1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ምርጫ ዝግጅትና ውዝግቡ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 5 2009

ከአራት ሳምንታት በኋላ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የምታካሂደው የኬንያ መንግሥት ከፍትሑ አካል ጋር ንትርክ ውስጥ ገብቷል። የድምፅ መስጫ ወረቀቶቹ ሕትመት ለአንድ ከሃገር ውጭ ላለ ኩባንያ የተሰጠበትን ውሳኔ የኬንያ ከ/ፍ/ቤት ባለፈው ሳምንት ውድቅ ካደረገ በኋላ፣ ፕሬዚደንት ኬንያታ የፍ/ቤቱን ውሳኔ በማጠያየቅ ያሰሙት ወቀሳ ውዝግቡን አባብሶታል።

https://p.dw.com/p/2gOqO
Kenia Wahlkampf | Uhuru Kenyatta
ምስል Reuters/T. Mukoya

mmt kenya election controversy - MP3-Stereo

በኬንያ የፊታችን በጎርጎሪዮሳዊው ነሀሴ ስምንት ፣ 2017 ዓም  ለሚደረገው ፕሬዚደንታዊው ምርጫ የምርጫው ዘመቻ  ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ሆኖም፣ የሃገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ሕትመት ጨረታን በተመለከተ የተፈጠረው ንትርክ የምርጫውን ሂደት እንዳያሰናክል አስግቷል። የኬንያ ነፃ አስመራጭ እና የድንበር ማካለል ኮሚሽን፣ በምህጻሩ «አይኢቢሲ» ከጥቂት ጊዜ በፊት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ሕትመት ጨረታን መቀመጫውን ዱባይ ላደረገው « አል ጉሬር  » ኩባንያ የሰጠበትን ውሳኔ የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሽሮታል። ከፍተኛው ፍርድ ቤት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በምህጻሩ «ናሳ» የተሰኘው በራይላ ኦዲንጋ የሚመራው የተቃዋሚ ብሔራዊ ከፍተኛ ህብረት የድምፅ መስጫው ወረቀት ሕትመት ከፕሬዚደንት ኬንያታ ጋር የቅርብ ግኝኙነት አለው ለሚለው የ«አል ጉሬር» በመሰጠቱ በ«አይኢቢሲ» ላይ ክስ ከመሰረተ በኋላ ነው። 
ክሱን  የመረመሩት ሶስቱ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ጨረታው የተካሄደበት አሰራር ግልጽነት የጎደለው እና ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው በማለት ነበር 27 ሚልዮን ዩሮ የያዘውን ኮንትራት አሰጣጥ  ሂደት ውድቅ ያደረጉት፣ የፕሬዚደንታዊው ምርጫ የድምፅ መስጫ ወረቀት ሕትመት ጨረታም እንዲደገም የፈረዱት። ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን የሚወዳደሩት ኬንያታ የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ኬንያውያን በሙሉ፣ ዳኞች፣ አስመራጩ ኮሚሽን እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች በጠቅላላ ምርጫው ለነሀሴ ስምንት መታቀዱን በግልጽ እንደሚያውቁ በማስታወስ የተቃዋሚው ወገን ክስ እና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ጠቅላላውን ምርጫ ለማዘግየት የተወሰደ ሙከራ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን መልሶ እንዲያጤነው አሳስበዋል።
« የምርጫውን ዕለት ለመቀየር የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ አንቀበልም። ምክንያቱም ፣ ይህ የኬንያ ሕዝብ መሪዎቹን የሚመርጥበትን ሕገ መንግሥታዊ መብቱን መንፈግ ነው።»ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ኬንያታ  በዚህ ዓይነት አነጋገራቸው ሕዝቡ በፍትሑ አካል ላይ ያለውን እምነት እንዳይሸረሽሩ አስጠንቅቋል። የድምፅ መስጫ ወረቀቱን ሕትመት በተመለከተ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ስላስተላለፈው ውሳኔ እና ፕሬዚደንቱ ስለሰነዘሩት ወቀሳ ኬንያውያን የተለያየ አስተያየት ነው የሰጡት።
« ፕሬዚደንቱ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ማክበር አለባቸው። ምክንያቱም፣ ይኸው ፍርድ ቤት ነበር በ2013 ዓም ኡሁሩ ኬንያታ አንዳንድ ያልተስተካከለ አሰራር የታየበትን በዚያን ጊዜ የተካሄደውን ፕሬዚደንታዊ ምርጫ  አሸንፈዋል ሲል የወሰነው። »
« አዲስ ሕገ መንግሥት ስናወጣ ነፃ የፍትሕ አውታር እንዲኖር ነበር ፍላጎታችን። «ናሳ»ም ይህንን ይደግፋል። እና ማድረግ ያለብን ለማንም ያልወገነ፣ ለሕግ የበላይነት የሚሰራ እና የሚሟገት  የፍትሕ አካል እንዲኖር መታገል ብቻ ነው። »
« የፍትሑ አካል ስራውን እንዲሰራ መተው እና በሚሰራውም ስራ ትክክለኛነት መተማመን ነው ያለብን። »
ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በሃገራቸው የፍትሕ አካል ላይ የሰነዘሩትን ወቀሳ ተከትሎ የተፈጠረው ንትርክ የመጻዒውን ምርጫ ሂደት እንዳያስተጓጉል ለማከላከል በማሰብም ነበር አስመራጩ ኮሚሽን  ከፕሬዚደንታዊ እጩዎች ጋር የተገናኘው። ሆኖም፣ ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ የቀረቡት እጩዎች የድምፅ መስጫው ወረቀት ሃገር ውስጥ ወይም ከሃገር ውጭ ባለ ኩባንያ ይታተም አይታተም በሚለው ጥያቄ ላይ አሁንም እንደተከፋፈሉ ይገኛሉ።

Wahlen Kenia
ምስል DW
Kenia Oppositionsführer Musalia Mudavadi, Raila Odinga, Isaac Ruto, Kalonzo Musyoka, and Moses Wetangula  in Nairobi
የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች፣ ሙሳሊ ሙዳቫዲ፣ ራይላ ኦዲንጋ፣ አይዛክ ሩቶ፣ ካሎንዞ ሙስዮካ፣ ሞዘስ ዌታንጉላምስል Reuters/T. Mukoya

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ