1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ መምህራን አድማ

ዓርብ፣ መስከረም 14 2008

የኬንያ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መምህራን የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ አንስተዉ የሥራ ማቆም አድማ ከጀመሩ አራት ሳምንት ሊሞላቸዉ ነዉ። በሁኔታዉ የተቆጣዉ የኬንያ መንግስት የወቅቱን የትምህርት ዘመን በመቀየር፣ የተማሪዎች የእረፍት ጊዜ አዉጆ የትምህርት ቤት በሮችን እስከነአካቴዉ ዘግቶአል።

https://p.dw.com/p/1Gcej
Nairobi Demonstration der Lehrergewerkschaft
በናይሮቢ የመምህራን ተቃዉሞ ሰልፍምስል DW/A. Kiti

[No title]


ይህ ዉሳኔ ግን፣ የዶይቼ ቬለ ያን ፊሊፕ እንደዘገበው፣ ለተማሪዎቹ ጉዳት እንጂ የሚያመጣዉ ፋይዳ የለም። በኬንያ የትምህርት ቤቶች የእረፍት ጊዜ ማብቅያ ይኖረው ይሆን? በጀርመን የሚገኙ አብዛኞቹ ተማሪዎች የሚመኙት ይህ ሁኔታ በወቅቱ ወደ 14 ሚሊዮን ለሚጠጉት ኬንያዉያን ተማሪዎች ገሃድ ሆኖዋል። ለነገሩ ለአራተኛ ሳምንት የግዳጅ እረፍት ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ ኬንያዉያን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸዉ መመለስ ይፈልጋሉ። ግን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መምህራን ደሞዛቸው እንዲሻሻል ያቀረቡት ጥያቄ መልስ እስኪያገኝላቸው አድማቸውን በመቀጠላቸው የኬንያ ትምህርት ቤቶች አሁንም በሮቻቸውን መዝጋት ተገደዋል። በሌላ በኩል አድማ ላይ የሚገኙት መምህራን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሥራ ገበታቸዉ እንዲመለሱ የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ዛሬ አርብ ማዘዙ ተሰምቶአል።
የኬንያ መንግሥት ካቢኔ በቀጠለው የመምህራን ስራ ማቆም አድማ አኳያ ባለፈው ሰኞ ርምጃ በመውሰድ የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት እና የእረፍት ጊዜ መጀመርያውን መርሃ ግብር እንዲቀይር ትዕዛዝ ሰጥቶአል። በዚህም ሚንስቴሩ ተጀምሮ የነበረውን የትምህርት ጊዜ ላልተወሰኑ ቀኖች አዛውሮዋል። በዉሳኔዉ በኬንያ የሚገኙ አንደኛ ደረጃና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሁሉ መምህራኑ የስራ ማቆም አድማ ከጀመሩበት ካለፈው ነሐሴ 25፣ 2007 ዓም ጀምሮ እረፍት ላይ ይገኛሉ ማለት ነው። ይኸው የመንግሥት ዉሳኔ ትምህርት ቤቶች በሮቻቸዉን የዘጉት በአስተማሪዎች የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ አድማ ሰበብ ሳይሆን በእረፍት ምክንያት አስመስሎዋል።
ይህ የመንግስት ዉሳኔ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ብቻ ሳይሆን በአድማ ላይ ያልሆኑ የግል ትምህርት ቤቶችንም እንዲዘጉ አስገድዶዋል። የኬንያ የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር ዋና ተጠሪ ኧርንስት ዋንጊ ሁኔታ እጅግ አስቆጥቶአቸዋል።
« ጉዳዩ የግል ትምህርት ቤቶችን ጎድቶአል ። ትምህርት ቤቶቻችንን የሚያዘጋ ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ከመምህራን እና የትምህርት ቤት ክፍያቸውን ካጠናቀቁ ወላጆች ጋር ነው ውል ያለን። »

በኬንያ የመምህራን ስራ ማቆም አድማ ዋና ሚና የያዙት የሃገሪቱ ብሔራዊ የአስተማሪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ ዌልሰን ሶስዮም በመንግስት ዉሳኔ ተበሳጭተዋል።
«ሁኔታዉ በጣም አስቂኝ ነዉ። ዝግ የነበረዉን ትምህርት ቤት እንዴት ነዉ እንደገና መዝጋት የሚቻለዉ? በዚህም አለ በዝያ በአድማዉ ምክንያት ምንም ዓይነት ትምህርት የለም።»
ኬንያዉያን መምህራን ለደምወዝ ጭማሪ ሲታገሉ ከአስርተ ዓመታት ጀምሮ ለተደጋጋሚ ጊዜ የስራ ማቆም አድማ ታይቶአል። የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መንግሥት ከጎርጎረሳዊ 1997 ዓ,ም ወዲህ የአስተማሪዎችን ደሞዝ እስከ 60 ከመቶ ጭማሪ እንዲያደር ባለፈዉ ነሐሴ ወር መጨረሻ መወሰኑ ይታወቃል። የመምህራን ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነው የሚመለከተው መስሪያ ቤት ግን በፍርድ ቤቱ ውሳኔ አንፃር ይግባኝ ማመልከቻ አስገብቷል። መምህራኑም ይህንን በመቃውም ነው አድማ የጀመሩት።
በኬንያ መምህራን ማኅበሩና በመንግስት በኩል የጀመረዉ ንትርክ እየጠነከረ በመምጣቱ ችግሩ በቅርቡ መፍትሄ የሚያገኝ አይመስልም። በዚህ መሃል ተማሪዎች በተለይም በያዝነዉ የጎርጎሮሳዉያን 2015 ዓመት መጨረሻ የትምህርት ማጠቃለያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸዋል። መንግስት የትምህርት ቤት መዝግያውን ቀን ቢለዉጥም የትምህርት ቤት የማጠቃለያ ፈተና መስጫ ቀን ግን አልተቀየረም። ሆኖም የኬንያ ብሔራዊ ትምህርት ቤት የማጠቃለያ ፈተና ኮሚሽን ፈተናው በመምህራኑ መልካም ፈቃድ ይካሄዳል የሚል እምነት እንዳላቸዉ የኮሚሽኑ ዋና ተጠሪ ኪብሩ ኪንያንጂ ተናግረዋል። «ጉዳዩ የሚመለከተዉ አስተማሪዎችንና ቀጣሪዎቻቸዉን ነዉ። ለሌላዉ ጊዜ አስተማሪዎች በፈተና ጊዜ ተመልካች ሆነዉ እንዲረዱን በተናጠል እንስማማ ነበር። »
የኬንያዉ የሀገር አስተዳደር ሚኒስትር ጆሴፍ ኒካዜሪ በበኩላቸዉ የማጠቃለያ ፈተናዉ ዝግጅት በአድማዉ ምክንያት መስተጓጎል ቢገጥመዉ በሕግ መምህራኑን እንደሚጠይቁ ዝተዋል። ኬንያ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መወሰኑ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት የኬንያዉ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መንግስታቸዉ የደሞዝ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችል እና እንደማይፈልግም አስታውቀዋል። ኡሁሩ በሰጡት ማብራርያ ደሞዝ የመጨመር አቅም እንደሌለው ነው ያስረዱት። ይህ በዚህ እንዳለ ፣ በኬንያ መንግሥት በመምህራን ማኅበር መካከል የጀመረዉ እሰጣ ገባ አሁን ለፍርድ ቤት የቀረበ ቢሆንም፣ በቅርቡ መፍትሔ የሚያገኝ አይመስልም።


አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Kenia Afrika Lehrerstreik Mudzo Nzili KNUT Nationale Lehrervereinigung
ሞዱዞ ንዚሊ፤ የኬንያ ብሔራዊ የመምህራን ማኅበርምስል Alfred Kiti
Kenia Afrika Lehrerstreik Gruppenbild
የኬንያ የመምህራን አድማ ቡድንምስል Alfred Kiti
Kenia Afrika Lehrerstreik Lydya Nzomo Nationale Lehrervereinigung
ሊዲያ ንኁሞ፤ የኬንያ ብሔራዊ የመምህራን ማኅበርምስል Alfred Kiti