1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዊኪሊክስ ሚስጢራዊ መረጃዎችና በዓለም ዙሪያ የተሰጡ አስተያየቶች

ረቡዕ፣ ኅዳር 22 2003

የአሜሪካውን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጥብቅ ሚስጥሮችን ትላንት ይፋ ያደረገው ዊክሊክስ የተሰኘው ድህረገጽ በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያ መሆኑ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/QLxb
ዊኪሊክስ እያነጋገረ ነውምስል picture-alliance/dpa

የአሜሪካ መንግስት በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶች የሰበበሰቧቸውንና በጥብቅ ሚስጥርነት የተያዙ መረጃዎች መውጣታቸው በተለይ መረጃዎቹ በስም ጠቅሰው ሚስጥር ገበናቸውን ካጋለጠባቸው ሀገራትና መሪዎች የተሰጠው ምላሽ ጠንካራና በቁጣ የተሞላ ነው። በዊኪሊክስ አማካኝነት የወጣው ሚስጢራዊ መረጃ ብዙዎቹን የአሜሪካ ሸሪክ መንግስታት የሚመለከቱ ናቸው። የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ሻላፊነት መውሰድን የሚሸሹ ብቃት የሌላቸው የሚል መረጃ ነው በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተቀመጠውና በዊኪሊክስ አፈትልኮ ትላንት የወጣው። የኢጣሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ የራስ ስብዕናን አጉልቶ መናገር የተጠናወታቸው ተብለዋል። የዊኪሊክስ ሚስጢራዊ መረጃ ያልነካካው የአሜሪካ ወዳጅ ሀገር መሪ የለም። ዊኪሊክስ የአረብ ሀገራት ለአሜሪካ ሹክ ያሉትንም ይፋ አድርጓል። ሰብዓዊ መብት ማለቷን አቁማ በእስላማዊ ጽንፈኞች ላይ እርምጃ እንድትወስድ አረብ ሀገራቱ አሜሪካንን አንዳማከሩ ዊኪሊክስ አጋልጧል። ግብጽ በተለይ በኢራቅ አሜሪካ የምታደርገውን ዘመቻ ዲሞክራሲና በመገንባት ሳይሆን ኢራንን የሚቋቋም አምባገነን መንግስት በመመስረት ላይ ያነጣጠረ እንዲሆን ማድረግ እንዳለባት አማክራታለች ብሏል ዊኪሊክስ። የሳዑዲው ንጉስ አብዱላህ በጓንታናሞ ተይዘው የሚቆዩ ተጠርጣሪ አክራሪዎች ሲለቀቁ እንቅስቃሴአቸውን የሚቆጣጠር መሳሪያ በሰውነታቸው ውስጥ እንዲደረግ ለአሜሪካ ምክር መስጠታቸውም ተጋልጧል። ሌሎች ሚስጢራዊ መረጃዎችም ሾልከው ወጥተው ዓለምን እያነጋገሩ ነው። በዚህ ዙሪያ ከየአቅጣጫው የሚሰማው አስተያየት በአብዛኛው በሚስጢራዊ መረጃዎቹ መውጣት የተነሳ ተቃውሞንና ቁጣን የሚገልጹ ናቸው። የእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰጡት አስተያየት ግን ለየት ይላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ የመረጃዎቹ መሽሎክ ለሰላም መምጣት አስተዋጾ ይኖራቸዋል አሉ።

ድምጽ

« እንዚህ በቅርብ በተጋለጡት መጃዎች ምክንያት አንዳንድ መሪዎች በሚስጥራዊ ስብሰባ የሚናገሩትን በአደባባይ እንዲናገሩ ድፍረት ይሰጣቸዋል። ይህም ምናልባት ለሰላም ዓይነተኛ ለውጥ የሚያመጣ ይሆናል።»

ትላንት ይፋ የሆኑት የዊኪሊክስን ሚስጢራዊ መረጃዎች ገና ባያበቁም ተቃውሞው ግን ተጠናክሮ እየተሰማ ነው። በዊኪሊክስ ስማቸው ተጠቅሶ በድብቅ የተመካከሩትአደባባይ የወጣባቸው የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርዶጋን አስተያየት ለመስጠት አልቸኩልም ብለዋል።

ድምጽ

«አሁን በዚህን ሰዓት የዊኪሊክስ መረጃዎች ታማኝነታቸው አጠራጣሪ ነው። ስለሆነም ዊኪሊክስ ያገኛቸውን መረጃዎች ይፋ አድርጎ እስኪጨርስ መጠበቅ አለብን። ያን ጊዜ መረጃዎቹን መመዘንና አስተያየት ልንሰጥበት እንችላለን።»

የአሜሪካ መንግስት በጉዳዩ ላይ ባለስልጣናት ተረባርበው መግለጪያ እየሰጡ ናቸው። ዋህይት ሸውስ አስቸኳይ ምርመራ እንዲያደርጉ የፌደራል የወንጀል መርመራ ማዕከላትን አዟል። የአሜሪካው የመከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታገን ለአሜሪካ ደህንነት አደጋ ስለሆነ መንግስት በቶሎ አንዲያስቆም ጠይቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን የመረጃዎቹ መውጣት ከአሜሪካን ይልቅ የሚጎዳው ዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ነው ሲሉ ትላንት ምሽት ገልጸዋል።

ድምጽ

«በግልጽ ለመናገር ይህ ዓይነቱ መረጃ ይፋ መሆን ጥቃቱ ያነጣጠረው በአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ፍላጎትና ጥቅም ላይ አይደለም። ይልቅስ ጥቃቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረ ነው። የህዝብን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል የአሜሪካንንም ብሄራዊ ደህንነት የሚጎዳ ነው»

የዊኪሊክስ ሚስጢራዊ መረጃዎች በእርግጥ አፍሪካንም የተመለከቱ ይገኙበታል። የዚምቧቡዌው መሪ ሙጋቤ በሰፊው ተጠቅሰዋል። የሩዋንዳው ፕሬዝዳንትም እንዲሁ። ያላለቀው ሚስጢራዊ መረጃ ይፋ መሆን እንደዊኪሊክስ ምንጮች ከሆነ ይቀጥላል። ጉድ ገና ይጠበቃል።

መሳይ መኮንን
አርያም ተክሌ