1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንዶም ግብይት በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ

ዓርብ፣ መጋቢት 12 2006

ያልተፈለገ እርግዝናን እና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ኮንዶም በዋነኝነት የሚጠቀስ መከላከያ ነው። ለመሆኑ የኮንዶም ግብይት በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/1BTSR
Symbolbild - Kondome
ምስል Fotolia/Sergejs Rahunoks

የወሊድ መከላከያ መድሓኒቶችን የመከላከያውን ላስቲክ ወይም ኮንዶም ግብይትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ከመጠየቃችን በፊት ለዚህ ዝግጅት መነሻ ወደሆነችን የሶማሊያ መዲና ሞቃድሾ እናምራ። አሁን ድረስ ሞቃድሾ ውስጥ የወሊድ መከላከያ መጠቀም፤ ስነ ምግባር የጎደላቸው ምዕራባዊያን ተግባር ነው ብለው የሚያምኑ ዜጎች አሉ። ስለሆነም በርካታ ወጣቶች ደፍረው የሚፈልጉትን ፅንስ ተከላካይ መድሀኒትም ሆነ ላስቲክ መግዛት አልቻሉም። ታድያ አንድ የመድሓኒት ቤት ባለቤት ለነዚህ ወጣቶች አንድ ሃሳብ አለው።

በሶማሊያ መዲና ብዙም ከቤተ መንግሥቱ እና ከምክር ቤቱ ራቅ ሳይል የጃማ ኢሳክ መድሓኒት ቤት ይገኛል። የመድሓኒት ቤቱን አድራሻ ብዙዎች ያውቁታል። የ27 አመቱ ጃማ ከራስ ምታት መድሓኒት እና ሌሎች ጥቂት መድሓኒቶች ባሻገር እንደ ኮንዶም እና ሌሎች የርግዝና መከላከያዎች ለደንበኞቹ ያቀርባል።« ኮንዶም መግዛት የሚፈልገ ሰው ጮክ ብሎ አይናገርም። አብዛኛውን ጊዜ እንዳማክረው ወደ በራፉ ወጣ እንላለን። በዚህን ጊዜ ሌሎች ደንበኞች ምንም አይሰሙም።»

Syrien Apotheke in Damaskus
ምስል Anwar Amro/AFP/Getty Images

ከዚህም ሌላ የመድሓኒት ቤቱ ባለቤት ስልክ ቁጥሩን የመድሓኒት ቤቱ በር ላይ ለጥፏል። በዚህ አማካኝነት ብዙ ወጣቶች አጭር የስልክ የፁሁፍ መልዕክት በመላክ እንዲገበያዩ መንገድ ፈጥሮላቸዋል። ደንበኞቹ ወንዶች ብቻ አይደሉም። « መልዕክቱን አንብቤ የሚፈልጉትን አውቃለሁ ያኔ ዋጋው ስንት እንደሆነ መልሼ እፅፍላቸዋለሁ። ወደ መድሓኒት ቤቴ ሲመጡ የተቀመጠላቸውን እቃ ተጠቅልሎ ያገኛሉ።»

በሶማሊያ ብዙዎች ስለ ቤተሰብ ምጣኔ ደፍረው አይወያዩም፤ በተለይ አክራሪው ቡድን አሸባብ በሚገኝባቸው ቦታዎች በኮንዶም መጠቀም ቅጣቱ ከፍተኛ ነው። ብዙ ሴቶች ምንም እንኳን ቤተሰቡ በቂ ገንዘብ ባይኖረውም በያመቱ ልጅ ይወልዳሉ። ወጣቶችን ግንዛቤ ለማስጨበጥ በአንድ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩት ሙክታር አብዲ የዚህን ምክንያት ያውቃሉ።« የሶማሊያ ሰዎች ወግ አጥባቂ ናቸው። ይህም ባህል እና ሐይማኖት ላይ የተመረኮዘ ነው። ለዚህ ነው አሳፋሪ ነው ብለው የሚያምኑት። በሌላ በኩል ደግሞ ጡረታ ስለሌላቸው ብዙ ልጆች ቢወልዱ ዕድሜአችው እየገፋ ሲሄድ ልጆቹ ይጦሩናል ብለው ያስባሉ። »

አብዱላሂ አዴን 34 ዓመቱ ነው። 7 ልጆች አሉት። ከዚህ ቀደም መምህር የነበረው የልጆች አባት አሁን ቋሚ ስራ የለውም። ምግብ የሚመገቡት በቀን አንድ ጊዜ ነው ። ነገር ግን በቅርቡ ባልተቤቱ አንድ ልጅ ትወልዳለች።« የቤቱ አባወራ ነኝ። ባለቤቴ የወሊድ መከላከያ እንድትጠቀም አልፈቅድላትም። ያገባኋት ልጅ እንድትወልድ ነው። እሷ በዚህ ጉዳይ ላይ አብሮ የመወሰን መብት የላትም። ይህ የኔ የራሴ ውሳኔ ብቻ ነው።»

Verhütung Geburtenkontrolle Pille Kondom Schwangerschaft Kontrazeption
የወሊድ መከላከያምስል picture-alliance/dpa

የአብዱላሂን አስተሳሰብ በርካታ የሶማሊያ ወንዶች ይጋራሉ። ይህን ደግሞ የመድሓኒት ቤት ባለሙያው ጃማ ኢሳክ ያውቃል። «ተስፋ የማደርገው ሰዎች በቅርቡ አስተሳሰባቸውን ይቀይራሉ ብዬ ነው ይላል።» ያኔ መሳቢያ ውስጥ የደበቃቸውን ኮንዶም እና የወሊድ መከላከያ መድሓኒቶች በይፉ መሸጥ ይጀምር ይሆናል። « የጎረቤት ሀገራትን ስመለከት የወሊድ መከላከያ መግዛት እና መጠቀም የተለመደ ነው። እኛ ጋር ግን ገና ብዙ መግለጫ እና ትምህርት መሰጠት ይኖርበታል። ምናልባት በቴሌቪዥን እና ራዲዮ። የቤተሰብ ምጣኔ በሕግ ያለተከለከለ መሆኑን ሰዎች ሊያውቁ ይገባል። »

ከሶማሊያ ጃማ ወደ ጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያ እናምራ። ያልተፈለገ እርግዝናን እና ተላላፊ በሽታዎችን መከላከያ ኮንዶሞች በየመድሓኒት ቤቶች መደርደሪያ ይገኛሉ። በሶማልያ አንፃር ኢትዮጵያን የተመለከትን እንደሆን በዚህ ረገድ ትልቅ ለውጥ እንዳለ ነው ያነጋገርናቸው የመድሐኒት ቤቶች ሰራተኞች ያስረዱን። ሁለት መድሓኒት ቤቶችን አነጋግረናል። ፋርማሲስት አቶ አበባው ከአዲስ አበባ እና አቶ አብዱልፈታህ መሀመድ ከሀረር ናቸው። አስተያየታቸውን ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ