1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወጣቶች እና ጎልማሶች ስጋት

ዓርብ፣ ሰኔ 9 2009

ጀርመን ውስጥ ሰሞኑን የተደረገ አንድ መጠይቅ እንደሚያመላክተው የጀርመን ወጣቶች እና ጎልማሶችን ከመቼውም በላይ ጦርነት እና የሽብር ጥቃት ያሰጋቸዋል። የወጣቶቹ እና ጎልማሶቹ ስጋት የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ርዕስ ነው።

https://p.dw.com/p/2eoNw
Weltkarte des Kartographen Rolf Böhm
ምስል R. Böhm/Müller und Richert Gotha

የወጣቶች እና ጎልማሶች ስጋት

ሰኞ ዕለት አንድ ኒዎን የተሰኘ የጀርመን መፅሔት ይፋ ያደረገው መጠይቅ እንደሚያመላክተው ጀርመን ውስጥ የወጣቶች እና ጎልማሶች ስሜት ተነክቷል። ይህም በአጠቃላይ በዓለማችን ላይ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ እና ከሽብር ጥቃት ስለሚያሳስባቸው ነው። «ጀነሬሽን 2017» የተባለው መጠይቅ ከ18 እስከ 35 እድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን አሳትፏል።  ከነዚህም 69 በመቶው የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚያራምዱት ፖለቲካ ስጋት ጥሎባቸዋል። 45 በመቶው ደግሞ የሽብር ጥቃት ዒላማ እንዳይሆኑ ይሰጋሉ።  55 በመቶው ጭራሽ በጀርመን ዳግሞ ጦርነት እንዳይነሳ ይፈራሉ። እኛም እድሜያቸው በመጠይቁ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እና በጀርመን ፣ በብሪታንያ እና በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሦስት ኢትዮጵያንን የመጠይቁን ይዘት ይጋሩ እንደሆን ጠይቀናል።

Deutschland Berlin Nach Anschlag auf Weihnachtsmarkt
በርሊን የገና ገበያ ውስጥ በሽብር ጥቃት ለተገደሉ ሰዎች የተደረገው መታሠቢያምስል picture-alliance/dpa/R. Jensen

የጀርመን ሙኒክ ከተማ ባለፈው ዓመት ብቻ ሁለት ጥቃቶችን አስተናግዳለች። አንዱ የ18 ዓመት ጀርመን-ኢራናዊ ወጣት በዘፈቀደ እየተኮሰ 9 ሰዎችን የገደለበት ጥቃት ሲሆን ሌላው አንድ የጀርመን ዜግነት ያለው የ27 ዓመት ወጣት ባቡር ውስጥ በስለት አንድ ሰው ገድሎ ሦስት ያቆሰለበት ነው። ማክሰኞ ዕለት ደግሞ አንድ ጎልማሳ ከፖሊስ ነጥቆ በተኮሰው ጥይት አንዲት ፖሊስን ክፉኛ አቁስሏል። በዚሁ ከተማ ስጋት ላይ የወደቀችው ሐይማኖት መሰለ ትኖራለች። እሷም ለረዥም ዓመታት በምትኖርባት ጀርመን እንዲህ ዓይነት ስጋት ሲገጥማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንስቶ ነው።

የጀርመንኑ የጥናት ተቋም ይፋ ያደረገው መጠይቅ እንደሚያሳየው ባለፉት ሁለት ዓመታት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች የተጠለሉባት ጀርመን የምታራምደው የስደተኞች ፖለቲካ እዚህ የሚኖሩ ወጣቶች አመለካከትን ከፋፍሏል። 54 በመቶው ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ያለው የጥላቻ አመለካከት ሲያሳስባቸው፤ ግማሽ ያህሉ ደግሞ ጨርሶ ጀርመን የመሰደጃ ሀገር መሆኗ ያሳስባቸዋል። በሽብር ጥቃት ስጋት አንዳንዶች እንደ እግር ኳስ ስቴዲዮም እና የሙዚቃ ድግስ የመሳሰሉ ሰው በብዛት የሚሰባሰብባቸው ቦታዎች ላይ መገኘትን ጨርሶ ሲተው ሌሎች  ደግመው ደጋግመው አስበውበት የሚሄዱበት ቦታዎች ሆነዋል።

London - Polizei auf London Bridge
ሰባት ሰዎች በሽብር ጥቃት ሰለባ የሆኑባት ለንደንምስል Reuters/P. Nicholls

የሽብር ጥቃት ሰለባ ከሚሆኑት ሰዎች ባሻገር ሁኔታው በሌላው ላይም ስነ ልቦናዊ ጫና ፈጥሯል። ቅዳሜ ዕለት አንድ ወደ ለንደን በበረራ ላይ የነበረ አይኖፕላን አቅራቢያችን የሚገኘው የኮሎኝ ቦን የአይሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ተገዷል። ይህም ሦስት አይሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ስለ ሽብር ጥቃት ሲያወሩ ነበር በሚል ስጋት ነው። አይሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 151 ሰዎች በአደጋ ጊዜ መውጪያ አይሮፕላኑን ለመልቀቅ ተገደዋል፣ አይሮፕላን ማረፊያውም ለሦስት ሰዓት ያህል ስራ አቋርጧል። መጨረሻው ግን ለጥንቃቄ ከተወሰደ ርምጃ ውጪ ምንም ነገር አልተገኘም።

ከጀርመን እራሱን እስላማዊ መንግሥት እያለ በሚጠራው ቡድን በተደጋጋሚ ጥቃት ወደ ተሰነጠረባት ብሪታንያ ስናመራ ደግሞ ሲስኮ በሉኝ ያለን ጎልማሳ፤ የመጠይቁ ውጤት በብሪታንያም ነባራዊውን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ይረዳል።ከኢትዮጵያ ወደ ብሪታንያ ሄዶ ሲኖር ገና ሁለት ዓመት የሆነው ሲስኮ በወጣቱም ሆነ በማህበረሰቡ ላይ ላደረው ስጋት ጥቃት ፈፃሚዎቹን እና ራሷ ብሪታኒያን ተጠያቂ ያደርጋል።

ኢትዮጵያ የሚኖረው ዳዊት እንብዛም የመጠይቁን ይዘት አይጋራም። ለዚህም ምክንያት አለው። ከዚህም በተጨማሪ ወጣቱ በመጠይቁ ተካፍሎ ቢሆን ኖሮ በቀዳሚ የስጋት ደረጃ የሚያስቀምጠው የስራ አጥነት እና ከዛ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ስደት ነው።

 

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ