1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ምርጫና የዉጤቱ አንድምታ

ማክሰኞ፣ የካቲት 26 2005

ኬንያዉያን ትናንት በተካሄደዉ አጠቃላይ ምርጫ ከተገመተዉ በላይ በመዉጣት ድምፃቸዉን ሰጥተዋል። የምርጫዉን ሂደት ከቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚሉትም ህዝቡ ያለፈዉን ከምርጫ በኋላ የታየ አመፅና ግጭት እንዳይደገም የሰጋ ይመስላል።

https://p.dw.com/p/17qxZ
ምስል DW/ M. Braun

ዛሬ ቆጠራዉ እየተካሄደት ባለበት ሁኔታ የመጀመሪያ የምርጫ ዉጤት የጠቆመዉ ዑሁሩ ኬንያታ የመሪነቱን ደረጃ እንደያዙ ነዉ። ኬንያታ ከጎርጎሮሳዊዉ 2007ዓ,ም ምርጫ ማግስት ከታየዉ አመፅ ጋ በተገናኘ ተጠያቂ ተብለዉ በዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸዉ በመሆኑ ይህ ምን አንድምታ ይኖረዋል?ዑጋንዳዊዉ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ቲሞቲ ካሊጊራን  አንተ የኬንያን የምርቻ ሂደት ከቅርብ ርቀት ከሚከታተሉት ወገኖች አንዱ እንደመሆንህ እስኪ የዘንድሮዉን የኬንያን ምርጫ ካለፈዉ ጋ በቅድሚያ አነጽፅርልኝ ነበር ያልኩት፤

Abschlusskundgebungen vor der Präsidentenwahl in Kenia
ምስል picture-alliance/AP Photo

«እዉነት ነዉ፤ ሁላችንም በምናዉቀዉና ምስራቅ አፍሪቃን ባተራመሰዉ በአመፅ በተጠናቀቀዉ ያለፈዉ ምርጫ ምክንያት ይህ ምርጫ የተለየ ነዉ። ሰዎች እንደአቢይ ብሄራዊ ጉዳይ ነዉ የወሰዱት፤ ምክንያቱም የሀገሪቱ ብሄራዊ እጣ ፈንታ አደጋ ላይ ስለሆነ ማለት ነዉ። ስለዚህ ለምርጫ እጅግ ከፍተኛ ህዝብ ነዉ የወጣዉ፤ ከሰባ በመቶ በላይ። እናም ከመነሻዉ ሰዎች በኤሌክትሮኒክ የድምፅ መስጫ ስልት ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል እጩ ተወዳዳሪዎች በቴሌቪዥን የምርጫ ክርክር አድርገዋል፤ የአሜሪካንን ስልት ለመጠቀም ሞክረዋል። ሆኖም ግን የምርጫ ዉጤቱ ሲታይ፤ አሁን ከአየአካባቢዉ መታየት ጀምሯል፤ በዚህ ደግሞ ወደኋላ ወደጎሳ ጉዳይ ተመልሰዉ የገቡ አስመስሏቸዋል።»

እንግዲህ አንተም እንደጠቀስከዉ የምርጫዉ የመጀመሪያ ዉጤት መታየት ጀምሯል፤ እናም ይህ እንደጠቆመዉ ዑሁሩ ኩንያታ እየመሩ ነዉ፤ ኬንያታ ባለፈዉ ምርጫ ማግስት ከተከሰተዉ አመጽ ጋ በተገናኘ በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድቤት ICC ተከሰዉ ጉዳያቸዉ እየተየ ይገኛል፤ ለመሆኑ ይህ ምንን ያመለክታል ማለት ይቻላል?

«ኬንያ በአሁኑ ወቅት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነዉ የተጋፈጠችዉ። በመጀመሪያ አዎ በዚህ በICC ክስ ምክንያት ማለትም ይህ ክስ በዑሩ ኬንያታ ላይ ብቻ ሳይሆን በተጓዳኛቸዉ ዊልያም ሩቶ ላይም ነዉ፤ እናም ኬንያታና ሩቶ በጋራ የቆሙት ተፎካካሪዎች የICC ተጠርጣሪዎች ናቸዉ። እናም ዉጤቱ በዚህ መልኩ ቀጥሎ ከተጠናቀቀ ኬንያ የመረጠችዉ ሁለት ICC እንዲቀርቡ የሚፈለጉ ሰዎችን ነዉ ማለት ነዉ፤ ይህ ደግሞ አሳፋሪነቱ ይቀጥላል፤ ምክንያቱም የሀገሪቱ ፕሬዝደንትና ምክትል ፕሬዝደንት የጦር ወንጀል ተጠርጣሪዎች መሆናቸዉ ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ አየሽ እንዲህ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፤ ይኸዉም ዓለም ዓቀፉ አካል፤ የአዉሮፓ እና አሜሪካ የፖለቲካ ስልት እነዚህን ሰዎች እንደጦር ወንጀለኛ የሚያይዋቸዉ ከሆነ ታዲያ እነዚህ ሰዎች እንዴት በዚህ ምርጫ አሸናፊዎች ሊሆኑ ቻሉ? ወይም እንዴት ብዙ ድምፅ ሊያገኙ ቻሉ? የሚለዉ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል። ኬንያዉያን ምንነካቸዉ? ለመሆኑ ኬንያዉያን የሚያዉቁት ነገር ግን ዓለም የማያዉቀዉ ምንድነዉ? ሚል ማለት ነዉ።»

Kenia Wahl 2013
ዑሁሩ ኬንያታምስል DW/J.Shimanyula

ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ቲሞቲ ጋሊጊራ እንደሚለዉ የዚህ ምርጫ ዉጤት አሁን በታየዉ አካሄድ የሚጠናቀቅ ከሆነ ሌላም ሊታይ የሚገባዉ አቅጣጫ ይኖራል፤

«ሁለተኛ ደግሞ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ በትዊተር የሚከራከሩበት ነጥብም አለ፤ ዊልያም ሩቶና ዑሁሩ ኬንያታ በICC መጠርጠራቸዉ ምርጫዉን አዛብቶታል የሚሉ ወገኖች አሉ። ይኸዉም እነዚህን ሰዎች የሚደግፏቸዉና የመጡበት ጎሳ አባላት ለምርጫዉ በከፍተኛ ደረጃ መዉጣታቸዉ ነዉ የሚነገረዉ፤ ይኸዉም እጩዎቻቸዉን ለመምረጥ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ሰዎች በመምረጥ ወደዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት ICC እንዳይወሰዱ ለመከላከል ያደረጉት ነዉ የሚሉ አሉ፤ የምለዉ ግልፅ ከሆነ። ይህ ማለት ሰዎች ርዕሰ ጉዳዮች፤ የፖለቲካ ጉዳዮች፤ የልማት መርሃግብር እና የመሳሰሉትን መሠረት አድርገዉ ሳይሆን ድምፅ የሚሰጡት በስሜታዊነትና በጎሰኝነት ይመስላል። የሚታየዉ አስገራሚ ሁኔታ ነዉ። እርግጥ ነዉ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ነዉ፤ ስለማጭበርበር ብዙም የሚወራ አይመስልም ግን ከምርጫዉ ጀርባ ያለዉ ስሜት ሚዛናዊነት የተላበሰ አይደለም። »

በመጨረሻም ከኬንያ የምርጫ ሂደት አጎራባች ሀገሮች ሊቀስሙት የሚችሉት ተሞክሮም ሆነ ልምድ ካለ ለሚለዉ ጋዜጠኛ ካሊጊራ ይህን ይላል፤

«ዋናዉ ትምህርት የሚመስለኝ፤ የተለያዩ የአፍሪቃ ሀገሮችን ምርጫ ተመልክቻለሁ፤ ታንዛኒያ፤ ቻድ፤ ሶማሌ ላንድ፤ አልጀሪያ የመሳሰሉትን አይተናል፤ አፍሪቃ ከምዕራቡ ዓለም የምርጫ አካሄድ ሊወስድ የሚገባዉ ነገር ያለ ይመስለኛል፤ በምርጫ ሁሉም ህዝብ ነዉ የሚያሸንፈዉ፤ ትልቁን ድምፅ ያገኘዉ አሸናፊ ይሆናል ፕሬዝደንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል ሆኖም ሌሎች ተሸናፊዎቹም ማለት ነዉ የዚህ ስልጣን አካል ነዉ የሚሆኑት። የስልጣን መጋራት በእኔ አመለካከት በቀጣይ ዓመታት አፍሪቃ ዉስጥ መምጣት ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል። ስልጣን መጋራት ሀገርን የሚያረጋጋ ርምጃ ነዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ