1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ጊዚያዊ ሁኔታ ከጋሪሳ ጥቃት በኋላ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 3 2007

የኬንያ መንግሥት ባለሥልጣናት አራት የአሸባብ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ 148 ሰዎች የገደሉበትን ጥቃት አስቀድመው ማስቆም አለመቻላቸው ትልቅ ስህተት መሆኑን አመኑ። የኬንያ ፀጥታ ኃይላት ወዳካባቢው አንድ ፈጣን አጥቂ የፖሊስ ቡድን የላኩት ጥቃቱ ከተጀመረ ከሰባት ሰዓታት በኋላ ነበር።

https://p.dw.com/p/1F669
Kenia Garissa Universität Anschlag Trauer
ምስል picture-alliance/dpa/D.Irungu

ያካባቢው ዕለታዊ ጋዜጣ «ዘ ደይሊ ኑሽን» እንዳመለከተው፣ ፖሊስ በጊዜ ዩኒቨርሲቲው ደርሶ ቢሆን ኖሮ ምናልባት ጭፍጨፋውን ማስወገድ ወይም ቢያንስ የሟቾችን ቁጥር ዝቅ ማድረግ ይቻል እንደነበረ ተገምቶዋል። አራቱ የአሸባብ ታጣቂዎቹ ያገቱዋቸውን ተማሪዎች የማዳኑ ተግባር በጊዜ አለመድረሱን የኬንያ ፕሬዚደንታዊ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ማኖዋ ኤሲፒሱ አስታውቀዋል።

« በጋሪሳ ስህተት ሰርተናል ወይ? አዎ፣ ሰርተናል። ከዚሁ ስህተታችን ግን ትምህርት አግኝተናል። ስህተት የማይሰራው ጥቃቱን በየት እና መቼ እንደሚጥል የሚያቅደው አሸባሪ ብቻ ነው። አንተ ጥቃቱን ለማስቆም ርምጃ መውሰድ ነው የምትችለው፣ እና ይህንኑ ርምጃ በማስተባበሩ ወቅት፣ ስለሁኔታው ትክክለኛ መረጃ ስለሌለህ፣ ጊዜ ማጥፋትህ አይቀርም። »

Kenia Garissa Universität Anschlag Trauer
ምስል Getty Images/AFP/de Souza

የኬንያ መንግሥት በሀገሩ ህብረተሰብ ውስጥ ካለፉት ዓመታት ወዲህ አክራሪነት እየተጠናከረ መምጣቱን ከተገነዘበ ወዲህ የፀጥታ ጥበቃ ርምጃውን ማጠናከሩን አስታውቋል፣ በሀገራቸው አክራሪነት እየተጠናከረ ለተገኘበት ሁኔታ ትኩረት የሰጡት ከፍተኛ የገዢው ፓርቲ ባለሥልን እና የኬንያ ምክር ቤት እንደራሴ አደን ዱዋሌ እንዳስረዱት፣ ከሁለት ዓመት በፊት አንዳንድ ሙሥሊም መንፈሳውያን በሞምባሳ ወደብ ከተማ የሚገኙ መስጊዶችን ፅንፈኛ የእሥልምና ርዕዮትን ለመስበኪያ ሳይጠቅሙባቸው እንዳልቀሩ ከተሰማ በኋላ የፀጥታ ኃይላት መስጊዶችን ዘግተዋል።

« አንዳንዶቹ ተቋማት በወጣት ሙሥሊሞች ዘንድ አክራሪነትን የሚያጠናክረው ርዕዮት መስፋፋት ላይ ሚና አላቸው። ይህ ፈታኝ ጉዳይ የደቀነውን ስጋት ለማጥፋትም በሀይማኖት አክራሪነት ተግባር የሚጠረጠሩትን ግለሰቦች እና ተቋማት በቅርብ እንከታተላለን። »

Garissa Kenia Soldaten

የኬንያ ባለሥልጣናት የሶማልያ ዓማፂ ቡድን አሸባብ በኬንያ የሽብር ጥቃትን ለማስቆም ጥረት በያዙበት በዚህ ወቅት በጋሪሳው ጥቃት ልጆቻቸው እና ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸው ቤተሰቦች ወደመዲናዋ ናይሮቢ የቺሮሞ ማዕከል ከተወሰዱት የተማሪዎቹ አስከሬኖች መካከል የልጆቻቸውን በመለየቱ አዳጋች ተግባር መጠመዳቸውን የማዕከሉ ኃላፊ ዶክተር ሶቢ ሙሉንዲ ገልጸዋል።

« በአሁኑ ጊዜ 97 አስከሬኖችን ሰብስበናል። የአንዳንዶቹን ማንነት በርግጥ ለይቶ በማወቁ ተግባር ላይ ችግር አጋጥሞናል።»

በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ላይ የተጣለውን የአሸባሪዎች ጥቃት ተከትሎ የኬንያ መንግሥት በመላ ሀገሩ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጥበቃ ማጠናከሩን አስታውቋል። ይሁንና፣ የኬንያ ዩኒቨርሲቲዎች ህብረት ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቻርልስ ሙክዋዬ የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ የሚገኝበት ሰሜን ም ሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢ አሁንም አደገኛ ቦታ የማያስተማምን ቦታ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ