1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወቅት ፍርርቅና ወባ

ማክሰኞ፣ መስከረም 28 2006

ወባ ዛሬም ገዳይ በሽታ ነዉ በተለይ በአፍሪቃ። በበሽታዉ በግምባር ቀደምትነት የሚጠቁት ህጻናትና ነፍሰጡር እናቶች መሆናቸዉን የህክምና ባለሙያዎች ያመለክታሉ። በወባ በሽታ በዓለማችን በየዓመቱ ከሚያልቀዉ ህዝብ ቁጥር 80 በመቶዉ የሚገኘዉ አፍሪቃ ነዉ።

https://p.dw.com/p/19wNR
ምስል AP

ኢትዮጵያ ዉስጥ የዝናቡ ወቅት በመገባደድ ላይ ይገኛል። ከክረምት ወደበጋ የመሸጋገሪያዉ ጊዜ ደግሞ ርጥበት የሚበዛበት በመሆኑ ለትንኝ መራቢያ ምቹ ጊዜ እንዲሆን ተፈጥሮ ራሷ ያመቻቸችዉ ይመስላል። በዚህ ወቅት ነዉ ወባ በሚያሰጋቸዉ አካባቢዎች የወባ ትንኝ ርጥበት ባገኘችበት ሁሉ የምትፈለፈለዉ። በዓለማችን በ99 ሀገራት የወባ በሽታ ተስፋፍቶ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። በየዓመቱም ወባ የ660,000 ሰዎችን ህይወት ትቀጥፋለች። 219 ሚሊዮን ሰዎችም በወባ ይያዛሉ። ግሎባል ፈንድ ከዛሬ 13ዓመት ወዲህ በሽታዉ አሳሳቢ የሆነባቸዉ በርካታ ሀገራት ወባን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረዉ መቀጠላቸዉን ይገልጻል። በዚህ ጥረትም 32 ሀገራት ወባን ለማጥፋት መቃረባቸዉን 67ቱ ደግሞ በሽታዉን ወደመቆጣጠሩ ተቃርበዋል።

Moskito Malaria Insekt stechen
ምስል Fotolia/Alexander Zhiltsov

ኢትዮጵያ ዉስጥም በአንዳንድ ከዚህ በፊት ወባ ከፍተኛ ጉዳት ታደርስባቸዉ በነበሩ አካባቢዎች በሽታዉን መቆጣጠር የተቻለበት ሁኔታ እንዳለ ታይቷል። በምሳሌነትም የድሬደዋ መስተዳድር ይጠቀሳል። ወባ በድሬደዋ መስተዳድር ታደርስ የነበረዉን ጉዳት ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ማጥፋት መቻሉ የተዘገበበትን ጊዜ በማስታወስ ያነጋገርኳቸዉ የመስተዳድሩ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ኃይለጊዮርጊስ ከድሬደዋ የአየር ንብረት አኳያ ወባን ከአካባቢዉ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ይቻላል ብሎ ማሰብ የሚያስቸግር ቢሆንም ጉዳት እንዳታደር ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረቱ እንደቀጠለ ይገልጻሉ።

የወባ በሽታን ለመከላከል ብሎም የምታደርሰዉን የሞት አደጋ ለማስቀረት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጥረትና ምርምሩ እንደቀጠለ ነዉ። ከሳምንቱ መጨረሻ አንስቶ በደርበን ደቡብ አፍሪቃ በመካሄድ ላይ በሚገኘዉ ጉባዉ አዲስ የወባ መከላከያ ክትባት ግኝት ይፋ ይሆናል ተብሎ እየተጠበቀ ነዉ። የብሪታኒያዉ ግላስኮስሚዝክላይን በእንግሊዝኛዉ ምህጻር የተባለዉ የመድሃኒት ፋብሪካ ለ18 ወራት ባካሄደዉ ክትትልና የመድሃኒት ሙከራ ክትባቱ ህጻናትን በወባ በሽታ የመያዝ እድል በግማሽ መቀነሱ ተገልጿል።

Schweiz Weltwirtschaftsforum in Davos Bill Gates
ቢል ጌትስምስል dapd

የመድሃኒት ፋብሪካዉ ለሶስት አስርት ዓመታት ያህል ምርምሩን ሳያካሂድ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን የክትባቱ ሙከራና ዉጤት ተጣርቶም በሚቀጥለዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2014 ለገበያ የመቅረብ ተስፋ እንዳለዉ ተሰምቷል። ክትባቱ እዉቅና አግኝቶ ለሽያጭ ለመቅረብ እንዲበቃም የአዉሮጳ የመድሃኒት ተቋም GSK ያቀረበለትን ማመልከቻ በመንተራስ ዉጤቱን መገምገም ይኖርበታል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ ግን ከ2015ዓ,ም በፊት ክትባቱ ገበያ ላይ ይወጣል ብሎ መገመት ይከብዳል። GSK የክትባት ምርምሩን የሚያካሂደዉ በወባ በሽታ የሚቀጠፉ ህጻናትንና አዋቂዎችን ህይወት ለመታደግ አሜሪካዊዉ ቱጃር ቢል ጌትስ ከነባለቤታቸዉ ባቋቋሙት ሚልንዳ ጌትስ ተቋም በተገኘ ገንዘብ ነዉ። እናም ክትባቱ ፍቱን ሆኖ ከተገኘም ገበያ ላይ የሚዉለዉ በተመጣጣኝ ዋጋ ይሆናል ብሎ መገመት ይቻላል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ