1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ምርጫና የአካባቢዉ መንግሥታት

ሰኞ፣ የካቲት 25 2005

ለምርጫዉ ሠላማዊ፥ ዲሞክራሲያዊነት፥ ለዉጤቱ ነፃ፣ ትክክለኛነት፣ከምዋዪ ኪባኪ፥ ከራይላ ኦዲንጋ፥ ከኡሑሩ ኬንያታ እኩል ዩዌሩ ሙሳቬኒ፣ ፖዉል ካጋሚ፣ ቴዎድሮስ አድሐኖም «አሰብን፣ ተጨነቅን» ማለታቸዉ እንጂ አነጋጋሪዉ

https://p.dw.com/p/17qGZ
Schlagworte: Kenyan elections 2013, Wer hat das Bild gemacht: James Shimanyula Wann und wo wurde es aufgenommen: 04.03.13, Mutomo  polling  station  in  central  Kenya Was ist darauf zu sehen : voters  queueing  to  vote  at  Mutomo  polling  station  in  central  Kenya,  60 kilometres    north  of  Nairobi.  Angeliefert von Mark Caldwell am 4.3.2013. Der Fotograf ist laut mr. Caldwell DW-Mitarbeiter.
ያሁኑ ምርጫምስል DW/J.Shimanyula


የኬንያ ሕዝብ ዛሬ ደምፁን የሰጠዉ ለሚደግፈዉ ፖለቲከኛ ድልን በመመኘት እና የዛሬ አምስት አመቱ እልቂት እንዳይደገም በመፀለይ፣ መጠንቀቅ መሐል እንደተቃረጠ ነዉ።ያለፈዉን ምርጫ አሳዛኝ መዘዝ የቀመሰዉ ቀርቶ የሰማዉም በዛሬዉ ምርጫ ከሚፎካከሩት ፖለቲከኞች ማንነት፣ መርሕ ይልቅ ሥለምርጫዉ ሒደት ዉጤት፣ ቢያስብ፣ ቢፀልይ፣ ቢጠንቀቅ በርግጥ አይበዛበትም። ለምርጫዉ ሠላማዊ፥ ዲሞክራሲያዊነት፥ ለዉጤቱ ነፃ፣ ትክክለኛነት፣ከምዋዪ ኪባኪ፥ ከራይላ ኦዲንጋ፥ ከኡሑሩ ኬንያታ እኩል ዩዌሩ ሙሳቬኒ፣ ፖዉል ካጋሚ፣ ቴዎድሮስ አድሐኖም «አሰብን፣ ተጨነቅን» ማለታቸዉ እንጂ አነጋጋሪዉ።ያሁኑ ምርጫ መነሻ፣ ያለፈዉ ልምድ ማጣቀሻ፣ የጎረቤት ሐገራት ፖለቲከኞች ማንነት እና ለኬንያዎች የማሰባቸዉ ሰበብ ምክንያት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ዴቦራሕ ምኬያሲ የአራት ዓመት ጨቅላ ነበረች።ቤታቸዉ ሲጋይ ወደ ዉጪ ሮጠች።ከቤት ስትወጣ ጎረቤቶችን በማየቷ ወደነሰዉ ሸሸች።«ወንድሜ፥ ወንድሜ» ትላለች ወደ እሚቃጠለዉ ቤት እያመለከተች።በገጀራ ተቀበሏት።እናትና አባት ሲደርሱ ቤታቸዉ ጋይቶ፥ የሰወስት ዓመት ወንድ ልጃቸዉ ከስሎ፥ የአራት አመት ሴት ልጃቸዉ ክንዷ በገጀራ ተገምሶ ጠበቋቸዉ።

«እዚሕ ጋ ነዉ፥ የክንዷ ነርቭ ነዉ የበጠሱት» አሉ አባት በቀደም፥ የልጃቸዉን የማይንቀሳቀስ እጅ እያመለከቱ።ድቦራሕ ዘንድሮ ዘጠኝ አመቷ ነዉ።አባት ፊሊሞን ሚኪያስ እስከ ያኔ ድረስ የአንድ የአበባ እርሻ ሥራ-አስኪያጅ ነበሩ።ከያኔ ጀምሮ ግን ወደ ሥራቸዉ አልተመለሱም።

«እዚያ ያሉት (ለኛ) ጠላቶች ናቸዉ።የምሠራበት ሥፍራ አሁን ያሉት ኩኩዮች ብቻ ናቸዉ።»የእስከ ያኔዉ ደስተኛ ቤተሰብ ዛሬ ከንኩሩዉ ከተማ የድሆች መንደር የመከራ ኑሮ ይገፋል። የድቦራሕ፥ የወላጅ፥ ባልጀራ፥ የዘመድ ወዳጆችዋ፥ ምኞት፥ ዛሬ የሚደረገዉ ምርጫ ሲሆን የያኔዉን የልብ ስብራታቸዉን የሚጠግን፥ ቁስል፥ ስቃይ ሰቆቃቸዉን የሚያሽር፥ ይኽ ቢቀር ያለፈዉ እንዳይደግም የሚያደርግ እንዲሆን ነዉ።

እሱ እነ ዲቦራሕን በአካል አያዉቃቸዉም።የደረሰባቸዉን ግን ጠንቅቆ ያዉቀዋል።የነዲቦራ የእድሜ አቻዎች በዳዮቻቸዉን ይቅር እንዲሉ መመኘት፥ መፀለይ ብቻ ሳይሆን ለማስተማር እያጠረም ነዉ።«ኤድዊን እባላለሁ።ይሕን በራሪ ወረቀት ልጆችና ለወጣቶች እያከፋፈልኩ ነዉ።መልዕክታችን ችግሩን እናስወግድ የሚል ነዉ።ችግር አንፈልግም።»

ሴትዮዋም ያለፈዉ እንዳይደገም ይመኛሉ።ተስፋም አላቸዉ።«ምርጫዉ ጥሩ እንደሚሆን አዉቃለሁ።ግጭት የሚቀሰቀስበት ምክንያት የለም።»ሰዉዬዉ ደግሞ ከተስፋም በላይ ካለፈዉ ጥፋት ተምረናል ባይ ናቸዉ።«እንደ በጥባጭ ታዉቀናል።አሁን ግን ጨዋ መሆን እንደምንችልም ለዓለም እናሳያለን። ካለፈዉ ጥፋታችን ተምረናል።»

የኬንያዎች ፀሎት፥ ምኞት፥ ተስፋ፥ ጥንቃቄ ዛሬ ቢያንስ ሞባሳ ላይ ሙሉ በሙሉ አልያዘም። በትልቂቱ የወደብ ከተማ ጠመንጃ፥ ጦርና ገጀራ በታጠቁ ሰዎችና በፀጥታ አስከባሪዎች መካካል ዛሬ ጠዋት በተደረገ ግጭት ከሁለቱም ወገን ስድስት፥ ስድስት ሰዉ ተገድሏል።በድምሩ አስራ-ሁለት።

የኬንያ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ቻርልስ ኦዊኖ እንዳሉት ግን ይሕን መሰሉ ግጭት ሞባሳ እንዳይደገም፥ ወደ ሌላ ሥፍራ እንዳይዛመትም ፖሊስ የሚችለዉን ሑሉ ያደርጋል።

«ሙሉ በሙሉ መዘጋጀታችንን ለኬንያዎች እናረጋግጣለን።ሠላማዊ፥ ነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ የሚደረግበት ድባብ እንዲፈጠር ከሌሎች የፀጥታ አስከባሪ ድርጅቶች ጋር ተባብረን እየጠርን መሆናችንን ለሁሉም እናረጋግጣለን።»

እንደ ፖሊስ አዛዡ ሁሉ ከአስመራጭ ኮሚሽን ባለሥልጣናት እስከ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ያሉ ፖለቲከኞች ምርጫዉን ሠላማዊ፥ ነፃ እና ፍትሐዊ ለማድረግ ለሕዝባቸዉ ቃል ገብተዋል።የገቡትን ቃል ገቢር ማድረግ አለማድረጋቸዉን ለማወቅ ግን በርግጥ ዕለታት መጠበቅ ግድ ነዉ።

ልክ እንደ ኬንያ ፖለቲከኞች ሁሉ ከዩጋንዳ እስከ እስከ ሩዋንዳ፥ ከኢትዮጵያ እስከ ጅቡቲ የሚገኙ መሪዎች እና ባለሥልጣናት የኬንያዎች ምርጫ ለኬንያዎች ሠላማዊ፥ ነፃ፥ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እንደተራዉ ሕዝባቸዉ ተመኝተዋል፥ እንደ ሐገር መሪነታቸዉ የየበኩላቸዉን ለማድረግ ቃል ገብተዋል።የሁለት መሪዎች ጨዋታ

ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ በጠብመንጃ፥ ኤሚሊዮ ምዋዪ ኪባኪ በዉርስ የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ ለመቀጠል ተቀናቃኝን የማራቅ፥ ማሳጣቱን ሥልት በመቀየሥ አንድ ናቸዉ።ያን ሥልት ገቢር ያደረጉበት ዘመንም አንድ ነበር።ሕዳር ሁለት ሺሕ አምስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር።)

ሥልቱን ገቢር በማድረጉ ሒደት ግን ተለያዩ።ከሃያ-አመት በፊት ከጫካ የመጡት ሙሳቬኒ ጫካ እንደኖሩበት፥ ሃያ ዓመት እንደሱሩበት ዋነኛ ተቀናቃኛቸዉን ኪይዛ ቤሲግዬን ሴት በመድፈር፥ በሙስና እና በአሸባሪነት፥ ወንጅለዉ ወሕኒ ወረወሯቸዉ።

ኪባኪ ግን ለሥልጣናቸዉ የሚያሰጉቸዋን ራይላ ኡዲንጋንና ብጤዎቻቸዉን ከሚንስትርነት ሥልጣን ሽረዉ ተዋቸዉ።ኪባኪ ከሥልጣን ያስወገዷቸዉ ራይላ ኦዲኒጋና ሌሎች ተቃዋሚዎቻቸዉ የመሠረቱትን ጥምረት ጠልፈዉ የሚጥሉበትን የምርጫ ዕለት ሲያሰሉ፥-ሙሴቬኒ ከሁለት ሺሕ አንድ ጀምሮ እያሰሩ፥ በሐሰት እወነጀሉ፥ እንዳዴም እያስደበደቡ፥ እያደካሙ የሚፈቷቸዉን ቤሲግዬን እንደገና ከእስር ቤት ፈተዉ «ምርጫ» ባሉት ድምፅ አሸንፍኩ አሉ።ሁለት ሺሕ ስድስት።

ሁለት ሺሕ ሰባት ማብቂያ ኬንያዎች መረጡ።የኪባኪ ሥልት፥ የኦዲንጋ አፀፋም ኬንያዊዉን ዘር፥ ጎሳ ለይቶ በማጨፋጨፍ ማሳረጉ እንጂ ድቀቱ።የኬንያ ፖለቲከኞች በዛሬዉ ምርጫ ያለፈዉን ሥሕተት ላለመድገም ቃል መግባታቸዉ፥ የኬንያ ሕዝብ ከሥሕተቱ ለመማር መወሰን፥ መፈለግ መጣሩን ሠላም ወዳዶች፥ የነፃ፤ ፍትሔዊ ምርጫ፥ የሕግ የበላይነት ደጋፊ፥ ናፋቂዎች ሁሉ ይመኛሉ።

ተቃዋሚዎቻቸዉን እያሰሩ፥ ተቃዋሞዉን እየደፈለቁ፥ የዩጋንዳን ሕዝብ ለሃያ-ሰባት ዘመናት ረግጠዉ የገዙት ዩዌሪ ሙሴቬኒም እንደ ሠላማዊ፥ ዲሞክራሲያዊ መሪ ለኬንያዎች ሠላም፥ ዲሞክራሲ ተጨነቅኩ ማለታቸዉ እንጂ ጉዱ።ግን አሉት።

«ልነግራችሁ የምፈልገዉ ኬንያዎች ሠላማዊ ምርጫ ያደረጉ ብዬ እንደማስብ ነዉ።ግጭትና አለመረጋት ለማንም አይጠቅምም።»

የኬንያ ፖለቲከኞች በምርጫ ዉጤት በፈጠሩት ዉዝግብ ሰበብ ኬንያዊዉ ሲተላለቅ፥ ኢንጂነር ሐይሉ ሻዉል የሚመሯቸዉ የቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፖለቲከኞች፥ አባላትና ነፃ ጋዜጠኞች እልቂቱን የእልቂቱን ሰበብ ምክንያት የሚሰሙት ወሕኒቤት ሆነዉ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት የያኔ ተቃዋሚዎች በጎዳና ላይ ነዉጥ የመወንጀል መታሰራቸዉ ሠበብ በሁለት ሺሕ አምስት የተደረገዉ ምርጫ ዉጤት ዉዝግብ እና ደም አፋሳሽ ግጭት ነበር።የኬንያ ፖለቲከኞች ተጣማሪ መንግሥት መስርተዉ ግጭት ግድያዉን አቀዛቅዘዉ፥ እርቀ-ሠላም ለማስፈን ሲጣጣጠሩ፥ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ በዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶ «አሸንፍኩ» ባለዉ ምርጫ ያራዘመዉን ሥልጣን ለሃያ-አንደኛ ዘመን እያጠናከረ ነበር።

የዛሬዉ የኬንያ ምርጫ ሠላማዊ፥ ነፃ፥ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊነቱን ለመከታተል ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊካዊቷ ኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯን ወደ ናይሮቢ ልካለች።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቴዎድሮስ አድሐኖም የኢጋድ አባል ሐገራት ሚንስትሮችን መርተዉ ባለፈዉ ሳምንት ወደ ናይሮቢ ሲሄዱ፥ መንግሥታቸዉ ሐይማኖታዊ ነፃነታችን ገፈፍን የሚሉ ሚሊዮን ሙስሊሞች ከአንድ ዓመት በላይ እንዳደረጉት ሁሉ በየመሳጂዱ ይጮሁ ነበር።


እንደ ሙስሊሞቹ ሁሉ የክርስቲያን የሐይማኖት መሪዎች መንግሥትን ይቃወሙ፥ በመንግሥት ይደገፋሉ ያሏቸዉን ወገኖች ያወግዙ ነበር።የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም መንግሥት በምርጫ እንዳንሳተፍ «በሩን ዘጋብን» በማለት ይወቅሱ ነበር።ዶክተር መረራ ጉዲና አንዱ ናቸዉ።


እንደ ዩጋንዳ፥ እንደ ኢትዮጵያ መሪዎች ሁሉ በጠመንጃ አፈሙዝ ሥልጣን የያዙት፥ተቃዋሚዎቻቸዉን በአሸባሪነት እየወነጀሉ፥ እያሰሩ፥ እያስፈራሩ ፥ሕዝባቸዉን ረግጠዉ የሚገዙት የሩዋንዳ ገዢዎችም የኬንያ ምርጫ ሠላማዊ፥ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን አጥብቀዉ እንደሚመኙ፥የሚችሉትን ለማድረግ እንደሚጥሩም ቃል ገብተዋል።

ኬንያ በርግጥ ሙስና የነገሠባት፥ ማጅራት መቺና ዘራፊ የሚፎልልባት ሐገር ናት።የዚያኑ ያክል የምሥራቅ አፍሪቃ ሐብታም፥ ሥልታዊ፥ ባለብዙ ወደብ ሐገር ናት።የዚች ሐገር መታወክ የአካባቢዉን መንግሥታት ከሰብአዊነትም ባለፍ ቢያሳስብ በርግጥ አይገርምም።በተለይ እንደ ዩጋንዳ፥ እንደ ኢትዮጵያ፥ እና ሩዋንዳ የመሳሰሉት ወደብ አልባ ሐገራት ኬንያ ዉስጥ ሠላም ከሌለ ምጣኔ ሐብታቸዉ በቀጥታ መነካቱ አይቀርም።ይሕ ቢያሳስባቸዉ እዉነት ነዉ።

ከዚሕ ባለፍ ከካምፓላ እስከ አዲስ አበባ፥ ከኪጋሊ እስከ ጅቡቲ፥ ከአስመራ እስከ ካርቱም፥ የሚገኙ የአካባቢዉ ሐገራት ገዢዎች ሥለ ኬንያ አሰብን የማለት፥ መልዕክተኛ የመላካቸዉ ምክንያት የነፃ፥ ፍትሐዊ ምርጫን፥ የዲሞክራሲ፥ የሕግ የበላይነትን እንዴትነት፥ የመገናኛ ዘዴ፥ የማሰብ-መደራጀት፥ የኢኮኖሚ ነፃነትን እስከየትነት ለማወቅ ፈለገዉ ከሆነ በርግጥ ዘየዱ። ከኬንያ ብዙ ይማራሉና።ግን እንዲያ አለመሆኑ ነዉ-ድቀቱ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ














A cyclist moves past campaign posters of Kenya's presidential candidate Peter Kenneth at the Kangemi slum in Kenya's capital Nairobi February 28, 2013. Kenya will hold its presidential and parliamentary elections on March 4. REUTERS/Siegfried Modola (KENYA - Tags: POLITICS ELECTIONS)
ያሁኑ የምርጫ ዘመቻምስል Reuters
Zwischenfälle an der Ostküste Kenias. Copyright: DW/Daniel Nyassy Bild geliefert von DW/Andrea Schmidt.
ያለፈዉ ጥፋትምስል DW/D. Nyassy
Auf dem Bild: Werbung für Frieden. Nairobi, Kenia, am 2.3.2013 Rechte: DW/M.Braun
ሠላምምስል DW/M.Braun
Supporters of Kenyan Prime Minister and Presidential candidate, Raila Odinga, gather at Nyayo National Stadium in Nairobi, Kenya, Saturday, March 2, 2013, for the final day of the campaign for the upcoming election. Kenya's top two presidential candidates are holding their final rally before the country votes on Monday March 4.(AP Photo/Sayyid Azim)
የምርጫ ዝግጅትምስል picture-alliance/AP Photo
Zwischenfälle an der Ostküste Kenias. Copyright: DW/Daniel Nyassy Bild geliefert von DW/Andrea Schmidt.
ያለፈዉ ጥፋትምስል DW/D. Nyassy