1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮፐንሃገን ተስፋ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 22 2002

በመጪዉ ሳምንት በኮፐን ሃገን ዴንማርክ የሚጀመረዉ የተመድ የአየር ጠባይ ጉባኤ ትርጉም ያለዉ ዉጤት ላይ እንዲደርስ የሚደገዉ ጥረትና ግፊት ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/Kn5I
የአየር ጠባይ ለዉጥ የሚያስከትላቸዉምስል Dominik Joswig

ከምንም በላይ ዓለም ብዙ የሚጠብቅባቸዉ እና ስልጣን ላይ ከወጡ ድፍን አመት ያልሞላቸዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ጉባኤ በተከፈተ በሁለተኛዉ ቀን ከመሰል አቻዎቸዉ ጋ ስብሰባዉን እንደሚካፈሉ መሰማቱ ጠዉልጎ ለከረመዉ የኪዮቶን ዉል ተኪ ስምምነት ተስፋ ነፍስ ዘርቶበታል። ለብዙሃኑ የአገራቸዉ ዜጋ የጤና መድህን ዋስትና በማስገኘቱ ጥረት ደፋ ቀና ሲሉ የአየር ጠባይ ለዉጥና የዓለም የሙቀት መጠን መጨመር አደጋን ችላ ያሉ መስለዉ የከረሙት ኦባማ ምንም እንኳን አገራቸዉ ግልፅ መስመር ባለመያዝ ብትወቀስም የአየር ጠባይ ለዉጥን ለመግታት የሚረዳዉን የበካይ ጋዞችን ቅነሳ ስምምነት መስመር ለማስያዝ እንደሚሞክሩ ተገምቷል። የጉባኤዉ አስተናጋጅ አገር ዴንማርክ እስከ

አዉሮጳዉያኑ 2050ዓ,ም በኢንዱስትሪ ያደጉት አገራት ወደከባቢ አየር የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን በግማሽ እንዲቀንሱ ጥያቄ አቅርባለች። ዴንማርክ እንደምትለዉ የበለፀጉት አገራት 80በመቶዉን ለመቀነስ መስማማት ይኖርባቸዋል። የዴንማርክን ጥሪ ወደከባቢ አየር በሚለቁት አደገኛ ጋዞች መጠን የአራተኛ ደረጃን የያዘችዉ ህንድ ተቃዉማለች። የህንድ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ጃይራም ራሜሽ የዴንማርክ አካሄድ ጉባኤዉ መፍትሄ አልባ እንዲሆን ያደርጋል ሲሉም ተችተዋል። ቻይናና ህንድ ቀደም ሲል በኢንዱስትሪዉ አብዮት በነበረዉ የብልፅግና ፉክክር ከቅሪተ አፅም የሚገኙ የኃይል ምንጮችን በመጠቀም ከባቢ አየርን ሲበክሉ የከረሙትና ዛሬ ከእድገት ቁንጮ የተፈናጠጡት አገራት እስከአዉሮጳዉያኑ 2020ዓ,ም ድረስ የታለመዉን የበካይ ጋዞጭ ልቀት ቅነሳ በግንባር ቀደምትነት ሲተገብሩ ካላየን በ2050ዓ,ም የካርቦን ዳይኦክሳይድን ልቀት በግማሽ መቀነስ የሚለዉን ሃሳብ አንቀበልም የሚል ጠንክራ አቋም እያራመዱ ነዉ። ለምጣኔ ሃብት እድገት አገራት በሚያደርጉት ዉድድር ከየግዙፍ ኢንዱስትሪያቸዉ የሚወጣዉ በካይ ጋዝ መጠኑ ጨምሮ የከረመ ቢሆንም በቅርቡ በዓለማችን በታየዉ የፋይናንስ ክስረት በያዝነዉ የአዉሮጳዉያኑ ዓመት ሶስት በመቶ ቀንሶ መገኘቱ ተመዝግቧል። እንግዲህ በተመድ የታለመዉ የአየር ጠባይ ለዉጥ ላይ ትኩረቱን ያደረገዉ የየመንግስታቱ ድርድርና ዉይይት ይህ ነዉ የሚባል የተጨበጠ ነገር ጠብ ሳይለዉ ዓመቱን ሙሉ ሽር ጉድ ሲባልለት የከረመዉ ኮፐንሃገኑ ጉባኤ ሊጀመር ስድስት ቀናት ብቻ ቀርተዉታል። ይህ ጉባኤ ድሃና የበለፀጉት አገራት ክስተቱ በዓለማችን የሚያስከትለዉንና እያደረሰ ያለዉን ጥፋት ተመልክተዉ ማን በምን ያህል በካይ ጋዞችን ይቀንስ፤ በየትኛዉ የጊዜ ገደብ፤ እንዲሁም ለዉጡ ካስከተለዉ ተያያዥ ችግር ጋስ አቅም የሌላቸዉ አገራት ተላምደዉ ለመኖር ሊደረግላቸዉ የሚገባዉ የገንዘብ ድጎማም ሆነ የቴክኒዎሎጂ ሽግግር ምን መስመር ይያዝ የሚለዉን ተስማምተዉ እንዲወስኑ ይጠበቃል።

Flash-Galerie Greenpeace erinnert in Hongkong an Klimawandel
የአየር ጠባይ ለዉጥ ይገታ!ምስል picture-alliance / dpa

ቻይናና ህንድ የሚመሩት በማደግ ላይ ያሉ አገራት ስብስብ ወደኮፐንሃገኑ ጉባኤ ለድርድር የሚያቀርቡት መሰረታዊ ጉዳይ እንደሚኖር እየተነገረ ነዉ። ለምሳሌ የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂባኦ ለአዉሮጳ ኅብረት እንደገለፁት አገሪቱ በከባቢ አየር ላይ የምታደርሰዉን ብክለት ለመቀነስ ዝግጁ ናት። ከምንም በላይ ደግሞ ከቅሪተ ዓፅም የሚገኙ የኃይል ምንጮችን በመጠቀም የምትለቀዉን የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ማለት ነዉ። የወቅቱ የአዉሮጳ ኅብረት ፕሬዝደንት የስዊድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍሬዴሪክ ራይንፌልድ ግን ከዚያዉ ከቻይና እንደተናገሩት ዓለም የተባለዉን የብክለት መጠን ለመቀነስ ከልቡ ዝግጁ አይደለም። ከዚህ የበለጠ ሊደረግ ይገባል ነዉ ያሉት። የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ላርስ ሎከ ራስሙሰን በበኩላቸዉ አገራቸዉ ከአምስት እስከ ስምንት ገፅ የሚደርስ፤ የየአገራቱን ግዴታ በግልፅ የሚያሳይ ፖለቲካዊ አሳሪነት ያለዉ ስምምነት ከኮፐንሃገን የተመድ የአየር ጠባይ ለዉጥ ጉባኤ እንዲወጣ ትፈልጋለች ብለዋል። ከበለፀጉት አገራት ብሪታንያ ፈረንሳይ የኮፐንሃገን የገንዘብ ድጋፍ ለተሰኘዉ መድረክ በየዓመቱ 10ቢሊዮን ዶላር ለማዋጣት ዝግጁነታቸዉን አሳይተዋል። ሃሳባቸዉ በአዳጊዎቹ አገራት ጊዜያዊ ድጎማ በሚል ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም የበለጠ እንደሚጠበቅባቸዉ ተነግሯቸዋል። የዓለም የአየር ጠባይ ዉልን ትርጉም ያለዉ ለማድረግ በየዓመቱ እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ እየተጠቆመ ነዉ። ያ በበለፀጉት አገራት ተቀባይነት ያግኝ አያግኝ ግን ገና አልታወቀም። እንደዉም የበለፀጉት አገራት ለአዳጊ አገራት ከሚሰጡት የልማት ርዳታ ጋ ይህ የአየር ጠባይ ለዉጥ የሚያስከትለዉን ችግር ተላምዶ ለመኖርም ሆነ ለቴክኒዎሎጂ ሽግግር ሊዉል ይገባል የሚባለዉ የገንዘብ ድጋፍ ሊምታታ እንደማይገባ ከወዲሁ ማስጠንቀቂያዉ እየተነገረ ነዉ። አገራቱ ለልማት የሚደረግላቸዉ የገንዘብ ድጋፍ ለልማት እንጂ በበካይ ጋዞች ምክንያት የተከሰተዉ የአየር ጠባይ ለዉጥ ካስከተለባቸዉ የተፈጥሮ መዛባት ኑሯቸዉን ለመታደግ ሊያዉሉት አይገባምና።

ሸዋዬ ለገሠ/ነጋሽ መሐመድ