1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አገሪቱ ሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ በተመለከተ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ትገኛለች»ኮሚሽነር ሁሴን

Merga Yonas Bula
ዓርብ፣ ሚያዝያ 27 2009

የተባበሩት መንግሥታ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራኣድ ኣል ሁሴን በመንግሥት ጋባዥነት በኢትዮጵያ የሠስት ቀናት ጉብኝታቸዉን አጠናቀዋል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣዉ መቅረቡ እንዳስገረማቸዉ የተናገሩት ኮሚሽነሩ በቆይታቸዉ፤ ከባለስልጣንናት እስከ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ያሉትን አግኝተዉ እንዳነጋገሩ ለዶይቼ ቬሌ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2cUEQ
Äthiopien DW-Interview UN-Menschenrechtler Seid al-Hussein
ምስል DW

Exlusive Interview with HC Hussein - MP3-Stereo

«ታዋቂ» ያሏቸዉን የፖለትካ እስረኞችም አግኝተዋል። አገሪቱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ አስጊ ሁኔታ ዉስጥ ብትገኝም ከመንግሥት ጋር ለመሥራት ተስፋ እንዳለቻዉም አመልክተዋል። ኮሚሽነሩን በተለይ ከዶቼ ቬለ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ያነጋገራቸዉ መርጋ ዮናስ ነዉ።

ዶይቼ ቬሌ :- በቅድሚያ አመሰግናለሁ፤ በኢትዮጵያ ባደረጉት የሦስት ቀናት ቆይታ ዉስጥ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ምን አስተዋሉ? ምንስ ታዘቡ?

ኮሚሽነር ሁሴን :- አገሪቱ ሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ በተመለከተ አሳሳቢ ሁኔታ ዉስጥ ትገኛለች። መንግሥት እኔ አገሪቱን እንድጎብኝ መጋበዙ አስገርሞኛል። ምክንያቱም ብዙ አገኝች የተባበሩት መንግሥታ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽንን ትኩረት ለማገኝት አይፈልጉም። ጉብኚቴም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይፋ ካደረገዉ ሁለተኛ ዘገባዉ ጋር ተገጣጥሟል። ያዉ እንደምታዉቀዉ ይህ ዘገባ ሙሉ በሙሉ ነጻ ባይሆንም ኮሚሽኑ ከተመሠረተ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ትልቅ ቦታ እያገኘ መጥቷል። በተጨማሪም ከሁለተኛዉ የመንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ተግራዊ ዕቅድ ጋርም ተገጣጥሟል። እንደ ሌሎቹ ሁሉ ለእኔም የማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶችን በተመለከተ መሻሻሎች መኖራቸዉ ግልፅ ነዉ። አሁን ጉድለቱ ያለዉ የሲቪክ ማኅበረሰቡን ማቀፍ፣ ለነፃ ፕሬስ መፈናፈኛ መስጠት፣ እናም የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ሙሉ ነፃነት እንደኖረዉ  ማድረጉ ላይ ነዉ።

ከመንግሥት ባለስልጣናት ከተቃዉሞ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ጥልቅ ዉይይት አድርገናል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም የጠበቀ ግኑኝነት እንዳላቸዉ መታዘብ ችያለዉ። እስር ቤቶችን ለመጎብኘት ችያለሁ፣ እዛም በአገሪቱ የታወቁ የፖለቲካ እስረኞችን አግኝቻለሁ፣ ስለ ኢትዮጵያም ረዥም ዉይይት አድርገናል። በመጨረሻ ላይም ኢትዮጵያ አስጊ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አምኛለሁ። መንግሥትም በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ፣ በሲቪልም ሆነ በፖለቲካ መብቶች፣ በጥልቀት መሥራት እንዳለበት ለመረዳት ችያለዉ።

ዶይቼ ቬሌ :- በቆይታዎት «ታዋቂ» የፖለቲካ እስረኞችንና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን እንዳገኙ አጋርተዉኛል። የመወያያ አጃንዳችሁ ምን ነበረ?

ኮሚሽነር ሁሴን :- በመሠረቱ እኔ ላገኘኋዉና ላዳመጥኳቸዉ ሰዎች የነበረኝ ጥያቄ በኢትዮጵያ አሁን ያለዉን ሁኔታ እንዴት እንደሚመለከቱትና ምን አይነት ምክር እንደምሰጡኝ ነበር። ይህን ተመሳሳይ ጉዳይ ለሲቪል ማኅበራትም በግልም ሆነ በአደባባይ አንስቻለዉ። ይሄንንም ያደረግ ነዉ ባጠቃላይ ያለዉ ችግር ለመመርመር እና በቀጣይ መፍትሄ ለመስጠት ምን መደረግ አለበት የሚለዉ ላይ ሰፋ ያለና ሙሉ እይታዎች ለማዳመጥ ነበር። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተፈፀሙትን የመብት ጥሰቶች ለመመርመር ብዙ ጥያቄዎችን አቅርበን ነበር። በጋዜጣዊ መግለጫዬ እንደጠቀስኩትም የእኔ መርማሪ ቡድን በክልሎቹ ሄዶ ጉዳዩን እንዲመረምር መንግሥት እንዲፈቀድልኝ ዳግም ጥያቄዉን አድሻለዉ። ይህም በቦታዉ የተፈፀመዉን እንድንረዳ ያደርጋል። ኮሚሽኑ ያወጣዉን ዘገባ የሚያጣራ ገለልተኛ የሆነ አካል ባለመኖሩ የተባለዉን እንደልማልደግፍ ለባለስልጣናቶች ግልፅ አድርግያለዉ። ለዚህ ነዉ በድጋሚ ጥያቄዉን ያቀረብነዉ።»

ዶይቼ ቬሌ :- በእስር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግርስ አመራር አቶ በቀለ ገርባንና ዶክተር መረራ ጉዲናን እንዳገኙ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ይህን ሊያረጋግጡልን ይችላሉ?

ኮሚሽነር ሁሴን :- «ማንን እንዳገኘሁ ላረጋግጥልህ አልችልም። ምክንያቱም የነሱን ፊቃደኝነት ማገኘት አለብኝ። ስለዚህ ማንነታቸዉን መጥቀስ ለእኔ ትክክል ሆኖ አይታየኝም። ግን ሁሉም ዉይይታችን መልካም ነበር። እናም እኔ የማንነዉ ኢትዮጵያ አስጊ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ነዉ። »

ዶይቼ ቬሌ :-  ላለፉት ሰባት ወራት በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደታወጀ ነዉ። አገሪቱም በኮማንድ ፖስት እየተዳደረች ትገኛለች። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ ነዋሪዎች ይናገራሉ። እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ይህን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?

ኮሚሽነር ሁሴን :- «አለመረጋጋቱ መከሰቱን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የያዘ ሪፖርት እንደሌሎቹ እኛም አግኝተን ነበር። ግን ይህን ማጣራት የምንችለዉ ችግሮቹ በተከሰቱት አካባቢ መድረስ ስንችል ብቻ ነዉ። ግን ከተከለከለን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማትን የማግባባት ስራ መስራት ነዉ። አሁን የምናደርገዉ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበዉን ሁለተኛዉን ሪፖርት እንወስዳለን፣ ከዛም በጥናቃቄ እናነባለን። በጥር ወር ተመልሰን እንመጣለን ብለን ተስፋ አድርገናል፣ በዚህ ጊዜም የምንደርስበትን ከመረመርኩ በኋላ፣ በዛን ሰዓት ችግሮቹ ባሉበት መድረስ እንድንችል ይፈቀድልናል ብዬ ተስፋ አደርጋለዉ። በዚህ ላይ ቆመንም መንግስት ለሲቪል ማኅበራት፣ ለነጻ ፕረስና ለኛ የበለጠ በር እንዲከፍትልን እንጠይቃለን።»

ዶይቼ ቬሌ :- በዘገባዉ ዉስጥ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ከ600 በላይ ሰዎች ሕይወታቸዉን እንዳጡ፤ የተወሰደዉ ርምጃም «ተመጣጣኝ» መሆኑን ጠቅሷል። እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር በተቃዉሞ ወቅት መንግሥትን የወሰደዉን ርማጃና በዘገባዉ የቀረበዉን እንዴት ይመለከቱታል?

ኮሚሽነር ሁሴን :- « እስካሁን ዘገባዉን አላነበብኩም፣ ግን ቁጡሩን ማየት ችያለዉ። ቁጡሩ የሚያመለክተዉም እዉነተኛ ቅሬታ፤ እዉነኛ ቁጣ በኅብረተሰቡ በኩል እንደነበረና ነገሮችም በትክክለኛዉ መንገድ እንዳልሄዱ ነዉ። እርግጥ ነዉ መጀመርያ እኛም ዘገባዉን ማንበብ አለብን፣ በቀጥታ ተሰታፍ የነበሩ ሰዎችንና ቤተሰቦችን እንድናገኝና እንድናናግር ፍቃድ እንዲሰጠንን እንጠይቃለን። ከዚያም የራሳችንን ምርመራና ትንታኔ እናደርጋለን። እናም ለዚህም መንግሥት ፍቃዱን ይሰጡናል የሚል ተሰፋ አለኝ።»

ኮሚሽነር ሁሴን ግዜዎን ወስደዉ ለሰጡን ቃለ ምልልስ ከልብ አመስግናለዉ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ