1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካርናቫሉ ድግስ እና የበርሊናለ 60 ኛ አመት

እሑድ፣ የካቲት 7 2002

የለቱ ዝግጅታችን በጀርመናዉያኑ ባህል ዙርያ ያጠነጥናል። ባለፈዉ ሃሙስ እዚህ በጀርመን ከቀኑ አምስት ሰአት ላይ የጀመረዉ የካርናቫሉ ፊየስታ እስከ መጭዉ ዕረቡ ይቀጥላል። በተለይ ራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት በኖርዝ ራይን ፊስት ፋልያ ግዛት የሚገኝ ህዝብ በናፍቆት የሚጠባበቀዉ በአሉ ነዉ፣ ሌላዉ ዘንድሮ የጀርመኑ ህገ መንግስት ስድሳኛ አመቱን ሲይዝ

https://p.dw.com/p/M0qu
ምስል AP

በበርሊን የተለያዩ የአለም አገራትን ፊልሞች በማምጣት የሚታወቀዉ በርሊናለ የተሰኘዉ የፊልም ማእከልም 60ኛ አመቱን በማክበር የበርካታ አገራት ፊልሞችን በአለም ዙርያ በፊልም ጥበብ፣ በፖለቲካ እንዲሁም በማህበራዊ ኑሮ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን በመጋበዝ ስድሳኛ አመቱን በማክበር ላይ ይገኛል፣ ዛሪ በባህል መድረካችን ሌላዉ የምናየዉ ርእሳችን ነዉ!
በአለማችን ዙርያ የሚነገሩ ሰላሳ ሶስት ቋንቋዎችን ይዞ የራድዮ ስርጭቱን በተለያዩ አገሮች የሚያስተናግደዉ ራድዮ ዶቸ ቬለ ባለፈዉ አርብ እለት እዚህ በኖርዝራይን ቪስት ፋልያ ግዛት ተወዳጅ የሆነዉን የካርናቫልን ፊየስታ አስተናግዶአል። ለነገሩ ሃሙስ የሚጀምረዉ በአልን ራድዮ ጣብያዉ አርብ ያደረገዉ አንድ የሳምንት መጨረሻ በመሆኑ ሌላዉ ድግሱን በስፋት ስላደረገዉ ጋዜጠኛዉ ምናልባት እንዳይዘናጋ ይሆን። ያ የኔ መላምት ነዉ። ግን የጣብያዉ ባልደረባ ቤተሰቡን ልጁን ጎረቤቱን ይዞ በአገራችን አባባል እብድ መስሎ ነበር ይታይ የነበረዉ ብል ማጋነን አይሆንብኝም። አንዷ የሙሽራ ቀሚስ ለብሳ ቀሚሱ ከኻላ የተቀደደ ይሆናል፣ ሌላዉ የወታደር ልብስ ለብሶ የፊቱን ገጽታ በጥላሸት ከንፈሩንም ደም አስመስሎ ተቀብቶ ይሆናል፣ የተቀዳደደ የተጻጻፈ ልብስ የተለመደ ነዉ፣ እንደዉ እብድ ሆኖ መታየት፣ አልያም ሰዉ አይን የሚገባ ነገር አድርጎ መገኘት ብቻ! እንደ ልዑላን አይነት አለባበስ የለበሱ የክብር ዘዉድ የደፉም የበአሉ ተካፋዩች ነበሩ። በሌላ በኩል አሳማ፣ የጦጣ የዉሻ ምስል ያለበት ጨንበል ያጠለቁም አልጠፉም! ብቻ ይህ ሁሉ ተደምሮ የበአሉ ሁኔታ፣ ለኔና ለናተ የእብዶች መንደር በማለት ትርጉም እንሰጠዉ ይሆናል። ታድያ የዛን እለት በነዚህ ሰዎች መካከል ስርአት ያለዉን ልብስን ለብሶ የተገኘ ጤነኛ አይባልም። ምናልባት ምን ለበሽ ትሉኝ ይሆናል። መቅረጸ ድምጽ በመያዜ፣ ለዘገባ በመሰናዳት ላይ ናት ብለዉ ይቅርታ ያደረጉልኝ ይመስላል! የጠየቀኝ የበአሉ እድምተኛ አልነበረም! በአሉን በሚያከብረዉ ህዝብ ላይ የሚታየዉ ደስ የሚለዉ ነገር፣ ደስታ ነዉ! ደስታ ነዉ! መጠጣት ነዉ! መብላት ነዉ! የአገራችንን የክቡር ዘበኛ ሙዚቀኛ የመሳሰሉ ቁመናቸዉ፣ ዘለግ ዘለግ ያሉ፣ ጥሩ አይን የሚገባ፣ መለዮ ያደረጉ ሴቶችና ወንዶች ደግሞ፣ ይህንኑ የሙዚቃ ማርሽ እያሰሙ፣ በበአሉ እድምተኞች መካከል አልፈዉ፣ እተዘጋጀላቸዉ መድረክን ይዘዉ ቆሙ።

የራድዮ ጣብያዉ የበአሉ አዘጋጅ የሴት ተጠሪ ሆና በተመረጠችዋ የኢራን ተወላጅ ፓሽቱ ቋንቋ ክፍል ባልደረባ ጋዜጠኛ እና በራድዮ ጣብያዉ ዋና ተጠሪ ኢሪክ ቤተማን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በአሉ በሙዚቃ ታጅቦ ተጀመረ። በካርናቫል ፈንጠዝያ ኮል አላፍ! ኮል አላፍ! እየተባለ በአንድነት ድምጽን ከፍ አድርጎ ማስተጋባት የተለመደ የበአሉ ስርአት ነዉ።
በባአሉ የተጋበዙ በቦን ከተማ እና አካባቢዋ የሚገኙ የተለያዩ አገሮች አንባሳደሮች እና ጥሪ የተደረገላቸዉ ተጋባዦች እንኻን ደህና መጣችሁ ተብለዉ በጭብጨባ ቅበላ ተደርጎላቸዋል። ታድያ እንግዶቹም ክራባት እና ጥሩ ልብስ ለብሰዉ ቢገኙም፣ ደረታቸዉ ላይ ያንጠለጠሉት የመዳልያና የድሪ ብዛት እንዲሁም አስቂኝ የሆነ ባርኔጣ፣ ከበአሉ እድምተኞች ምንም አልተለዪም። የዶቸ ቬለ ራድዮ ጣብያ ዋና ተጠሪ ኤሪክ ቤተማንም በበኩላቸዉ፣ ድምቅ ያለዉን ዉሃ አረንጌ ሱሪና ኮት ለብሰዉ፣ ደረታቸዉ ላይ የለጠፉት የሜዳልያ ብዛት እና ያደረጉት በወርቅማ ገመድ የተንቆጠቆጠ ባርኔጣ፣ እዉነትም የበአሉ ዋና አዘጋጅ ያሰኛቸዋል።
ከእንኳን ደህና መጣችሁ በኻላ የተዘጋጀዉን የምስር እና የስጋ ሾርባ፣ በዚሁ በካርናቫል ወቅት የሚበላዉ በርሊነር የተሰኘዉ ፓስቲ ብጤ ጣፋጭ እና፣ ያዉ የጀርመኑ ጥም ቆራጭ ቢራ በገፍ ቀርቦአል። በለቱ ቢራ አልተጎነጨሁም! ያችን ጣፋጭ ፓስቲ ግን ቀምሻለሁ። ለሰላሳ ደቂቃ ያህል በአሉን ቃቼ እድምተኞችን አነጋግሪ ወደ ስራ ጠረቤዛዪ ተመለስኩ።
አምስት ሺ ዘመን እንዳስቆጠረ የሚነገርለት ይህ የካርናቫል ድግስ በተለይ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የፋሲካ ጾም ለመጀመር ሲቃረቡ በፈነዝያ ለሰባት ቀናት ቆይተዉ፣ ከዝያ ስድስት ሳምንት የፋሲካን ጾም የሚጾሙበት ሁኔታ እንደሆን ዘገባዎች ያስረዳሉ። በጀርመንም አብዛኛዉ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በምዕራቡ እና በደቡባዊ የአገሪቷ ክፍል ስለሚኖር ይኽዉ በአል በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። ታድያ በበአሉ መጀመርያ ቀን ወንዶች ክራባት ለብሰዉ ሴቶች ቀይ ቀለም በተቀባ ከንፈራቸዉ የወንዶችን ጉንጭ መሳም ክራባታቸዉን መቁረጥ የተለመደ ባህላቸዉ ነዉ። የዚያ ቀን ታድያ አንድ ወንድ ተስሞ ጉንጩ ላይ ምልክት ኖሮበት ሚስት ብታይ፣ አትቆጣም! ባህል ነዉና! የበአሉ መጠናቀቅያ እለት ማለት ሰባተኛዉ ቀን ረቡዕ ይዉላል። አሸር ሚትቮህ ይሉታል። የዛን እለት ጾም የሚጀመርበት ክረምትም የሚወጣበት የጸደይ ወራት የሚጀምርበት ተብሎ ይታሰባል።

Eröffnung der Berlinale 2010 in Berlin Flash-Galerie
በመክፈቻዉ ስነስርአት ላይምስል AP
Karneval 2010
ምስል AP


የበርሊኑ የፊልም ማዕከል ስድሳኛ አመት ክብረ በአል


ባለፈዉ ሃሙስ ምሽት በጀርመን ታዋቂ የሆነዉ በርሊናለ የተሰኘዉ የፊልም ማእከል የአለም ታላላቅ የፊልም ስራ አዋቂዎችን ተዋናዮችን እና የአገሪቷን ታዋቂ ሰዎች ፖለቲከኞች ባሉበት ተከፍቶአል። የጀርመኑ ህገ መንግስት ስድሳኛ አመቱን ሲያከብር ዘንድሮ ይህ ታሪካዊ የፊልም ማዕከልም ስድሳኛ አመቱን በማክበር ላይ ነዉ። ለአስራ አንድ ቀናት የሚዘልቀዉ በርሊናለ Berlinale የተሰኘዉ በበርሊን የሚገኘዉ የፊልም ማእከል ዘንድሮ ከ 18 አገራት የመጡ 400 ያህል ፊልሞችን ለዉድድር የያዘ ሲሆን በሽልማቱ የበርሊን መለያ የሆነዉ ወርቅማዉ ድብ ይሰጣል።
በርሊናለ የፊልም ማእከል የስድሳኛ አመት በአሉን ዘንድሮ ሲያከብር የበአሉን መክፈቻ ያደረገዉ ወጣቱ ቻይናዊ Wang Quan በሰራዉ ፊልም ነዉ ከዚህ ቀደም ባቀረበዉ የፊልም ስራዎቹ የበርሊናለዉን ሽልማት ተሳላሚ ነበር።
በርሊናለ የዛሪ ስድሳ አመት ጀርመን በምስራቅ እና በምእራቡ ርእዮተ አለም ተከፍላ ሳለ በርሊን ሶሻሊስት ርእዮተ አለም በሚከተሉ አገሮች ምስራቅ ጀርመንን ጨምሮ ተከባ ሳለ ነበር በርሊን የምእራቡን አለም አገራት የፊልም ታዳሚዎች በመጋበዝ የፊልም ስራን ለማሳደግ፣ የባህል ልዉዉጥን የጀመረችዉ። ከ1951 እስከ 1966 አም ድረስ የበርሊን ከንቲባ የነበሩት ከዝያም የምእራብ ጀርመን ርእሰ ብሄር የነበሩት ቪሊ ብራንት የዚህን ዛሪ በበርሊን የአለም አገራት የተለየ ባህልን፣ ፖለቲካን፣ ነቀፊታን አልያም ተጽኖን የሚያንጸባርቁ የተለያዩ እዉቀቶችን ያዘሉ ፊልሞች ለህዝብ ለእይታ እንዲበቁ መሰረቱን የጣሉት። ቢሆንም ግን በዚህ የፊልም ስራዎችን በማምጣት ስራዉን የጀመረዉ በዝያን ግዜ አንድ አሜሪካዊ የፊልም ስራ አዋቂ የፖሊስ አዛዥ ነበር። በመጀመርያ በርሊን ከ 36 አለም አገራት የተሰሩ ፊልሞችን በማምጣት ለእይታ አቅርባለች። የምእራብ በርሊን የካፒታሊዝምን ርእዮተ አለም የሚከተሉ አገሮችን የፊልም ስራ እያመጣች ለህዝብ ማሳየቷ በምስራቅ እና በምእራብ በርሊን መካከል ያለዉን ቀዝቃዛ ጦርነት ሳያጠነክረዉም አልቀረም። ይኸዉም ምንም እንኻ ምእራብ በርሊን በምስራቁ ተከባ ብትገኝም የአለም አገራትን በማስተናገዷ የምስራቁን ወገን አስቆጥቶአል። በዚህም ነዉ የበርሊኑ ግንብ የመገንባት መሰቱ የተጠነሰሰዉ። በ 1970ዎቹ በአሜሪካዊ የፊልም አዋቂ የጦር አዛዥ ሲተዳደር የነበረዉ ይህ የፊልም መአከል አንድ የዝያን ግዜ የምእራብ ጀርመን የፊልም ስራ አዋቂ Michael Verhoeven በተቀናበር አሜሪካ በቪየትናም የፈጸመችዉን ግፍ እና በወቅቱ ስለነበረዉ አሜሪካዉያን ሴትን በመድፈር ይሰሩት የነበረዉን ግፍ በመጻረር የሰራዉን ፊልም በዚህ የካፒታሊስቱ አለም መድረክ በማሳየቱ የዝያን ግዜዉን አሜሪካዊ የፊልም ቤት አስተዳዳሪ ክፉኛ አስቆጥቶአል። በዚህም ለአንድ አመት ይህ የአለም ፊልም መድረክ ፊየስታ ተቋትጦ ነበር። ከዝያም ከአንድ አመት በኻላ ቀጥሎ ይኸዉ ዛሪ ስድሳኛ አመቱን በማክበር የሆሊዉድ የቦሊዉድ ታዋቂ የፊልም ሰራተኞችን እና ተዋናዮችን እንዲሁም ከአለም አገራት የመጡ ታዋቂ የፖለቲካ እንዲሁም በማህበራዊ ኑሮ ዘርፍ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል።

አዜብ ታደሰ