1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወቀሳ እና ሙገሳው መድረክ 

Eshete Bekele
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 15 2009

ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሳምንት ከተቃዋሚዎች፤የንግዱ እና ሲቪል ማሕበረሰብ ተወካዮች ጋር አዲስ አበባ ላይ መክሯል። በኮንሶ፤ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሱት ተቃውሞዎች ግን በጥልቀት ውይይት ሲደረግባቸው አልታየም። 

https://p.dw.com/p/2RZ2o
Infografik Karte Proteste und Ausschreitungen in Äthiopien 2016

ትኩረት በአፍሪቃ

ምክር እና ልመና ፤ትዝብት እና ንትርክ ወቀሳ እና ሙገሳ በአንድ ዕለት በአንድ መድረክ። «የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ከየት ወዴት፤ ፈተናዎቹና መልካም እድሎቹ» በሚል ርዕስ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በተካሔደው ውይይት የተሰሙት ድምፆች እንደ ተናጋሪው ማንነት እና የፖለቲካ አቋም የተለያዩ ነበሩ። መነሻቸውን የተለያዩ ዘመናት ያደረጉ አራት የመነሻ ፅሁፎች የቀረቡበት መድረክ ዋንኛ ዓላማ «የሃሳብ ትግል፤ውይይትና ክርክር» ማካሔድ መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጠው ነበር። በመድረኩ የቀረቡት ሃሳቦች፤ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ግን አንድ ማዕከላዊ የማጠንጠኛ ጉዳይ አጥተው እዚህም እዚያም የሚረግጡ ሆነው ተስተውለዋል። ውይይቱ በማሕበራዊ ድረ-ገፆች ከተሰራጨ በኋላ የተከታተለው ግርማ ጉተማ በኦስሎ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ላይ የሚገኝ የፖለቲካ አቀንቃኝ ነው። ውይይቱ በይዘቱ ብቻ ሳይሆን በድምፀቱም ከወትሮው የተለየ ነው የሚለው ግርማ ጊዜ ለመግዛት የታቀደ ይመስላል ሲል ይናገራል። 

በውይይቱ የተሳተፉት ዶ/ር መረራ ጉዲና ገዢው ፓርቲ ከመታደስ ይልቅ እንደገና ቢወለድ ይቀለዋል ሲሉ ተደምጠዋል። ገዢውን ፓርቲ ወክለው በጉባዔው ከተገኙት መካከል የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ «ምሰሶው ከፈረሰ እንደገና መሰራት የለም።» ሲሉ መልሰዋል። የኢህአዴግ ሹማምንት እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፤የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች የታደሙበት እና ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያለው ፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ባዘጋጀው መድረክ ዶር/መረራ ጉዲና አንዱ ነበሩ። የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የዕለቱ ውይይት እና ማምሻውን የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ መመሪያ ዕርስ በርስ ተጋጭተውባቸዋል።
አንድ የውይይቱ ተሳታፊ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የነፃ ኃሳብ ማንሸራሸሪያ የሆነውን የፌስቡክ ማሕበራዊ ድረ-ገፅ የሚዘጋ ከሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ የኋልዮሽ ጉዞ አንድ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል። ተሳታፊው የዴሞክራሲ ሥርዓቱ ወደ ኋላ አልሔደም ብለው የሚከራከሩ ወገኖች ነባራዊውን ሁኔታ በቅጡ ስለመገንዘባቸው ጠይቀዋል። የመንግስት እና ፓርቲ መቀላቀል፤ኃሳብን የመግለፅ ነፃነት እጦትን የመሳሰሉ ችግሮችም ተነስተዋል። ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ በበኩላቸው አገሪቱን የሚያስማሙ የጋራ እሴቶች አለመኖራቸውን፤በመንግስት ዘንድ የተጠያቂነት እጦት፤ የሲቪል ማሕበረሰብ እና መገናኛ ብዙኃን መቀጨጭን አንስተዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ልጅ ሰመሐል መለስ በበኩሏ የገዢውን ፓርቲ የውስጥ ጉዳይ አንስታለች። ሰመሐል ስም ጠቅሳ ከፓርቲው የተሰናበቱ አመራሮች ለምን ተመልሰው ወደ ፖሊት ቢሮ ገቡ? ስትል ጠይቃለች። ግርማ የወጣቷ አስተያየት በገዢው ፓርቲ ውስጥ ስላለው ውጥረት የሚናገረው አንዳች ነገር አለ ባይ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ካሳሁን ብርሐኑ ወደ ኋላ አመታትን ተንደርድረው በ1966 የኢትዮጵያ አብዮት አገሪቱ አመለጧት ያሏቸውን እድሎች ዘርዝረዋል። የፖለቲካ መምህሩ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሙከራ የተጀመረው በዚያው የአብዮት እና አብዮተኞች ዘመን እንደሆነ አስታውሰዋል። የ1983 ዓ.ም. የመንግስት እና የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ የታዩ በጎ ለውጦች ያሏቸውን ጠቃቅሰዋል። ዶ/ር ብርሐኑ «መሪ ድርጅት» ያሉት ኢህአዴግ እና ፌዴራላዊው መንግስት ያሉባቸው ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተፃራሪ የሆኑ አሉታዊ ክስተቶች በመጠንና በአይነት እያደጉ መሔድ ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 

Proteste in Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri

የመልካም አስተዳደር እና የሕግ የበላይነት ግድፈቶች፤ የተጠያቂነት እና ግልፅነት መዳከም፤ በአገሪቱ ታሪክ «ታይቶ በማይታወቅ አይነት እና መጠን» ዘርፈ ብዙ ሙስና መንሰራፋት፤በአገር እና በሕዝብ ጥቅም ኪሳራ በግል ጥቅም ላይ  የተዋቀረ አሰራር መሥፋፋት የሥርዓቱ ችግሮች መሆናቸውን ጠቃቅሰዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የውሳኔ ሰጪዎች በሥልታዊ የፖለቲካ ሙስና ለግለሰቦች ጥቅም ማደራቸውንም ጠቆም አድርገዋል። የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሶማሊያ ከበታተኗ በፊት እነዚህ ችግሮች ተከስተው እንደነበር አስታውሰው ተመሳሳይ ኩነት በኢትዮጵያ «ይኸ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ» ሲሉ ተደምጠዋል። 

የግል ዘርፉን ወክለው የቀረቡት ኢንጂኔር ፀደቀ ይሁኔ «መቻቻል እና መነጋገር ባለመኖሩ ምክንያት በውስጣችን ያለውን የአስተሳሰብ ልዩነት በተናጠል ልንጠቀምበት ሞክረን አልተሳካልንም።» ሲሉ ተናግረዋል። «ሰብዓዊ መብት ተንቋል» ያሉት ኢንጂኔር ፀደቀ «ማዕከላዊ መንግስት በእጁ የያዘውን የንግድ እና የገንዘብ የማቀባበል ሥራ መስራት የለበትም።» ሲሉም ተደምጠዋል። ግርማ ጉተማ የመንግስት ሹማምንቱ በመድረኩ የቀረቡ ኃሳቦችን ለማድመጥ ፈቃደኛ ከሆኑ ጠቃሚ ጉዳዮች ተነስተዋል ሲል ይናገራል። 
የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የወከሉት አቶ ልደቱ አያሌው የመንግስት መገናኛ ብዙሃንን በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ተደምጠዋል። ፖለቲከኛው ነባራዊው የኢትዮጵያ ምስቅልቅል በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የተከሰቱ ኩነቶች ድምር ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል። ገዢው ፓርቲ የምክር ቤት ምርጫዎችን መቶ በመቶ ሲያሸንፍ እንኳ ከስህተቱ አለመማሩን ወቅሰዋል። «የአስተሳሰብ ብዝኃነት ቦታ አጣ፤ሰላማዊ እና ህጋዊ ትግል የሚያደርጉ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከፌስቡክ እና ከአካባቢ የጎበዝ አለቆች ባነሰ መጠን እርባና አጡ፤ኮሰሱ።» ያሉት አቶ ልደቱ አክራሪ ያሏቸው የፖለቲካ ኃይሎች የለማ መሬት ማግኘታቸውን ገልጠዋል።  «ሕብረተሰቡ ድምፁን የሚያሰሙለት የሚወክሉት በተወካዮች ምክር ቤት በክልል ምክር ቤት የነበሩ ሰዎች ሲጠፉ የሚተነፍስበት ቦታ አጣ፤ ተስፋ ቆረጠ፤ወደ ነውጥ ወደ አመፅ ገባ።» ያሉት አቶ ልደቱ በምክንያታዊነት እጦት ምክንያት ከ25 ዓመት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በኋላ አገሪቱ ወደ መንግስት አልባነት እና የርስ በርስ ጦርነት ልትገባ ከምትችልበት አደጋ ውስጥ ወድቃለች ብለዋል። 

Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu
ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

አቶ በረከት ስምዖን የአገሪቱ ኤኖሚ እና ዴሞክራሲ አድጓል፤ምርጫዎቻችንም ተዓማኒ ነበሩ የሚል መከራከሪያ ይዘው ብቅ ብለዋል። አቶ በረከት ፓርቲያቸው እና መንግስታቸው የገጠሟቸው ችግሮች የአገሪቱ እድገት እና አመራር የፈጠሯቸው ናቸው ብለዋል። «የአመራር ብልሽት አጋጥሞናል» ያሉት አቶ በረከት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአርሶ አደሩ ዘንድ ቦታ የላቸውም ሲሉ ተናግረዋል።  በውይይቱ ላይ አሁን ኢትዮጵያ የገጠማትን ፖለቲካዊ ቀውስ በአለፍ አገደም ከመጠቃቀስ ባለፈ የኮንሶ፤ኦሮሚያም ይሁን በአማራ ክልሎች የታዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በጥልቀት አልተፈተሹም። የተቃውሞዎቹ መነሻ ያስከተለው የዜጎች ሞት እና የንብረት ኪሳራ አልተፈተሸም። 

ውይይቱ ውጥረት ከማስተንፈስ የዘለለ ሚና የለውም ያሉት ኢንጂኔር ይልቃል ጌትነት ገዢው ፓርቲ እና አቶ በረከት ከነበራቸው አቋም ለውጥ አላሳዩም ሲሉ ወቅሰዋል። የቀድሞው የሰመያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት «አሁን ባለው ሁኔታ ችግሮች የሚፈቱበት እና ችግሮች የሚፈለፈሉበት ፍጥነት በጣም የተራራቀ» መሆኑን ገልጠው ለመፍትሔው የሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ያሻል ብለዋል። 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ