1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮህለር የአፍሪቃ ጉብኝትና የሞዛምቢክ ኤኮኖሚ

ሐሙስ፣ መጋቢት 28 1998
https://p.dw.com/p/E0du
የጀርመኑ ፕሬዚደንት ማፑቶ አየር ጣቢያ ሲደርሱ
የጀርመኑ ፕሬዚደንት ማፑቶ አየር ጣቢያ ሲደርሱምስል picture-alliance / dpa/dpaweb

የጀርመኑ ፕሬዚደንት ሆርስት ኮህለር “ለአፍሪቃ የልማት ሽርክና” በሚል መርህ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ትብብር እንዲሰፍን ሃሣብ ከመጸነስ ባሻገር ከጥቂት ወራት በፊት በዚህ በቦን የተወሰኑ የአፍሪቃ መንግሥታት መሪዎችንና ጠበብትን ጋብዘው ማነጋገራቸው ይታወሣል። ኮህለር አሁን ለሁለተኛ ጊዜ በአፍሪቃ የሚያደርጉት ጉብኝት መሠረተ-ዓላማም ይሄው ነው።

ፕሬዚደንት ኮህለር ባለፉት ቀናት የሞዛምቢክ ጉብኝታቸው ደቡብ አፍሪቃይቱ አገር የምታደርገውን የልማት ዕርምጃ በማወደስ የጀርመንን ባለሃብቶች ልትስብ የምትችልበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሆነ አመላክተዋል። በእርግጥም ሞዛምቢክ እንደ ሌላዋ የቀድሞ የፖርቱጋል ቅኝ ግዛት እንደ አንጎላ ሁሉ በወቅቱ ግሩም በሆነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ነው የምትገኘው። አሁንም ድህነትና የልማት እጦት መለያው ለሆነው ክፍለ-ዓለም የዕድገት አርአያ መባል ጀምራለች።

ሞዛምቢክ እ.ጎ.አ. በ 1992 ዓ.ም. አስከፊ ከነበረው የእርስበርስ ጦርነት ከተላቀቀች ወዲህ ወዲያው ብዙ ሳይቆይ ለበጎ አስተዳደር ቁልፍ የሆነውን ነጻ ምርጫ ለመካሄድ ችላለች። ዓመታዊ የኤኮኖሚ ዕድገቷ በአማካይ 8 ከመቶ መጠን ላይ ደርሷል፤ የኑሮው ውድነትም ከሌሎች ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። ምዕራባውያኑ ለጋሽ መንግሥታት ደግሞ በቅርቡ ሙሉ የዕዳ ምሕረት በማድረግና ዕርዳታቸውን ከፍ በማድረግ እርካታቸውን ሲገልጹ ከነዚሁም አንዷ ጀርመን ናት። ወደፊት ሃብት በሥራ ላይ ለማዋል አመቺው ሁኔታ እንደሚፈጠር ታላቅ ተሥፋ ጥለዋል።

ለመሆኑ በወቅቱ ወይም በመጪዎቹ ዓመታት ጀርመናውያን፤ በአጠቃላይም ምዕራባውያን ባለሃብቶች ገንዘባቸውን አስተማማኝ በሆነ መንገድ በተግባር የማዋላቸው ዕድል እስስከምን ድረስ ነው? እርግጥ በጎ አስተዳደር ሰፍኖ መቀጠሉ፣ ቢሮክራሲ መወገዱና ጸረ-ሙስናው ትግል ፍሬ መስጠቱ የውጭ ሃብትን ለመሳብ ለዘለቄታው ወሣኝነት ይኖራቸዋል።
ለረጅም ጊዜ በቱሪዝምና በሆቴል ግንባታ ተግባር ተሰማርተው የሚገኙ የደቡብ አፍሪቃ ባለካፒታሎች ሞዛምቢክን ከዛሬው የዕድገት፤ የብልጽግና አገር ይሏት ጀምረዋል። ሰፊ የምጣኔ-ሐብት ዘርፍ የልዑካን ቡድንን አስከትለው ወደ አፍሪቃ የተጓዙት የጀርመኑ ፕሬዚደንት ሆርስት ኮህለርም ለአገራቸው ባለሃብቶች ጥሩ ዕድል ነው የሚታያቸው።

“ለጀርመን ወይም ለሌሎች የውጭ ባለሃብቶች ጥሩ ዕድል ነው ያለው። ግን እነዚህ የካፒታል ባለቤቶች አጠቃላዩ ሁኔታ በጀርመን፣ በፈረንሣይ ወይም ከአውሮፓ ካለው የተለየ መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል። ሁኔታው ገና ከበድ ያለ ነው። ግን አገሪቱ በጥሩ ዕርምጃ ላይ መሆኗም ግልጽ ነው” ኮህለር እንደተናገሩት!

ለዚያውም ኮህለር እንዳሉት በትክክኛው መንገድ! የሞዛምቢክ መንግሥት ባለሃብቶች ወደ አገር ገንዘብ የሚያስገቡበትን ሁኔታ ማራኪ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ ለማመቻቸት እየጣረ መሆኑ ነው የሚነገረው። በአገሪቱ ሕጋዊ የአስተዳደር ሥርዓት እየተስፋፋ ለመሆኑም ሞዛምቢክ በትራንፓረንሢይ ኢንተርናሺናል የሙስና መስፈርት ዝርዝር ላይ ከሁሉም በታች በዝቅተኛ ደረጃ መገኘቷ ጥሩ ምሥክር ነው።

እርግጥ በሚገባ ድህነትን ለመታገል ፍቱን ሆኖ የሚንቀሳቀስና የሚያድግ ኤኮኖሚ ማስፈኑ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ አያጠራጥርም። ተጨባጭ ዕድገት የሚገኘው ደግሞ ገንዘቡ በጤና ጥበቃና ትምሕርትን በመሳሰሉት ማሕበራዊ ዘርፎች በሥራ ላይ ሲውል ነው። ሞዛምቢክ ውስጥ በወቅቱ በዚህ አቅጣጫ አበረታችጥረት መያዙ የሚታይ ቢሆንም በሌላ በኩል ግን መንግሥት ገና ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል።

ችግሩን ለማቃለል ገና ቢያንስ 15 ሺህ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ይጎላሉ፤ በጤና አገልግሎቱ ዘርፍም የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ብዙ ነው የሚቀረው። በጎ አስተዳደርን በተመለከተም ፕሬዚደንት ኮህለር የሞዛምቢክን አመራር ያወድሱ እንጂ ገና ብዙ ይቀረዋል የሚሉ ተቺዎችም አልታጡም። ለምሳሌ ሞዛምቢክ ውስጥ ሳያስተጓጉሉ ለመንግሥት ግብር የሚከፍሉት አምራቾች ከአምሥት በመቶ አይበልጡም። የተቀረው በጉቦ ከግዴታው የሚያመልጥ ነው። በየዕለቱ በር በሚያንኳኩ የመንግሥት ተቆጣጣሪዎች ጭ’ቅጭቅ ተመረርን የሚሉም አልጠፉም።

እንደሚባለው ሞዛምቢክ ውስጥ ሙስና በመንግሥቱ መዋቅር ከላይ እስከታች የተሥፋፋ ትልቅ ችግር ነው። ያለጉቦ ወይም ጥሩ ግንኙነት አንዳች ነገር ለማስቀሳቀስ አይቻልም። ለነገሩ የጀርመን መንግሥት ከሞዛምቢክ ጋር የባለሃብቶች ንብረት ዋስትና ውል ለመፈራረም ሲጥር ቆይቷል። የውሉ ረቂቅ ተጠናቆ መቅረቡም አልቀረም። ይሁንና እስከዛሬ ጸድቆ ለመጽናት አለመብቃቱ ነው ችግሩ። ፕሬዚደንት ኮህለርን ያጀቡት የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ዘርፍ ተጠሪዎች ይሄው ውል በወቅቱ ጉዟቸው ዕውን እንደሚሆን ተሥፋ ጥለው ነበር ወደ አፍሪቃ ያመሩት።