1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ውዝግብና የአውሮጳ ኅብረት ዛቻ

ማክሰኞ፣ ጥር 6 2000

ኬንያ ውስጥ በፕሬዚደንታዊው ምርጫ የተነሳ የተፈጠረው ውዝግብ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

https://p.dw.com/p/E0Zr
ተቃውሞ በኬንያ
ተቃውሞ በኬንያምስል picture-alliance/ dpa

ትልቁ የኬንያ ተቃውሞ ፓርቲ፡ ኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ሙቭመንት መሪ ራይላ ኦዲንጋ በምርጫው ድላቸውን በወቅታዊው ፕሬዚደንት ምዋይ ኪባኪ እንደተነጠቁ በመግለጽ ደጋፊዎቻቸው ከነገ ጀምረው ተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ዛሬ በተከፈተው አዲሱ ምክር ቤት ውስጥ የተቃዋሚው ወገን እንደራሴዎች የመንግስቱን መንበሮች ለመያዝ ዝተዋል። ውዝግቡን ለማብቃት አሁን በቀድሞ የተመድ ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን የሚመራ አንድ የሽምግልና ተልዕኮ ይጀመራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። የምርጫው ውጤት ተቀባይነት የማያገኝና ቀውሱ የሚቀጥል ከሆነ የአውሮጳ ኅብረት ለዚችው ሀገር የሚሰጠውን የልማት ርዳታ ሊያቋርጥ እንደሚችል ዛቻ አሰምቶዋል።

የኬንያ ፕሬዚደንት ምዋይ ኪባኪ ባለፈው ታህሳስ አስራ ሰባት የተካሄደውን ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት በማጭበርበር ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን በቅተዋል በሚል በፕሬዚደንቱ እና በተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች መካከል በተነሳው ግጭት እስከዛሬ የሞተው ሰው ቁጥር ሰባት መቶ ደርሶዋል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩም በኪባኪ የኪኩና በኦዲንጋ የሉዎ ጎሳ ደጋፊዎች መካከል የተከተለው ግጭትም ሊያስከትለው የሚችለውን የበቀል ርምጃ ፈርተው ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ባለፈው ሳምንት ወቅታዊው የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀ መንበር የጋና ፕሬዚደንት ጆን ኩፎር እና ሌሎች አፍሪቃውያን መሪዎች፡ እንዲሁም፡ የዩኤስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪቃ ክፍል ረዳት ኃላፊ ጄንዳይ ፍሬዘር ያደረጉዋቸው የሽምግልና ጥረቶች ከከሸፉ በኋላ፡ በአሁኑ ጊዜ ተቀናቃኞቹን ወገኖች ለማስታረቅ በቀድሞው የተመድ ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን የሚመራ አንድ ቡድን ናይሮቢ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ኮፊ አንና በሚመሩት ቡድን ውስጥ የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚደንት ቤንጃሚን ምካፓና የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ ባልተቤት ግራሻ ማቼል ይገኙበታል፤ የኮፊ አናን የሽምግልና ጥረት ለኬንያ የሚበጅ አዎንታዊ ውጤት እንደሚያስገኝ ለኬንያ ትልቁን ርዳታ የሚያቀርበው የአውሮጳ ኅብረት ኮሚስዮን የልማት አስተባባሪ ክፍል ቃል አቀባይ ጆን ክላንሲ ዛሬ ለዶይቸ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።
« ኮፊ አናን በቅርቡ ኬንያ ይገባሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ባሁኑ ጊዜ ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተነቃቃውን ጥረት ይደግፋል። ኮፊ አናን ሁለቱ ወገኖች በአንድ ጠረጴዛ ዙርያ ተቀምጠው በውይይት አሁን በሀገሪቱ ለተፈጠረው ውዝግብ መፍትሄ - ብሎም ኬንያ ሰራሽ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማበረታታት የሚያደርጉትን ጥረት በርግጥ ይደግፋል። »
ኬንያውያኑ ተቀናቃኝ ወገኖች በመፍትሄ ፍለጋው ላይ እንዲተባበሩዋቸው አናን ጥሪ አቅርበዋል፤
ይሁን እንጂ፡ በኬንያ ሰፊ ተሰሚነት ያላቸው የሀገሪቱ መገናኛና መጓጓዣ፡ እንዲሁም የስራ ሚንስትር ጆን ሚቹኪ የዋና ጸሀፊው የሽምግልና ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው ነው ያስታወቁት።
« እኛ ማንንም አልጋበዝንም። ምርጫውን አሸንፈናል። ምርጫው የሚመለከተው ባለስልጣንም ይህንኑ ነው ይፋ ያደረገው። »
የኅብረቱ ኮሚስዮን የልማት ርዳታ አስተባባሪ ክፍል ቃል አቀባይ ሚስተር ጆን ክሌንሲ እንዳመለከቱት፡ ኮፊ አናን የሚጀምሩት አዲሱ የሽምግልና ጥረት ፕሬዚደንት ምዋይ ኪባኪንና ተቀናቃኛቸውን ራይላ ኦዲንጋን ማቀራረብ ካልቻለ ግን፡ የአውሮጳ ኅብረት ለኬንያ የሚሰጠውን የልማት ርዳታ ሊቀንስ ወይም ሊያቋርጥ ይችላል።
« ኅብረቱ የልማት ርዳታ አሰጣጥን በተመለከተ ከተጓዳኝ ሀገሮች ጋር በፈረመው የኮቶኑ ስምምነት አንቀጽ ዘጠና ስድስት መሰረት፡ ለኬንያ የሚሰጠው ርዳታ የሚቋረጥበት ሁኔታ አለ። ይህ አንቀጽ የልማት ርዳታ አሰጣጡን ተግባር ከመልካም አስተዳደር፡ ከምርጫ ሂደትና ከዴሞክራሲ ጋር ያስተሳስረዋል። የልማት ኮሚስዮኑ ተጠሪ ልዊ ሚሼል ትናንት በሽትራስቡርግ ለአውሮጳ ምክር ቤት እንደራሴዎች ባሰሙት ንግግራቸው የኬንያ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው በማስታወቅ ይህንን የኮሚስዮኑን አቋም ግልጽ አድርገዋል። ይኸው የኮቶኑ ስምምነት አንቀጽም የልማቱ ርዳታ እንዲቋረጥ እንደሚያስችል ነበር ያስታወቁት። »
ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ዓለም አቀፍ መለኪያዎችን ያልጠበቀ እንደነበረ ምርጫውን በታዛቢነት የተከታተሉ የውጭ ዜጎች ቢያመለክቱም፡ የምርጫው ውጤት ይፋ ከሆነ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አከራካሪውን ምርጫ አሸንፌአለሁ ሲሉ ቃለ መሀላ በፈጸሙት ፕሬዚደንት ምዋይ ኪባኪ አንጻር እስካሁን ድረስ አንድም የውጭ ሀገር ተቃውሞ አላሰማም።