1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮምፒተር ጠበብትና የመገናኛ ሥነ ቴክኒክ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2006

በየዓመቱ የሚዘጋጀው የጀርመን የኮምፒዩተር ጠበብት ጉባዔ ፣ ዘንድሮ በጀርመን ግዙፍ የወደብ ከተማ ፣ በሃምበርግ፤ 30ኛውን ዐቢይ ስብሰባ፣ ከታኅሣሥ 18 እስከ 21 ፤ 2006 ዓ ም፣ አካሂዷል። አምና በበርሊኑ ጉባዔ የተሳተፉት ጠብብት 4,500

https://p.dw.com/p/1Amtd
Deutschland Kongress Chaos Computer Club in Hamburg
ምስል AP

ገደማ ነበሩ፤ በዘንድሮው ግን 800 ገደማ ሊገኙ ይችሉ ይሆናል ተብሎ ቢገመትም፤ ከ 900 በላይ ነበሩ ለመሳተፍ የቻሉት። ዘንድሮ ፣ አያሌ ተሳታፊዎች ለመገኘት የበቁበት ምክንያት፤ ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር ኤድዋርድ ስነውደን በተባለ አሜሪካዊ የቀድሞ የብሔራዊ ስለላ ድርጅት ሠራተኛ ፣ ካገር ወጥቶ ፣ መንግሥት ፣ አላግባብ እጅግ በዛ ያሉ ሰላማዊ ሰዎችን የኮምፒዩተር የግል መረጃ ሰነድ ይበረብራል ሲል ካጋለጠ ወዲህ የብዙዎቹን የኮምፒዩተር ሊቃውንት ትኩረት በመሳቡ ነው ተብሏል። Chaos Computer Club (CCC) በመባል የታወቀው ድርጅት ፣ የዘንድሮው 30ኛው የኮምፒዩተር ጠበብት ጉባዔ «የስነውደን ዓመት» ከተሰኘው አገላለጽ ጋር ተያይዞ ፣ የጠበብቱን ብቻ ሳይሆን ፣ የብዙዎችን ዜጎች ትኩረት ሳይስብ አልቀረም።

የጉባዔው አዘጋጅ የሆነው C C C ቃል አቀባይ፣ Constanze Kurz በዘንድሮው ጉባዔ ላቅ ያለ ግምት የተሰጣቸው የፖለቲካና የሥነ ቴክኒክ ጉዳዮች የትኞቹ እንደነበሩ እንዲህ የሚል መግለጫ ነበረ የሰጡት።

«እንደሚመስለኝ፤ ስነውደንና ይፋ የወጡት ጉዳዮች፣ የዘንድሮውን መወያያ ጉዳይ በማዕከላዊነት እንደያዙት ናቸው። በአንድ በኩል፤ ሥነ-ቴክኒኩን አያያዝ መመርመርና መተንተን፤ሆኖም ግን የዚህን ተቃራኒ መፈልሰፍ ሠርቶ ማቅረብን ይጠይቃል። በፖለቲካው መስክ እንደሁ ያን ያህል የምንጠብቀው ርዳታ የለም። ስለዚህም ራሳችን ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳችንን በሥነ-ቴክኒክ መርዳት ይኖርብናል። »

Elektronik Messe in Las Vegas Gerät Mother
ምስል picture-alliance/dpa

የ CCC መሥራች አባል Klaus Schleisiek ስለ ኮምፒዩተር ዓዋቂዎች በጀርመን የነበረውን አስተሳሰብና አሁን ያለውን ግንዛቤ በማያያዝ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«በጀርመን ሃገር ስለ ኮምፒዩተር አዋቂዎች የነበረው አስተሳሰብ፣ «የሃር ጎዳና» በተሰኘ የኮምፑዩተር ልዩ አገልግሎት መሥመር በከፊል የሚጠቀሙ መጥፎ ሰዎች የሚል ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህን መሰሉ አመለካከት ተለውጦ ፣ አሁን የኮምፒዩተር ጠበብቱን ፣ በኢንተርኔት ምን እንደሚደረግ የሚያውቁ የሥነ ቴክኒክ ልሂቃን የሚያሰኝ ስያሜ አስገኝቶላቸዋል። »

በእንግሊዝኛው አጠራር፤ «ኬዎስ ኮምፒዩተር ክለብ» የተሰኘው የሥነ ቴክኒክ ባለሙያዎች ማኅበር፣ ጠበብት የተሰባሰቡበት የመረጃ መለዋወጫ ክለብ ሲሆን ፣ በዓለም ዙሪያ ሰብአዊ መብት እንዲከበር፤ ያለገደብ የመገናኛና መረጃ አገልግሎት እንዲያገኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጥርም ነው። ሥነ ቴክኒክ ፣ በሕብረተሰብ ላይ ያለውንም ሆነ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ይከታተላል። ዋና ጽ/ቤቱ በሐምበርግ የሚገኘው ማኅበር

ከ 4,500 በላይ አባላት እንዳሉት ነው የሚገልጸው። የኮምፒዩተር ሥነ ቴክኒክ ጠበብቱ ማኅበር ፣ ከአባላቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ጋር ተባባሮ እንደሚሠራ ነው የሚገልጸው።

Eine Anzeige der Hisense Fernsehbildschirmen
ምስል Reuters

ሥነ ቴክኒክ በአመዛኙ ለብዙ ነገሮች ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ከቶውንም የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ለደኅንነት ሲባል የሚወሰዱ እርምጃዎች አላስፈላጊ የብዙ ሰላማዊ ሰዎችን የግል የመረጃ ሰነድ የመጠበቅን መብት እንዳሳጣ የስነውደን የማጋለጥ እርምጃ እንደጠቆመ ነው የሚነገረው። በመሆኑም በተለያዩ ሃገራት ዜጎች ፣ መንግሥታት የዜጎችን የመረጃ ሰነድ የመጠበቅ ምሥጢር እስከምን ድረስ በማክበር ላይ ናቸው የሚለውን ጥያቄ በማንሳት መከራከራቸው አልቀረም። CCC እንደሚያስረዳው፤ ካለፈው ዓመት ከሰኔ ወር ወዲህ፤ መንግሥታት ያላንዳች ገደብ የተጠቀሰውን ጉዳይ በተመለከተ ከመሰለል የቦዘኑበት ጊዜ የለም። ለመንግሥት ሥጋት ያልሆኑ ዜጎች የስልክ፤ ኢንተርኔት ኢ-ሜይልና ሌሎች የመገናኛ ዓይነቶች በድብቅ መመርመራቸው ተደርሶበታል ነው የተባለው። ለዚህም ነበረ፣ CCC እንዳለው፤ ከ 100 ከሚበልጡ ሃገራት የተውጣጡ 300 የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ ከእርሱ ጋር በመተባበር ፤ የግልሰቦችን መረጃም ሆነ የግል ምሥጢሮችን የመጠበቅ መብት እንዲከበር የጠየቁት። ከዚህም ጋር በተያያዘ ማኅበሩ 13 ነጥቦችን ያዘሉ ጥያቄዎችን ማቅረቡን ነው ያስታወቀው።

የኮምፒዩተር ሥነ ቴክኒክ ጠበብት ሥልጣን ላይ ላለ መንግሥት ከሚያገልግሉት ሌላ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ፤ ሕብረተሰቡ ፤ ለመብቱም ለእውቀትም እንዲነቃ የሚያግዙ ፤ የሚታገሉና የሚያታግሉ የመኖራቸውን ያህል፤ ለራሳቸውም ሆነ ለወከላቸው ወገን በመቆም፤ በሥነ ቴክኒክ ሥርቆት ላይ ያተኮሩ ጠበብትም አሉ። የእነዚህ የኮምፒዩተር ጠበብት የሥነ ቴክኒክ ሥርቆት፤ በያመቱ 400 ቢሊዮን ዶላር ኪሣራ እንደሚያስከትል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ሥርቆታቸው ይበልጥ የሚያተኩረው በፈጠራ ውጤቶች ወይም ግኝቶች ምሥጢር እንዲሁም በባንክ ሂሳብ ካርዶች ላይ ነው። በኮምፒዩተር ፤ የተለያዩ የተከማቹ መረጃዎችን ፤ የ «ኢ-ሜይል»አድራሻዎችንም ይሠርቃሉ።

ይም ሆኖ ፤ የኮምፒዩተር መረጃ ሠርሣሪዎችን ተግባር የሚገቱ የተለያዩ መከላከያዎችን በማቅረብ ረገድ የተካኑ ጠበብትም አሉ።

ያም ሆነ ይህ፤ የ 21ኛው ክፍለ ዘመን ሥልጣኔ፤ ይበልጥ በዚያው የሚገፋ እንጂ ከኮምፒዩተርና ከመሰል የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ መሣሪያዎች የሚያፈነግጥ እንደማይሆን ሂደቶች ይጠቁማሉ።

Ein Schwinn CycleNav
ምስል Reuters

የቀጠለው ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የኤሌክሮኒክስ መሣሪያ ምርቶች ውድድር ተንቀሳቃሽ ስልክ፤ ኮምፒዩተርና ሌሎችም ዘመናዊ የመገናኛ ዓይነቶች ከዓመት ዓመት እየተሻሻሉ እንደሚቀርቡ የታወቀ ነው። በመነሻችን ላይ ያወሳነው ጥቅምና ጉዳት እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። የተጠቀሱትን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ትርዒት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማቅረብ የታወቁት 3 ቦታዎች ናቸው ፣ አንደኛ ፣ ከትናንት አንስቶ እስከ ፊታችን ዓርብ ትርዒት የከፈተችው፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኔቫዳ ምድረበዳ የምትገኘው የጨፌ ከተማ ላስ ቬጋስ ናት። የምታዘጋጀው ፤ ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትርዒት የገዢዎች የኤሌክትሮኒክስ ትርዒት (Consumer Electronics Show-CES)ይሰኛል።

3,000 ያህል ትርዒት አቅራቢ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበትና፣ 150,000 ያህል ጎብኝዎች ጎራ እንደሚሉበትም ይጠበቃል። ትርዒቱ ከመዘጋጀቱ በፊት፤ 20,000 ያህል አዳዲስ የኤሌክትሮኒስ መሣሪያዎች ለእይታ ሳይቀርቡ እንደማይቀሩ ሲነገር ነበረ የከረመው።

የኮምፒዩተር መጽሔት መሪ አዘጋጅ ፎልከር ዞታ እንዲህ ነበረ ያሉት---

«በ ሸማቾች/ገዢዎች የኤሌክትሮኒክስ ትርዒት(CES)ፈጣን ንዑሳን የኮምፒዩተር ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ሰጪ የኤሌክትሮኒክስ ደብተሮች፤ ከ«ዊንደውስ» ጋር የሚሠሩ ሊሆኑ ይችላሉ ሌሎች በአንድሮይድ የሚሠሩና ረከስ ባለ ዋጋ የሚሸጡም አይታጡም። የደራ ገበያ ያለውና ያለማቋረጥ በ CES በብዛት የሚታየውም ይኽ ነው ሊሆን የሚችለው።

2ኛው የባርሴሎናው ፣ «ሞባይል ወርልድ ኮንግረስ »በመባል የታወቀው ሲሆን ከየካቲት 16-20፤ 3ኛው በጀርመን ሀገር በሃኖፈር ከተማ የሚዘጋጀው CeBIT የተሰኘው ተመሳሳይ ትርዒት ደግሞ ከመጋቢት 1-5 ፣ ይሆናል የሚካሄደው።

USA Elektronik Messe CES in Las Vegas
ምስል Reuters

በላስ ቬጋሱ ትርዒት፣ የኮምፒዩተር «ቺፕ» በመሥራት የታወቀው ግዙፍ ኩባንያ «ኢንቴል» ወደ ተንቀሳቃሽ ስልክ በተለይም ከልብስ በታች ወይም በላይ፣ ከሰው አካል ጋር በሚያገኙት ሙቀት በሚሠሩ ረቂቅ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ላይ ማትኮሩ ነው የተነገረው። ሌላው በላስ ቬጋሱ ከቀረቡት አስደናቂ ከተሰኙት የኤልክትሮኒክስ ውጤቶች መካከል፤ በአንድ የፈረንሳይ ኩባንያ ተሠርቶ የቀረበው ከ 16 ሴንቲሜትር የማይበልጥ መጠን ያለው የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ሲሆን ቤት ውስጥ 24 ያህል ተግባራት ማከናወንም ሆነ መቆጣጠር የሚያስችል ነው።

አትክልቶች ፤ አበባዎች ወሃ መጠጣት አለመጠታቸውን ፤ የቤተሰብ አባላት ሃኪም ያዘዘላቸውን መድኃኒት በጊዜው ወስደዋል አልወሰዱም ጥርሳቸውን ፍቀዋል አልፋቁም፣ እነዚህንና የመሳሰሉትን የሚያስታውስ ነው ስሙም ፣ ቀልድ ነው የሚመስለው ፤ «እናት» (Mother)ተብሏል።

በሌሎቹ ሁለት የአውሮፓ ዐበይት የኮምፒዩተር ትርዓት ማሳያ ማዕከላትስ ምን ይቀርብ ይሆን? ወደፊት የምናየው ይሆናል።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ