1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዐረብ መገናኛ ብዙኀንና የነጻነት ትግል፣

ሰኞ፣ ነሐሴ 21 2004

ውጊያ በሚካሄድበት ሶሪያ 30 ያህል ጋዜጠኞች ህይወታቸውን አጥተዋል። በግብፅ የመንግሥት ጋዜጠኞች ዋና አዘጋጂዎች ተለዋውጠዋል። በቱኒሲያ የመገናኛ ብዙኀን መርኅ የጠጠረ መስሏል ከባህረ ሰላጤው የዐረብ አገሮችና ከኢራን የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ጋር

https://p.dw.com/p/15xf1
ምስል Reuters

የተያዘው ፉክክርም ቀላል አይደለም። በዓረቡ ዓለም ፣ የለውጥ እንቅሥቃሤ ከተዛመተ ወዲህ ፣ የመገናኛ ብዙኀን ነጻነትና አሠራር የያዘው አቅጣጫ ምን ይመስላል?

በዐረቡ ዓለም ፣ የመገናኛ ብዙኀን አሠራር ፤ ከሰላማዊው አብዮት ወዲህ ፣ በአሁኑ ጊዜ ውስብስብ ያለ እንዳንዴም ግራ የሚያገባ ነው የሚመስለው። በመካከለኛው ምሥራቅ የዓለም አቀፉ የድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት (RSF) ተመራማሪ ሶአዚግ ዶሌት እንደምትለው፣ ሰላማዊው አብዮት እንደተጀመረ በብዙዎቹ የዐረብ አገሮች ፈጣን እመርታን ነበረ ያሳየው። ይሁን እንጂ ፈተናው አሁንም አለ።

«በአጠቃላይ ከአብዮቱ ወዲህ የፕረስ ነጻነት በብዙ የዐረብ ሀገራት፤ እመርታ ማሳየቱ አልቀረም። ግን ሁኔታው የሚያረካ አይደለም። የፕረስ ነጻነት እንዳይሸረሸርም ሆነ እንዳይገታ ሥጋት አለ። የፕረስ ነጻነት ድል ስለማድረጉ ለመናገር፣ አንዳች አስተማማኝ ሁኔታ የለም።»

Syrien - Neue Proteste gegen Assad
ምስል AP

ሰላማዊው አብዮት በተካሄደበት ወቅት፣ በተለይ በግብፅ ሀገር፤ ቴሌቭዥኑ፤ ጋዜጦችና ኢንተርኔት የፖለቲካውን ሂደት በመቀየስ ረገድ ጭምር አስተዋጽዖ አድርገዋል። በፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ የተፋፋመው ተቃውሞ ውጤታማ እንዲሆን ካበቁት አንዱ ዋና ጣቢያው በቓጣር የሚገኘው አል ጀዚራ የተባለው የቴሌቭዥን ድርጅት ዘገባ ነው።

ከመንግሥት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ይልቅ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ነበሩ ተጠናክረው የለውጡን ሂደት ይመሩ የነበሩት። ይህንም ቴሌቭዥኑ በሚገባ አስተጋብቷል።ስለሆነም የተቃውሞ ሰልፉ ከተጀመረ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ እ ጎ አ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ ም፤ ሙባረክ አልጄዚራ በግብፅ እንዳይሠራጭ ተመለካቾችም ዝግጅቱን እንዳይከታተሉ አዘዙ።

Said Ferjani Leiter der islamistischen Ennahda Regierungs Partei Ennahda Partei
ምስል Reese Erlich

በሶሪያም በበሺር ኧል አሰድ አገዛዝ ላይ በመካሄድ ላይ ያለውን የተቃውሞ እንቅሥቃሴ ሰፊ ድርሻ በማበርከት በተለይም ለተፋላሚዎቹ ወገኖች ድጋፉን በመስጠት ሰፊ አስተዋጽዖ ከማድረጉም፤ የአሰድን አገዛዝ መግለጫ ተዓማኒነት እንዲያጣ ማድረጉ ይነገርለታል። ከዚህ ተመክሮ በመነሳትም የመካከለኛው ምሥራቅ መንግሥታት ብሔራዊ የመገናኛ ተቋማትን በከፊልም ቢሆን ለመቆጣጠር በመሞከር ላይ መሆናቸው ታውቋል። በቱሲያ መገናኛ ብዙኀን አስተማማኝ ዋስትና እንዲኖራቸው ይጸድቃል የተባለው አዲስ ህግ በመጓተት ላይ ሲሆን፣ «ናህዳ»የተባለው ገዥው እስላማዊ ፓርቲ ፤ በራዲዮ ቴሌቭዥንና ጋዜጦች ዋና -ዋና አዘጋጂዎችን ራሱ በመምረጥ የወሰደው እርምጃ ተጽእኖ በማድረግ ላይ መሆኑን የሚጠቁም ነው ስትል ዶሌት ሥጋቷን ገልጻለች። በግብፅም የሚያሳስብ ሁኔታ ነው የተከሠተው። ሙባራክ በሥልጣን ላይ የሉም። ይሁን እንጂ ከፊሉ የሥርዓታቸው ሰዎች አሁንም አሉ። በፕሬዚዳንት ሙርሲ ትእዛዝ በመግሥት መገናኛ ብዙኀን አዘጋጂዎች እንዲለወጡ መደረጉ፤በተዘዋዋሪ መንገድም ቢሆን የመቆጣጠር ፍላጎት ለመኖሩ ጠቋሚ ነው።

በመካከለኛው ምሥራቅ የቀድሞው የ „CBS News” ዘጋቢና አሁን በ«ዋሽንግተን እስቴት ዩንቨርስቲ» ስለዐረቡ ዓለም የመገናኛ ብዙኀን አሠራር ጠቃሚ ንግግር የሚያሰሙት ሎረንስ ፒንታክ፤ ዶቸ ቨለ ባደረገላቸው ቃለ ምልልስ እንዳሉት ከሆነ፤ከባድ ፈተና አለ በተለይ በግብፅ መገናኛ ብዙኀን ላይ

Skulptur Selbstverbrennung Mohammed Bouzizi Sidi Bouzid Tunesien
ምስል Reese Erlich

«የመገናኛ ብዙኀኑ ነጻነት አደጋ ነው የተደቀነበት። የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን አሁንም ለአዲሱ ገዢ ፓርቲ አፈ ቀላጤ እንዲሆኑ በመገደድ ላይ ናቸው። ሌላ አገዛዝ ቢሆንም ሌሎች የመገናኛ ብዙኀን መሪዎች ፤ሰዎች ናቸው ለሥራው የተመደቡት። ነጻ ሆኖ መንቀሳቀስ ጀምሮ የነበረው መገናኛ ብዙኀን ፣ ወደፊት አንድ እመርታ ከተጓዘ በኋላ፤ ሁለት እርምጃ ወደኋላ መመለስ ግድ ሆኖበታል።

።እርግጥ በትጋት ዝግጅቶችን የሚያቀርቡ ተደማጭነትና ተመላካችም ያላቸው መገናኛ ብዙኀን አልታጡም ፣ ይሁን እንጂ ከመንግሥት ተጽእኖ አልተላቀቁም።

ካለፉት ጥቂት ዓመታት አንዳንድ ምሳሌዎችን መጥቀስ እንችላለን። ዮርሲ ፉዳ የሚያዘጋጀው ውይይት፤ በወታደራዊው ም/ቤት ባደረገበት ተጽእኖ አልፎ- አልፎ ማቋረጥ ነበረበት። በግብፅ የመገናኛ ብዙኀን፤ ሙርሲና የፖለቲካ አማካሪዎቻቸው ፍጹም ነጻ ለሆነ የፕረስ አገልግሎት የቆሙ ናቸው ብሎ የሚናገር ቢገኝ እጅግ ነው የምገረመው።»

Symbolbild Arabischer Frühling Saudi-Arabien
ምስል AP

ፒንታክ እንዳሉት፤ በዐረቡ ልሣነ ምድርም ተጽእኖው እንዳለ ነው። እርግጥ ነው የስዑዲ መገናኛ ብዙኀን የመሻሻል ምልክት ይታይባቸዋል፤ ነገር ግን ብዙ መገደቢያ መሥመሮች አሉ። ለዘብ ያለ አቋም ያላቸው ሲነቃቁ፤ ወግ አጥባቂዎች የሚባሉት ገደብ እየተደረገባቸው ነው ይባላል። ሶአዚግ ዶሌት እንደምትለው የባህረ ሰላጤው መገናኛ ብዙኀን ወደፊት ከኢራን በኩል ጠንከር ያለ ፉክክር ይሆናል የሚያጋጥማቸው።

በአካባቢው በመረጃ አቅርቦት መሪ ሆኖ ለመገኘት «የመረጃ ጦርነት » የሚሰኘው ትግል መካሄዱ አይቀሬ ነው። «አል ጀዚራ» ና «ኧል ዐረቢያ፣ ለጊዜው በባህረ ሰላጤው አገሮች የመሪነቱን ቦታ ይዘዋል። በተንቀሳቃሽ ስዕልና ድምጽ የሚደረገው የመገናኛ ብዙኀን ትግል ባጋደለና ፕሮፖጋንዳነት ባለው መልኩም ይሆናል የሚካሄደው።

ተክሌ የኋላ

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ