1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ምርጫ ዉጤትና አስተያየት

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2005

በኬንያ ባለፈዉ ሳምንት ሰኞ የተካሄደዉ አጠቃላይ ምርጫ ዉጤት ይፋ መሆን እስካሁን ያስከተለዉ ችግር የለም። የዛሬ አምስት ዓመት ምርጫ በከፍተኛ አመፅ መታጀቡ፤ ያም ያስከተለዉ የህይወት ጥፋትና የሰዎች መፈናቀል ቢያንስ ዛሬ እንዲደገም የሚፈልግ ወገን አለመኖሩ ሂደቱን በቅርበት የሚከታተለዉን ዓለም ዓቀፍ ኅብረተሰብ ከስጋት አሳርፏል።

https://p.dw.com/p/17v9i
ምስል Reuters

«ኬንያዉን በሰላም ለመዝለቅ በመወሰናቸዉ በጣም አመሰግናለሁ።»

ሞምባሳ የሚገኙት የኬንያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ ሎረንስ ቻይ ናቸዉ ይህን ያሉት። የኬንያ የምርጫ ዉጤት ከተገለፀ በኋላ እንዲህ ያለዉን አስተያየት የሚሰጡ ተበራክተዋል። በተለይ ኪሱሙ በጎርጎሮሳዊዉ 2007/2008ዓ,ም ከምርጫ ማግስት የተከሰተዉ አመፅ ያስከተለዉ መዘዝ ዛሬ በሰዎች አጥንት ዉስጥ የተሸሸገ ይመስል የፍርሃት ድባብ ረቦባታል። ህዝቡም የምርጫ ዉጤቱ ምንም ይሁን ምንም ያንን ክፉ ቀን አይመልሰዉ የሚል አስመስሎታል። ኪሱሙ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ጠንካራ ይዞታ ነዉ፤ ኦዲጋ ያኔ የምርጫዉን ዉጤት አለመቀበላቸዉን ሲናገሩ የእሳቸዉ ወገኖች ኪኩዮዎች ላይ የበቀል ርምጃ ወስደዋል።

በአንፃሩ በዘንድሮዉ ምርጫ ኬንያዉያን ድምፃቸዉን ከሰጡ በኋላ ዉጤቱን ከዛሬ ነገ በሚል ሲጠባበቁ ሳምንቱ ረዝሞባቸዉ ነዉ የሰነበተዉ። የምርጫ ታዛቢዉ ዛካሪ ሙቡጉዋ እንደሚሉት፤ በርግጥ ቆጠራዉ በኮምፒዩተር ተጀምሮ በእጅ ነዉ የተጠናቀቀዉ።

«ድምፁ በኤሌክትሮኒክስ እንዲተላለፍ ነበር የተፈለገዉ ነገር ግን በርካታ ግድፈቶች ተከሰቱ፤ ስለዚህ ድምፁ በእጅ ተቆጥሮ እስኪጠናቀቅ በትዕግስት መጠበቅ ነበረብን።»

ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ኬንያ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራትን ፕሬዝደንቷን አወቀች። ዑሁሩ ኬንያታ 50,07 በመቶ ድምፅ ይዘዉ ለመለያ ዳግም ሊካሄድ ከሚችለዉ ምርጫ ለጥቂት ተርፈዋል።

ዑሁሩ ኬንያታ በይፋ ማሸነፋቸዉን ከሰሙ በኋላ ባሰሙት ንግግር እንዲህ ብለዋል፤

«ኬንያዉያን ወገኖቼ ዛሬ የዴሞክራሲን፣ የሰላምን እና የዜጎችን ድል አድራጊነት ልዕልና እናከብራለን። በዓለም ዙሪያ ብዙዎች ሳንክ ያለበት አድርገዉ ቢያዩትም እንኳ ፖለቲካችንን ብስለት ስክነት እንዳለዉ ለዓለም አሳይተናል።»

Kenia Präsidentschaftswahl Raila Odinga
ራይላ ኦዲንጋምስል Getty Images/AFP

ተቀናቃኛቸዉ ራይላ ኦዲንጋ አሁንም እንደያኔዉ የምርጫ ዉጤቱን የተቀበሉ አይመስልም። የክስ አቤቱታቸዉን ወደከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ለማቅረብ እያጠናቀሩ እንደሚገኙ ተሰምቷል። ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ለመመልከት ዝግጁ መሆኑን አሳዉቋል።

ኬንያታ በምርጫዉ ያገኙት ድል ያልተጠበቀ ነዉ ባይባልም ሊያስከትል የሚችለዉ ገና ይፋ ሳይነገር አንስቶ ማነጋገር ጀምሯል። ኬንያታ እና ተጓዳኛቸዉ ዊሊያም ሩቶ የዛሬ አምስት ዓመት የተፈጠረዉን የምርጫ ማግስት አመፅ በማነሳሳት ተጠርጥረዋል። ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ችሎት ICC ኬንያታ ላይ በሰብዓዊነት ላይ ከተፈፀመ ወንጀል ጋ የተገናኙ አምስት ክሶችን መስርቷል። የሀገሪቱ ፕሬዝደንት እንዲሆኑ የተመረጡት በICC ክስ የተመሠረተባቸዉና በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀመ ወንጀል ተጠርጣሪ መሆናቸዉ ከተለያዩ ሀገሮች ጋ ኬንያ ያላትን ግንኙነት ጥያቄ ዉስጥ ይከታል የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም ኬንያዊዉ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ አህመድ ራጂብ ደግሞ እንዲህ ነዉ ያለዉ፤

«እንደብሪታንያ ወይም ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ሀገሮች ኬንያ ላይ የሚጥሉት ጠንካራ የሚባል ማዕቀብ አይኖርም፤ ምክንያቱም ከፍተኛ የኤኮኖሚ ግንኙነት ፍላጎቱ ስላለ። በተጨማሪ ደግሞ አሜሪካ ከኬንያ ጋ ጠቃሚ ጉድኝት መሥርታለች ፀረ ሽብርተኝነት ጦርነት በሚባለዉ ማለት ነዉ።»

ICC በዛሬዉ ዕለት ከኬንያታ ጋ ክስ ከተመሠረተባቸዉ ኬንያዉያን አንዱ ፍራንሲስ ሙታዉራን ክስ ማንሳቱን አስታዉቋል። ክሱ የተነሳዉ በሙታዉራ ላይ ይመሰክራሉ የተባሉ ዋነኛ ምስክር አመኔታ የሚጣልባቸዉ ሆነዉ ባለመገኘታቸዉ እንደሆነ ዘገባዎች አመልክተዋል። የችሎቱ አቃቤ ህግ ፋቱ ቤንሱዳ የሙታዉራን ክስ ከማንሳት በቀር አማራጭ አለመኖሩን ገልፀዋል። ሆኖም የሌሎች ተከሳሾች ጉዳይ በተያዘበት ሁኔታ እንደሚቀጥል አሳስበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ