1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ብክለቱን ምን አባባሰዉ? መፍትሄስ ይኖረዉ ይሆን?

ማክሰኞ፣ መስከረም 24 2009

ከዓለማችን ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነዉ ሕዝብ የዓለም የጤና ድርጅት ተገቢ ከሚለዉ የንፁሕ አየር ጥራት እጅግ ዝቅ ባለ እና የተበከለ አየር ባላቸዉ ከተሞች እንደሚኖር ይገልጻል።

https://p.dw.com/p/2Qrpk
Iran Teheran Stadtansicht
ምስል picture alliance/AP Photo/V. Salemi

የከተሞች የአየር ብክለት

የዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገዉ መረጃ በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2016 በመላዉ ዓለም በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች የአየር ብክለቱ ከፍ ማለቱን አመልክቷል። በዚህ ዘገባ መሠረትም የምድራችን አየር መበከል መጨመር የሰዎችን ለተለያዩ የመተንፈሻ አካላት የጤና እክሎች የመጋለጥ ሁኔታ ያባብሳሉ።

«በምድር ላይ ከሚከናወነዉ መለኪያ በተጨማሪ የሳይተላይት መረጃዎች ያጣመረ አዲስ ስልት ነዉ የተጠቀምነዉ፤ በዚህ አማካኝነትም ነዉ ለመጀመሪያ ጊዜ መላዉን ዓለም ያካተተ የሰዉ ልጅ ምን ያህል ለአየር ብክለት ተጋልጧል የሚለዉን የመለካት ተግባር ያከናወነዉ።  ይህም ከ90 በመቶ የሚበልጠዉ የዓለም ሕዝብ ለተበከለ አየር የተጋለጠ መሆኑን ይፋ አድርጓል።»

ይላሉ የዓለም የጤና ድርጅት ዉስጥ በዚህ ዘርፍ የሚሠሩት ሳይንቲስት አኔት ፕሩስ ኢዉስተን። እሳቸዉ እንደገለጹትም ይህ ደግሞ እጅግ አሳሳቢ እና አስጊ ነዉ። የተበከለ አየር በየዕለቱ ለመተንፈስ መጋለጣቸዉም በጤናቸዉ ላይ የሚያስከትለዉ የራሱ የሆነ መዘዝ ይኖረዋል። ባለሙያዋ አክለዉ እንደገለፁልን የአየሩ የጥራት የደረጃ የተለካዉ በአምስት ለዚሁ ጥራት ማሳያ በሚዉሉ አምስት ረቂቅ ስልቶች አማካኝት ነዉ። የብክለቱ መጠን ከፍ ብሎ መታየቱ በአሁኑ ወቅት የአየር ብክለቱን ሊያባብስ የቻለ ነገር በመኖሩ ሳይሆን ይላሉ ሳይንቲስቷ፤ የተካሄደዉ ምርምርና የመለካቱ ሂደት ይበልጥ ጥልቅ በመሆኑ ነዉ። ቀጠሉ፤

«በመጀመሪያ ይህ አዲስ ቅኝት እና እጅግም ጥልቅ ነዉ። ብክለቱ ይህን ያህል ደርሷል የሚለዉ የሚያሳየዉም በዝርዝር በመመርመሩ የተገኘ ዉጤት እንጂ የግድ የአየር ብክለቱ በመላዉ ዓለም ጨምሯል ማለት አይደለም። እርግጥ ነዉ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት ብክለቱ መጨመሩን እናያለን፤ በተቃራኒዉ ደግሞ ከፍተኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት ብክለቱ ቀንሶ ነዉ የሚታየዉ።»

አኔት ፕሩስ ኢዉስተን እንደሚሉት የአየር ብክለቱ መንስኤ የሆኑት ምንጮች እንደየአካባቢዉ ይለያያሉ። በአጠቃላይ ግን በዋናነት ለብክለቱ አስተዋፅኦ የሚያደርጉት፤ ኢንደስትሪዎች፤ እንዲሁም የኢንደስትሪ ምርቶች፤ የኃይል ማመንጨት ሂደት፤  የተሽከርካሪዎች ብዛት፤ ሲሆኑ የቤት ዉስጥ የኃይል አጠቃቀምም የራሱ የሆነ የብክለት ድርሻ እንዳለዉም ይዘረዝራሉ። የቤት ዉስጥ የኃይል አጠቃቀም ሲባል ይላሉ ተመራማሪዋ፤

«ለምሳሌ ምግብ ለማብሰልም ሆነ ቤትን ለማሞቅ የሚዉሉ ተቀጣጣይ የኃይል ምንጮች፤ እነዚህ ቀደም ሲል የተዘረዘሩት ናቸዉ ዋናዎቹ ለአየር ብክለት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ስልቶች። በአንዳንድ አካባቢ ደግሞ በተፈጥሮ ያለዉ አቧራ እራሷ ለብክለት መንስኤ ነዉ።»

Nepal Atemschutzmasken in Kathmandu
ምስል picture-alliance/dpa/N. Shrestha

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተዉ በሚታየዉ የአየር ብክለት መላዉ የዓለም ሕዝብ የሚጎዳ ቢሆን በይበልጥ ግን አነስተኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት ከመቶ ሺህ የሚበልጡ ነሪዎችን በያዙ ከተሞች የሚኖሩ ወገኖች ለከፍተኛ የአየር ብክለት ችግር የተጋለጡ ናቸዉ።

«አዎ በዓለም ለዚህ የተጋለጡ አካባቢዎች አሉ በተለይም እስያ እና አፍሪቃ ዉስጥ በይበልጥ ተጽዕኖዉ የሚጠናባቸዉ አሉ። የአየር ብክለቱ ከፍተኛ ገቢ ካላቸዉ ሃገራት ይልቅ በእነዚህ አካባቢዎች በጣም ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ፈሳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮችን ለቤት ዉስጥ አገልግሎት በብዛት ጥቅም ላይ ይዉላሉ፤ የኢንዱስትሪ ምርቶች የሚያስከትሉትን ብክለት ለመቆጣጠርም ሆነ ለመቀነስ ሥራ ላይ መዋል የሚገባዉ የቁጥጥር ሥልት ከፍተኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት ጠንካራ ሲሆን፤ ባጠቃላይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት ደካማ መሆኑ፤ ለምሳሌ ከተሽከርካሪዎች የሚመጣዉ የብክለት መጠን፤ አዉሮጳ እና ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ስንመለከት ፤ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ ሃገራት ይልቅ በጣም ጥብቅ  ነዉ። እናም ይህ የሚያሳየዉ በአንዳንድ የዓለማችን ክፍል ኢንዱስትሪዉን የማስፋፋቱ ነገር ሊደረግ የሚገባዉ ቁጥጥርና ክትትል ሥራ ላይ እንዲዉል ሆኖ አለመቀናጀቱን ነዉ። ይህ ነዉ ዋናዉ ምክንያት።»

የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ ያደረገዉ መረጃ ያተኮረዉ ከተሞች ላይ ይመስላል። የገጠሩስ አካባቢ ከአየር ብክለቱ ምን ያህል የጸዳ ይሆን?

«ይፋ ያደረግነዉ የአየር ሽግግርን የሚያሳየዉ መረጃ በተለይ ሊያስከትል የሚችላቸዉ በሽታዎች ስጋት የገጠሩንም ክፍል ያጠቃልላል። ምናልባትም አንዳንዶች ገጠራማዉ አካባቢ ይበልጥ ለብክለት የተጋለጠ ነዉ ብለዉ ሊያስቡ ቢችሉም ሁኔታዉ ግን ከከተማዉ የተሻለ ነዉ። ያም ሆኖ ግን እዚያም አለ፤ መንሴዉ ደግሞ በግንባር ቀደምትነት በከፍተኛ ደረጃ ለማብሰልም ሆነ ቤትን ለማሞቅ ጥቅም ላይ የሚዉለዉ ፈሳሽ ያልሆነ የኃይል ምንጭ እዚያ ስለሚጠቀሙ ነዉ። ይህ ደግሞ በመኖሪያ አካባቢዎች  በጣም ጥቅጥቅ ያለ ጭስ ያስከትላል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከከተማዎች አካባቢ የተበከለዉ አየር ወደ ገጠሩ ይሄዳል።»

China Müllverbrennung
ምስል picture alliance/dpa/Dong Mu

በአሁኑ ወቅት በመላዉ ዓለም የአየር ብክለት መንስኤ እና ያለበት ደረጃ ይህ በመሆኑም የብዙሃኑን ሕዝብ ጤና ሊያቃዉስ እንደሚችል ነዉ የተገለጸዉ። የልብ ሕመም፤ የደም ጭንቅላት ዉስጥ መፍሰስ፤ የሳንባ ካንሰር፤ እና ጠንከር ያለ የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚፈጠሩ የጤና እክሎች ለምሳሌ አስምን የመሳሰሉት፤ አየራቸዉ ክፉኛ በተበከለ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎችን እንደሚያሰጉ ከተዘረዘሩት በሽታዎች መካከልም ይገኙነታል። የአየር ብክለቱ እነዚህ በሽታዎች ጋር ስለሚኖረዉ ቀጥተኛ ግንኙነት አኔት ፕሩስ ኢዉስተን እንዲህ ይላሉ፤

«ትክክል ነሽ፤ ተፅዕኖ ከፍተኛ የሚሆነዉ በተለይ በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚከሰቱትን በሽታዎች ይመለከታል። እንዴት ነዉ በመተንፈሻ አካላት ላይ ተፅዕኖዉን የሚያስከትሉት የሚለዉ አሁንም በምርምር ላይ ያለ ጉዳይ ነዉ፤ ያም ሆኖ ግን ተፅዕኖ እንዳላቸዉ እና ያም ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የጭንቅላት ዉስጥ ደም መፍሰስ እንዲሁም የልብ ሕመም፤ ይኸዉም ቁስለት ሊሆን ይችላል፤ ወይም የዉጥረት አተነፋፈስ ፤ ወይም የደም ቧምቧዎች ሥራ መስተጓጎልና የመሳሰሉትን  ሊያስከትል እንደሚችል ግልፅ ነዉ። ይህ በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚፈጠር የመመረዝ ችግር ነዉ በሂደት ጭንቅላት ዉስጥ የደም መፍሰስንም ሆነ የልብ ሕመምን የሚመጣዉ።»

ተመራማሪዋ እንደሚሉት በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገራት ላለፉት 30 ዓመታት በየበኩላቸዉ የሚበክሉትን አየር ለማጽዳት የወሰዷቸዉ ጠንካራ ርምጃዎች አሁን ለሚታየዉ ዉጤት አብቅቷቸዋል። ጥናቱ እንዳመለከተዉም ከፍተኛ ገቢ ያላቸዉ ተብለዉ ከተመደቡት ከእነዚህ ባለ ከፍተና ኢንዱስትሪ ሃገራት ይልቅ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸዉ እና ኢንዱስትሪያቸዉን ለማስፋፋት የሚንቀሳቀሱት ሃገራት ከተሞች አየር በጣም የተበከለ ነዉ። ይህን ያስከተለዉ ደግሞ ይላሉ ባለሙያዋ፤

USA Schulbus in Los Angeles
ምስል Getty Images/D. McNew

«በርካታ ንፁሕ አየርን ማስገኘት የሚችሉ ርምጃዎች እና ብክለትን የሚያስቀንሱ እቅዶች ፤ ማለትም የኢንደስትሪ ብክለትን የሚገድቡ መመሪያዎች፤ ጽዱ የኃይል ምንጮችና የመሳሰሉትን ሥራ ላይ በማዋላቸዉ ነዉ። በተቃራኒዉ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸዉ ሃገራት ገና እንዲህ ያሉ መመሪያዎች የሉም።»

የአየራቸዉ ክፉኛ የተበከለ አካባቢዎች የሚባሉት የትኞቹ ይሆኑ?

«እንደሚመስለኝ በጣም የተበከለ አየር ያላቸዉ ሃገራት የሚገኙት እስያ ዉስጥ ነዉ። እስያ ዉስጥ በርካታ ሃገራት የአየር ብክለታቸዉ ከፍተኛ ነዉ። አዉሮፓ ዉስጥ ደግሞ በተለይ የምሥራቅ አዉሮጳ ሃገራት ይህ ችግር ይታይባቸዋል። አፍሪቃ ዉስጥ በየአካባቢዉ የአየር ብክለቱ ከፍተኛ ነዉ፤ በአንጻራዊ ደረጃ ከደቡብ አፍሪቃ በቀር፤ አፍሪቃ ዉስጥ ያለዉ ብክለት ሰዉ ሰራሽ ከሆነዉ ይልቅ የሚበዛዉ በአቧራ ምክንያት የሚመጣዉ ነዉ።»

በየአካባቢዉ የሚታየዉን የአየር ብክለት ለመቀነስም መደረግ የሚገባቸዉ ጠቃሚ ርምጃዎች አኔት ፕሩስ ኢዉስተን ዘርዝረዋል። በቅድሚያ በየቤቱ እንጨት ወይም ከሰልን ለማብሰያም ሆነ ለማሞቂያ ከመጠቀም ተላቆ ንፁሕ የኃይል ምንጭ የመጠቀም ዕድል መገኘት አለበት፤ በየኢንዱስትሪዉ ፅዱ የኃይል ምንጭ አማራጮችን ሥራ ላይ ማዋል፤ ታዳሽ የኃይል ምንጭን ማስፋፋት፤ መጓጓዥን በተመለከተ ደግሞ በግል መኪና ይልቅ የሕዝብ መጓጓዣን ማዘዉተር፤ አነቃቂ የሚባሉት መጓጓዣዎች ለምሳሌ ብስክሌት መጠቀም እንዲሁም በእግር መጓዝ በየደረጃዉ ሊተገበሩ የሚችሉ እንደሆኑ ጠቁመዋሉ።

 ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ