኢትዮጵያ መንግስት መልካም ዜና ነው። አገሩ ላይ አሸባብ የደቀነበትን ስጋት ለመከላከል ለሚፈልግ አሜሪካዊ ፕሬዝዳንትም ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ነገር ግን በዚሁ የጸጥታ ኃይል ከፍተኛ ጫና ለሚደርስባቸዉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎችና ሲቪል ማህበረሰብ የሚያስተላልፈዉ መልዕክት እንዴት ያለ ይሆን?

በአፍሪቃ ህብረት ባደረጉት ማራኪ ንግግር ባራክ ኦባማ ውስጣቸው የተቀበረዉን የተስፋ ነጸብራቅ አሳይተዋል። ፕሬዝዳንቱ የአፍሪቃ መሪዎች የስልጣን ዘመናቸውን አክብረው እንዲወርዱ ሲወተውቱ ታዳሚዎቻቸው በአድናቆት አጨብጭበዋል። ከዋይት ሃውስ ውጪ ለሚጠብቃቸው ህይወት ምን ያህል እንደ ጓጉ አፅንኦት ሲሰጡና ሙስናን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለማጥፋት ሲወተውቱም ታዳሚዎቻቸዉ በአክብሮት አድምጠዋቸዋል።

ነገር ግን አፍሪቃን ለመቀየር ከቃላት ጨዋታ ይልቅ ተግባርን ይጠይቃል። እዉነት ባራክ ኦባማ ለአባታቸው የትውልድ አህጉር ለውጥ ማምጣት ከፈለጉ ትኩረታቸውን ወደ አፍሪቃ አስተዳደር ፖሊሲዎች ለመቀየር መወሰን ይኖርባቸዋል። አሁን የተከተሉት አካሄድ አፍሪቃን የተሻለ አያደርጋትም።

ዳንኤል ፔልስ/እሸቴ በቀለ

Pelz Daniel Kommentarbild App
ዳንኤል ፔልስ በዶይቼ ቨሌ የአፍሪቃ እንግሊዝኛ ክፍል ኃላፊ

ሸዋዬ ለገሠ