1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከባቢ አየር ለዉጥ በኤኮኖሚ ላይ ያለዉ ተፅኖ

ረቡዕ፣ ኅዳር 15 2008

የዓለም አቀፉን የአየር መዛባት አስመልክቶ በሚቀጥለው ሳምንት በፓሪስ ላይ በሚከፈተው ጉባዔ የሚቀርቡ በርካታ ጥናቶች ይፋ ሆነዋል። በየጊዜው እየጨመረ የሚሄደው የከባቢ አየር ሙቀት በዚሁ ከቀጠለ -ብዙዎቹ አንድ ቀን መመለሻ የሌላው ችግር ውስጥ እንደሚጥል የማይቀር ነገር ሲሉ ስጋታቸዉን ይገልፃሉ።

https://p.dw.com/p/1HCcP
Deutschland Atomkraftwerk Gundremmingen
ምስል Imago/Eibner

ይህን አስተያየት ከሚሰጡት መካከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይገኝበታል። የብርታኒያው የካምብርጂ ተቋምም ሌላው ነው። በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚያም ተነስተው ትላልቅ የእንዱስትሪ አገሮችና ታዳጊ መንግሥታት፣ በተለይ ደግሞ እንደ ቻይና እና እንደ ሕንድ ያሉ አገሮች የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን ሳይረፍድ እንዲቀይሩ ጠይቀዋል።

ችግሩ ያለው በጢስ ወለዱ የኢኮኖሚ ዕድገት እና በትርፍ አምጪው እንዲስትሪና ፋብሪካዎች ላይ የተመሠረተ ነው። እሱን ደግሞ ለማገድም ሆነ ለመቆጣጠር ጉዳዩ ውስብስብ ስለሆነ አስቸጋሪ ነው።

USA Dr. Scott Kelly
ዶክተር ስኮት ኬሊምስል privat

በሌላ በኩል ከጥፋት ለመዳን የቀረው ጊዜ ብዙዎቹ እንደሚሉት ቢበዛ ሃያ ስምንት ዓመት ነው። ይህ ሲታሰብ አጭር ጊዜ ነዉ። እንግዲህ እሰከ አሁን ድረስ በተያዘው አካሄድ ሁሉ ነገር ከቀጠለ፣ በረዶዎች አለጥርጥር ነገ ይቀልጣሉ፣ደሴቶች ይሰምጣሉ፣ድርቅ በያለበት ተስፋፍቶ ምግብ ያጥራል፣በሽታ ይስፋፋል፣ቃጠሎ አሁን ከምናየውና ከምንሰማው ይበዛል፣ንፋስና ማዕበል፣ሞገዶች ተነስተው ሰውንና መሬቱን ይመታሉ። በአንዳንድ አካባቢም ዝናቡ ተጠናክሮ ጎርፎች መንደሩን ጠራርገዉ ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትሉ አይቀርም ። በሌላ አካባቢ ጠበብቶች እንደሚሉት መጠጥ ንፁሕ ወኃ እጦት ግጭት ይቀሰቅሳል። እነዚህን ሁሉ ተከትሎ ደግሞ ሞት ወይም ስደት በዓለም ላይ ይስፋፋል። ወደ አርባ ሺህ የሚጠጉ፣ፓለቲከኞችና ሳይንቲስቶች፣ ጋዜጠኞችና ታዛቢዎች፣ በፓሪሱ የዓለም አቀፍ ጉባዔ ይገኛሉ ይጠበቃል።

ይልማ ኃይለ-ሚካኤል

አዜብ ታደሰ