1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውሃ ማጣሪያ ማዕድናዊ ቅመም፣

ረቡዕ፣ ኅዳር 8 2003

አኀዙን በማየትም ሆነ በመስማት ሲያሰላስሉት እጅግ የሚያስደነግጥ ነው ፤ ንፁህ የሚጣጣ ውሃ የማያገኘው የዓለም ህዝብ ቁጥር ከ አንድ ቢሊዮን በላይ ነው። በመሆኑም በቀላሉ ሊወገዱ በሚችሉ ተውሳኮች ሳቢያ ብዙ ህዝብ በአጭር ይቀጫል።

https://p.dw.com/p/QBSM
የውሃ ማጣሪያ ማዕድናዊ ቅመም፣ምስል Jacques Botha/University of Stellenbosch

ችግሩ፣ በአፍሪቃው ክፍለ ዓለም እጅግ የጎላ ሆኖ ሳለ ፍቱን አብነቱም በዚያው በአፍሪቃ ፣ በደቡብ አፍሪቃ የ Stellenbosch ዩኒቨርስቲ ሳይገኝ አልቀረም። ጤናይስጥልን እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፤ ለ 300 ሚሊዮን ያህል የአፍሪቃ ህዝብ ተስፋ የሆነው፣ የውሃ ማጣሪያ ማዕድናዊ ቅመም፣ በሚል ርእስ ያጠናቀርነውን ይሆናል የምናሰማችሁ። በቅድሚያ ግን ከሥነ-ቴክኒክ ጋር ግንኙነት ያለውን አንድ ጉዳይ እናስቀድማለን።

በቂ እንቅልፍ ባለማግኘት ለሴኮንድ ያህል ለሚያንጎላጁ አውቶሞቢል አሽከርካሪዎች፣ አደጋ አስጠንቃቂ መሣሪያ ተፈለሰፈ፤

በቂ እንቅልፍ ሳያገኙ፣ አውቶቡሶችን ፣ የጭነት ተሽከርካሪዎችንም ሆነ የቤት መኪናዎችን የሚነዱ ሰዎች፣ በጉዞ ላይ እንዳሉ አልፎ-አልፎ በሚያጋጥም ቅጽበታዊ ማንጎላጀት ወይም የሴኮንድ እንቅልፍ፣ አደጋ በማድረስ ለራሳቸውና ለሌሎች መቁሰል ብሎም ህይወት መጥፋት ሰበብ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው።

ታዲያ ለችግሩ መፍትኄ ሲሹ ከነበሩት፣ ከጀርመን ታዋቂ የምርምር ተቋማት መካከል አንዱ፣ «ፍራውንሆፈር ተቋም» ፣ አብነቱን ማግኘቱን አብሥሯል። የዐይን ብሌንና የዐይን ቆብን ይዞታ ፣ የሽፋሽፍትን እንቅሥቃሴ በመከታተል ፣ ቀስ እያለ ፣ ዐይን ጭፍን፣-ጭፍን ሲል የሚመዘግበው ፤ ድካም መኖሩን የሚጠቁመው ፣ ከመሪው ላይ የሚጣበቀው መሣሪያ ፣ ብልጭ-ብልጭ በሚል የማስጠንቀቂያ መብራት ወይም በሚጮህ ድምፅ፣ አሽከርካሪው ተገቢውን እርምጃ ይወስድ ዘንድ ያሳስባል ማለት ነው።

ይህን ፣ በእንግሊዝኛ Eye Tracker የሚል ስያሜ የተሰጠውን ፣ አሽከርካሪዎችን የሚያስጠነቅቀውን መሣሪያ የሠሩት ተመራማሪ፣ ፍራንክ ክሌፌንትዝ ፣ እሽቱትጋርት ጀርመን ውስጥ Vision በሚል መፈክር በተካሄደው ትርዒት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ እይታ እንዲቀርብ አድርገዋል።

የጀርመን የትራፊክ ደኅንነት ጉዳይ መ/ቤት እንዳስታወቀው በጀርመን ሀገር ከ የ 4 የመኪና አደጋዎች አንዱ የሚያጋጥመው በአሽከርካሪዎች ቅጽበታዊ ማንጎላጀትም ሆነ የአንዲት ሴኮንድ እንቅልፍ ሳቢያ ነው። ይኸው በድካም ሳቢያ የሚያጋጥም የአንዲት ሴኮንድ እንቅልፍ፣ በተለይ እጅግ አደገኛ የሚሆነው በፍጥነት ሲያሽከረክሩ ነው። በሰዓት 130 ኪሎሜትር ፍጥነት የሚሽከረከር አውቶሞቢል፣ በ 5 ሴኮንድ ውስጥ 180 ሜትር ነው የሚጓዘው።

በአሁኑ ጊዜ በቱዑሪንገን ፌደራል ክፍለ-ሀገር ኢልመናው በተባለ ቦታ ፤ ከተለያዩ የአውቶሞቢል ኩባንያዎች ጋር በመስማማት ሙከራውን በተጨባጭ ሁኔታ በመፈተሽ ላይ የሚገኘው ፍራውንሆፈር ተቋም፣ ባልደረባና የ «ዐይ ትራከር» ፈልሳፊ ፍራንክ ክሌፈንትዝ፣ እንደሚሉት፣ መሣሪያው አሽከርካሪው ሳያስተውለው የራሱን ተግባር የሚፈጽም ሲሆን፤ ጠቆር ያለ የፀሐይ መነጽር ቢደረግም እንኳ በቀይ ጨረር ስለሚሠራ በጨለማም ቢሆን ተግባሩን ያከናውናል ማለት ነው። ከውጭ የሚንጸባረቅ መብራት ፣ ተግባሩን አያሠናክልበትም። «ዐይ ትራከር» የተባለው ይኸው መሣሪያ፣ የሚጠቀምበትን አሽከርካሪ የራስ መጠን፣ የዐይንን እንቅሥቃሤ፣ የሽፋሽፍትን መርገብገብ የሚመዘግብ ሲሆን ፣ ሁኔታውን ለማመሣከር ቢፈለግም መረጃ ይሰጣል ማለት ነው።

«ዐይ ትራከር» በመጀመሪያ ለአውቶቡስና የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ይሆናል እንዲውል የሚደረገው። ዋጋው ያን ያህል ውድ ባለመሆኑም ለሁሉም እንዲዳረስ ሳይደረግ አይቀርም። ከመጪው 2011 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት አንስቶ ተግባራዊ እንደሚሆን የተነገረለት የዐይን እንቅሥቃሴ ተከታታይና ማስጠንቀቂያ መልእክት አቅራቢ መሣሪያ ወጋው ከ 100 ዩውሮ ቢያንስ እንጂ እንደማይበልጥ ነው ክሌፌንትዝ የጠቆሙት።

Eye Tracker Interface
የሽከርካሪዎች አይን መድከሙን የሚጠቁመዉ መሳሪያ (Eye Tracker)ምስል flickr/cfarivar

የውሃ ማጣሪያ ማዕድናዊ ቅመም፣

ለአንድ ብርጭቆ ሻይ የሚውል ንዑስ የሻይ ከረጢት በሚያክል ተመሳሳይ መያዣ፣ በፕላስቲክ መሰል ንዑስ ከረጢት የሚታሸግ የላመ ጥቁር ድንጋይ የሚመስል ማዕድናዊ ቅመም ነው። የተቀመመው፣ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በእስቴለንቦሽ ዩኒቨርስቲ ነው። ዋጋው ርካሽ ሲሆን ፣ በቀላሉ ወደየትኛውም ቦታ ማጓጓዝ ይቻላል።

(ATMO)-----

ማርሊዝ ቦታ ይባላሉ ተመራማሪዋ፣ በኢንዱስትሪ ከመመሥረቱ በፊት የመጨረሻውን ፍተሻ ያደርጋሉ። የሥነ-ህይወት ተመራማሪዋ ፣ በፕላስቲክ ጠርሙስ የተሞላውን ግማሽ ሊትር ውሃ ፣ ንዑሷን የሻይ ከረጢት በምትመስለው የማዕድን ቅመም በተሞላችው ከረጢት ላይ በማፍሰስም ሆነ በማንቆርቆር ወሃውን ያጠራቅማሉ። ከዚያም ይመረምሩታል። 30 እስኩየር ሜትር የማይሞላ ስፋት ባለው የእስቴለንቦሽ ዩኒቨርስቲ ቤተ-ሙከራ ነው እንግዲህ የውሃ ማጣሪያው ንዑስ ከረጢት የተዘጋጀው።

«ማጣሪያው፤ በዋጋ ረገድ ረከስ ያለ ነው። ከውሃ ወይም ከሌላ በገበያ ከሚገኝ ማጣሪያ ይረክሳል። ክብደቱም በጣም ቀላል በመሆኑ ፈንጠር ብለው ለሚገኙ አካባቢዎች ለማዳረስ ከባድ አይደለም። ማጣሪያው፣ በቆሸሸው ውሃ ውስጥ የሚገኙ ተኀዋስያንን መለየት ብቻ ሳይሆን ቀስ በቀስ ይገድላቸዋል። ስለዚህ ወደ ነበሩበት ተመልሰው የማንሠራራት ዕድል የላቸውም።»

በዛ ያሉ የእርዳታ ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር ፤ ማመልከቻ አስገብቷል። የውሃ ማጣሪያውን የሚፈልጉት ብዙዎች ናቸው። ይህ የሚያስገርም ላይሆን ይችላል። በአፍሪቃ ብቻ፣ 300 ሚሊዮን ያህል ህዝብ፣ ንፁህ የሚጠጣ ውሃ አያገኝም። ይሁንና ፕሮፌሰር ኦይገን ክሎትና ባልደረቦቻቸው ማጣሪያውን ለመፈልሰፍ የተነሳሱት ባጋጣሚ ነው።

«በመጀመሪያ በዚህ አቅጣጫ አልነበረም ምርምራችን ያተኮረው። እንደ እውነቱ ከሆነ ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች የሚጠቀሙበት ማጣሪያ ለመፈልሰፍ ነበረ ያተኮርነው። ነገር ግን እንደሚታወቀው በቤተ-ሙከራ ምርምር ሲደረግ፣ በጥቂት ነገር ነው የሚተኮረው። በጥቂት የውሃ መጠን ውጤት ካገኘሁ በኋላ ነበረ፣ ንዑስ የውሃ ማጣሪያ ለመሥራት፣ ማሰብ ማሰላሰል የጀመርሁ።»

ታዲያ፣ በዚህ ሁኔታ ነበረ፣ ለአንድ ጊዜ የሚሆን የሻይ ንዑስ ከረጢት (Tee Bag )የመሰለ የውሃ ማጣሪያ ንዑስ ከረጢት የማዘጋጀቱ ሐሳብ የመጣልኝ። የደቡብ አፍሪቃ ሻይ «ሮይቡስ» ወይም ጥቁር ሻይ ሳይሆን፣ በማጣሪያው ውስጥ፣ በውሃ የውስጥ የሚጎኙ ጎጂ ነገሮችን የሚያጣራ የተፈጨ ወይም የደቀቀ ልዩ የድንጋይ ከሰል እንዲሞላበት የተደረገው። አዲሱ ነገር ፣ የማጣሪያው ወረቀት ዓይነት ነው ። እርሱም በኢምንት ቀጫጭን ገመድ መሰል ነገር በተሠራ ንዑስ ከረጢት፣ በሚታሸገው ማጣሪያ ማዕድናዊ ቅመም፣ ተኀዋስያን ተለይተው ውሃው እንዲጣራ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዚሁ የማጣራት ተግባር ተኀዋስያኑ ይሞታሉ። በወንጠፍት መሰሉ መሳሪያ የሚጣራው ውሃም በፕላስቲክ ጠርሙስ እየተጠራቀመ ለመጠጥ ውሃ ይዘጋጃል።

«እዚህ የምናደርገው፤ በኢምንት ሥነ ቴክኒክ በመጠቀም እጅግ የደኸዩ ሰዎችን ለመርዳት ቆርጦ መነሳት ነው። ኑሮአቸው እንዲለወጥ እናደርጋለን። የሰዎችን ተስፋ የማለምለሙን ነገር በማሰብ ሰው ሊገነዘበው ይችል ይሆናል። ከእንግዲህ፣ የቆሸሸ ውሃ በመጠጣት ብቻ አንድም ልጅ ተቅማጥ ይዞት ሊሞት አይገባም።»

ኬፕታውን አቅራቢያ የሚገኘው የእስቴለንቦሽ ዩኒቨርስቲ፣ በንዑስ ፍጡራን ሥነ ህይወት ላይ ምርምር ባደረጉት ክሎት ና ባልደረቦቻቸው ኩራት ይሰማዋል። ዩኒቨርስቲው እስካሁን በምርምር ስኬታማ ውጤት ካስመዘገበባቸው አንዱ ይኸው የውሃ ማጣሪያ ሲሆን ፣ እርሱም፣ የወደፊት አቅዱን በተመለከተ ብሩኅ ተስፋን ያስጨበጠ ሆኗል። አንድ ዘመን የዘረኛው ሥርዓት (አፓርታይድ) ካድሬዎች መመልመያ የነበረው የተጠቀሰው ዩኒቨርስቲ፣ ከአሳፋሪ ታሪኩ ተላቆ፣ አሁን ስሙን ሊያድሥለት የሚችል «ተስፋ» የተባለ ፕሮጀክት አቋቋሞአል። ወደፊት የደቡብ አፍሪቃና የክፍለ ዓለሙ ችግሮች መፍቻቸው፣ ምርምር ፣ ሲሆን ፣ ከውሃ ማጣሪያው ፈልሳፊዎች መካከል ዴዝመንድ ቶማስ የተባሉት ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል።

«እስቴለንቦሽን የመሰለ የከፍተኛ ትምህርት ተቋምና ሌሎች የደቡብ አፍሪቃ ዩኒቨርስቲዎች፣ የአድሎአዊው ፤ ዘረኛ (አፓርታይድ)ሥርዓት አካላት ነበሩ። አሁን ይህን አቁመን ፣ ያለፈውን ስህተት ለማረም ወስነናል።»

የእስቴለንቦሽ ዩኒቨርስቲ ብቻውን ሊያሳካው የማይቻለው አንድ አቅድም ሆነ ራእይ አለው። በሚመጡት ሳምንታት የዩንቨርስቲው ተማሪዎችና ፕሮፌሰሮች፣ «ሆፕ» የተሰኘውን ፕሮጀክታቸውን ለማስተዋወቅ ከአፍሪቃ፤ አሜሪካና አውሮፓ ዩኑኒቨርስቲዎችም ጋር መተባበር የሚቻልበትን ብልኀት ለመሻት ከአገር አገር ከክፍለ-ዓለም ክፍለ-ዓለም ይዘዋወራሉ። የእስቴለንቦሽ የመጪው ዓመት መርኀ-ግብር ፣ ልክ እንደዚህ ክፍለ ጊዜ መጠሪያ ሳይንስና ኅብረተሰብ፤ «ሳይንስ ለኅብረተሰብ» የተሰኘ ነው ። ኅብረተሰብን የሚታደግ ሳይንስ ነውና!

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ