1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወንዞች ብክለት በአዲስ አበባ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 10 2006

እንደኦክስጅን ሁሉ ለፍጥረታት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ዉሃ መሆኑ ይታወቃል። የፍጥረታት መሠረት የሆነዉ ዉሃ ለምግብ የሚሆኑ ተክሎችን በማብቀል ነፍስ ለማቆየት ሲፈለግ እሱ ራሱ በልዩ ልዩ ነገሮች ተበክሎ የበሽታ መንስኤ ሲሆን አሳሳቢነቱ ያኔ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1CKKz
Symbolbild Plastikmüll Strand Meer
ምስል China Photos/Getty Images

በአዲስ አበባ ከተማና አካባቢዋ የሚፈሱ ወንዞች አብዛኞቹ ለብክለት የመዳረጋቸዉ ጉዳይ ሲነገር ከርሟል። የብክለታቸዉን ሁኔታ መንስኤና በዉስጣቸዉ ያለዉን ለማጥናትና ለሚመለከታቸዉ በማሳወቅ ትኩረት እንዲደረግ ጥናቶች ጥቂት በማይባሉ ምሁራን ተካሂደዋል።

በአዲስ አበባ ከተማና አካባቢዋ ከሚፈሱት ወንዞች ቀበና፣ ቡልቡላ፣ ትንሹና ትልቁ አቃቂ፣ እንዲሁም የቄራ ወንዝን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። የወንዞቹ መኖር ከከተማና አካባቢ ዉበት በተጨማሪ በአንዳንድ አካባቢዎች ዉሃዉ እየተጠለፈ ለአትክልትና ፍራፍሬ ማብቀያ መዋላቸዉ ይታወቃል። አንዳቸዉንም ግን ከብክለት የጸዱ አይደሉም። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በተለይ ትንሹና ትልቁ የአቃቂ ወንዞች ከደረቅ ቆሻሻ በተጨማሪ የፋብሪካ ተረፈ ምርትና ፍሳሽ የሚገባባቸዉ በመሆኑ የብክለታቸዉ ደረጃ ከባድ ብረት ንጥረነገሮችን ሁሉ የያዘ ነዉ። በዚህ ምክንያትም በዉሃዉ የሚበቅለዉ ማንኛዉም ለምግብነት የሚዉል ተክል ወዲያዉም ሆነ ዉሎ አድሮ ለጤና ጉዳት የመዳረግን ጣጣ የያዘ ነዉ።

Afar-Region in Äthiopien
ምስል picture-alliance / africamediaonline

ከከተማዉ ልማትና እድገት ጋ በተገናኘ የሚቋቋሙ ፋብሪካዎች በበኩላቸዉ የሚሰጡት አገልግሎት ባይካድም እንቅስቃሴያቸዉ የአካባቢዉን ተፈጥሮ ለጉዳት እንዳያጋልጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸዉ አያነጋግርም። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ አንዳንድ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች የብክለት ችግሩ መኖሩ የሚታበል እንዳልሆነ እና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንም ሆነ ልዩ ልዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቆሻሻ አወጋገድ ጥንቃቄ እንዲወሰድ የየበኩላቸዉን የግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶች እንደሚያከናዉኑ ገልጸዋል። የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ብክለት ጥናትና ምርምር ባለሙያ አቶ አበራ ብርሃኑ እንደሚሉት ወንዞቹ የሚገኙበትን የብክለት ደረጃ ለማወቅ በመሥሪያ ቤታቸዉ በኩል በየጊዜዉ የግምገማ ጥናቶች ይካሄዳል። ይህም የተቀናጀ ርምጃ ለመዉሰድ እንደሚረዳ ያመለክታሉ፤ ከዚህ አስቀድሞ ደግሞ የሚደረግ ሌላ ነገር እንዳለ ነዉ አቶ አበራ ያመለከቱት፤ ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ