1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወሊድ እረፍት፤ የእናቶች መብት

ማክሰኞ፣ የካቲት 29 2008

በመላዉ ዓለም ሥራ ላይ ከተሠማሩ ሴቶች 830ሚሊየኑ ተገቢዉ የእናቶች የወሊድ ጊዜ እረፍት አያገኙም። ከእነዚህ መካከል 80 በመቶዉ የሚገኙት አፍሪቃ እና እስያ ዉስጥ ነዉ። የዓለም የሠራተኞች ድርጅት ማለትም ILO 183ኛዉ አንቀፅ በሥራ ላይ የተሠማራች የትኛዋም ሴት በተለይ በወሊድ ጊዜ በቂ ክብካሄ እንድታገኝ የሚያሳስብ ድንጋጌን ይዟል።

https://p.dw.com/p/1I9RQ
Bildergalerie Muttertag International Kongo Save the Children Report
ምስል JUNIOR D.KANNAH/AFP/Getty Images

የወሊድ እረፍት፤ የእናቶች መብት

ይህም ነፍሰ ጡር እናቶችን ከሚገጥማቸዉ መገለልም ሆነ ከሥራ የመባረር ጥቃት መከላከልን ጨምሮ፤ በቂ የወሊድ ፈቃድ፣ ልጇን የመንከባከቢያ እና ማጥቢያ እረፍት፣ ከዚያም ከወሊድ ፈቃድ እና እረፍት ሲመለሱ የሥራ ቦታቸዉን ጠብቆ ወደቦታቸዉ መመለስንም ሁሉ ያካትታል። ይህን ድንጋጌ እስካሁን አራት የአፍሪቃ ሃገራት ማለትም ማሊ፣ ሞሮኮ፣ ቤኒን እና ቡርኪናፋሶ ተቀብለዉ ተግባራዊ እያደረጉ እንደሆነ ተመዝግቦላቸዋል። የዓለም የሠራተኞች ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህፃሩ ILO የ52 የአፍሪቃ ሃገራትን የሠራተኞች መብት መርምሮ በዉጤቱ ከእነዚህ ሃገራት ገሚሱ 14 ሳምንታትን ለእናቶች የወሊድ እረፍት እንደሚሰጡ አጣርቷል። 32 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ12 እስከ 13 ሳምንታት ብቻ እረፍት እንደሚሰጡ ደርሶበታል። በዚያም ላይ 10 በመቶ የሚሆኑ የወለዱ እናቶች ደሞዛቸዉን ላያገኙ ይችላሉ ወይም ከወሊድ እረፍት በኋላ ወደሥራቸዉ ሲመለሱ ቦታቸዉን ያጣሉ። ከወሊድ ጋር በተገናኘ ለእናቶች የሚደረገዉ ክብካቤ በኤኮኖሚ ባደጉት ሃገራት ጥሩ ነዉ ቢባልም የአፍሪቃ እና እስያ ሃገራት አሁንም ብዙ ይቀራቸዋል።

Sexualkundeunterricht
ምስል Fotolia/shootingankauf

የሠራተኞች መብት ጉዳይ ተንታኟ ላዉራ አዳቲ እንደሚሉት አሁን ሩዋንዳ እያዳበረች የመጣችዉን ዓይነት ማኅበራዊ ክብካቤ እና ድጋፍ በሌሎቹ ዘንድ አይታይም። ምንም እንኳን ይላሉ አዳቲ ሴቶች ጠንካራ ሠራተኞች መሆናቸዉ ቢታወቅም በእርግዝናቸዉ ወራት ሊያገኙት የሚገባዉ ተገቢ ክብካቤ በአሠሪዎቻቸዉም ሆነ በመንግሥት ማኅበራዊ ተቋማት ያን ያህል ትኩረት አይሰጠዉም። በዚህ ምክንያትም አብዛኞቹ ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት ያሉ ሴቶች ተቀጥረዉ የሚሠሩት ይበልጥ በግል ዘርፎች ዉስጥ እና በቤት እመቤትነት ለመኖር ይገደዳሉ። ከአጎራባቾቿ በተሻለ ሩዋንዳ ሠራተኛ ሴቶች ተገቢዉን ክብካቤ እንዲያገኙ እየጣረች መሆኑ ተነግሮላታል። በቅርቡ የሩዋንዳ ምክር ቤት የወለዱ እናቶች እስከዛሬ ከነበረዉ በተለየ ለ3 ወራት ሙሉ ደመወዛቸዉ እየተከፈላቸዉ የወሊድ ፈቃዳቸዉ ላይ መቆየት እንዲችሉ ረቂቅ ሕግ አቅርቧል። የፕሬዝደንት ፖል ካጋሜን ፊርማ የሚጠብቅ ቢሆንም አዎንታዊ ርምጃ ተብሏል።

ወደኢትዮጵያ ስንመጣ ለረዥም ዓመታት ሠራተኛ እናቶች የሚያገኙት የወሊድ ፈቃድ 45 ቀናት ብቻ ነበር። ያ አሁን ታሪክ ሆኖ ሶስት ወራትን ማለትም ዘጠና የሥራ ቀናትን እረፍት ማግኘት ችለዋል። ማተርኒቲ ፋዉንዴሽን የተሰኘዉ የዴንማርክ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የምሥራቅ አፍሪቃ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሕይወት ዉብሸት የወሊድ ፈቃድና ክብካቤዉን ማሻሻልን ተመለከተ በሀገር አቀፍ ደረጃ አለ ስላሉት እንቅስቃሴ ገልጸዉልናል።

Geburtenrate Deutschland Geburt Baby Säugling Alterspyramide Mutter Kind Mutterschutz
ምስል picture-alliance/dpa

ወ/ሮ ሕይወት እንዳሉትም አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ከወሊድ እረፍት የተመለሱ እናቶች ልጆቻቸዉን ወደቤት ተመላልሰዉ ጡት ማጥባት ስለማይችሉ በሥራ ቦታቸዉ ለዚህ የሚሆን ስፍራ በማዘጋጀት ተገቢና ቀና ትብብር እያደረጉ መሆኑንም ለመረዳት ችለናል።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሠራተኛ እናቶች የሚሰጠዉ የወሊድ እረፍት በድጋሚ እንዲሻሻል ከሚቀርቡ ዉይይቶች ባሻገር ይህ እዉን እንዲሆን የበኩላቸዉ ጥረት የጀመሩም አሉ። በወሊድ ፈቃድ ከሥራ ገበታቸዉ የሚርቁት ሴቶች ተጨማሪ ቀናት ማግኘታቸዉ መልካም እንደሆነ ቢያምኑም አንዳንዶች ግን የሥራ ዋስትና ስጋት እንዳላቸዉ አይሸሽጉም። ለተወሰኑ ወራት አዲስ የወለደችዉን ሕፃን ስትንከባከብ፤ የግል ጤንነትና አቅሟም እስኪመለስ የምትታገል እናት ወደሥራዋ ስትመለስ መንፈሷ ከጨቅላዉ ጋር ወደኋላ መጎተቱ ግልፅ ነዉ። ይህን የእናቶችን ስጋት ራሷ እንዳለፈችበት የምትናገረዉ ጋዜጠኛ እና ጸሐፊ ሮዝ መስቲካ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ማለትም ፌስ ቡክ ሥራ ላይ የተሠማሩ ኢትዮጵያን እናቶች የወሊድ እረፍት ወደስድስት ወር ከፍ እንዲል ነዉ ዘመቻ ጀምራለች። እዚህ ጀርመን ሀገር ዘጠኝ ወር ልጅ ከአካሏ አዋህዳ የተሸከመችዉ እናት ብቻ ሳትሆን የወሊድ እረፍት የምታገኘዉ አባትም አዲስ የተወለደ ልጁን የሚንከባከብበትና እናቲቱን በሚችለዉ ሁሉ በቤቱ ሥራ የሚረዳበት የአባትነት የእረፍት ፈቃድ ይሰጠዋል። ሚስቶቹም ቢሆኑ እኔ አምጬ ወልጄ ለምን ለእሱ ተሰጠብኝ ቀኑ አይሉም፤ እንዲህ ባለዉ ጊዜ ከጎን ሆኖ ልጅ በመንከባከቡ ተግባር የሚራዳ ሰዉ ከሰማይ እንደወረደ ገጸበረከት ነዉና።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ